የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 14 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 14 ቀን 2011 ዓ.ም

ፓርላማው በዛሬ ዉሎው የኢትዮ -ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ ዝርጋታን ስምምነት አፀደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ማስተላለፊያን ለመዘርጋት የተደረሰውን ስምምነት እና የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት ሲያካሂድ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል። በዚህ ወቅት ከህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ አበበ ጉዴቦ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁ ላይ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር፣ እንዲሁም ከሕዝብ ክንፍ ጋር በቂ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ፣የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት እና ህገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ ህጎች፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ፈርማ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት እስረኞችን በመጠበቅ እና በማነፅ የተጣለበትን ሓላፊነት እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ የማረሚያ ቤቶችን አደረጃጀት የተሻለ ለማድረግ ፣ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከተልዕኳቸው ጋር የሚመጣጠን “የማረሚያ ቤት ፖሊስ”የሚል ስያሜ አግኝተው፣ ደረጃውን እና ሓላፊነቱን የሚገልፅ ማእረግ እና ምልክት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑንም የቋሚ ኮሚቴው አባል ገልፀዋል።

ማረሚያ ቤቶች የእስረኞችን ሰብኣዊ መብት በማክበር ፣ እንዲሁም የእስረኞቹ ግላዊ ሁኔታ በሚጠይቀው የፍርድ አፈጻጸም እና እርማት ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ እውቀትና ክህሎትን አዳብረው ከኅብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑም በተያያዥነት ተጠቅሷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያዩ በኋላ ፣ አዋጁን በሙሉ ደምጽ አጽድቀዋል። በመቀጠልም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረሰውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ተመልክቷል።

ከተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ ፣ ረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጋዝ በሚዘረጋው ቧንቧ በማስተላለፍ፤ ጋዙን ለሚጠቀሙ ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችላት መሆኑን ተናግረዋል።

የቧንቧ መስመሩ ባለቤት ኢትዮጵያ መሆኗን በረቂቁ ላይ በግልፅ መቀመጡን ፣ በሀገራቱ መካከል የተደረሰው የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስምምነት ዓለም አቀፍ የስምምነት ደረጃ መስፈርትን የሚያሟላ እና ከዚህ በፊት በሀገራቱ መካከል የነበሩ ስምምነቶችን የሚያጠናክር መሆኑንም አመላክተዋል።

በዚህ መሠረት የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረሰውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ደምጽ አፅድቀዋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ በውጭ አገራት ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበ ረቀቅ አዋጅንም በዛሬው ዕለት ሲመለከት መዋሉን ሰምተናል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ የግልግል ዳኝነት እና ስምምነት በአባል አገራት ፍርድ ቤቶች እውቅና እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ጠቁመው ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚረዳ መሆኑን እና የውጭ አገራት ኢንቨስትመንት እና ንግድን እንደሚያበረታታም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ብትቀበለው እና ብታፀድቀው በአገሪቱ የሚሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች በሌሎች አገራት ተፈፃሚ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም በሌሎች አገራት የተወሰኑ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ እንዲፈፀሙ በማድረግ ነገሮችን ለማቀላጠፍ እና ለማቃለል ይረዳል ሲሉ ተደምጠዋል።

ከአስፈፃሚ ጋር በተያያዘ በረቂቅ አዋጁ አስፈፃሚው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከሌሎች አካላት ጋር የሚለው ለምን በዝርዝር ለፖሊስ እና ፍርድ ቤት በሚል በግልፅ የሚል ጥያቄ የምክር ቤቱ አባላት አቀርበዋል።

ምክር ቤቱም ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ በዋናነት ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።

ከባድ የሙስና ወንጀል ተሠርቶባቸዋል በተባሉ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥናት ተጠናቀቀ

ትልልቅ የሙስና ወንጀል ተሠርቶባቸዋል ተብለው በተጠረጠሩ ተቋማት ላይ የተደረገው ጥናት መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አረጋገጠ::

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ባለፉት ስድስት ወራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጠጣር የሚያስችሉ መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የተሳካ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል።

የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመከላከል በኩል በግብር ስወራ፣ ኮንትሮባንድ እና የጨው ምርት ሽያጭ አሻጥር ላይ ተቋሙ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ መረጃ ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ደመላሽ ፤ ከግብር ስወራ እና የመንግሥት ሀብት ምዝበራ አንፃር ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ሀብት ለማዳን ያስቻለ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል በተባሉ የመንግሥት ተቋማት ላይ ጥናቶችን አጠናቆ ለመንግሥት ማስረከቡንም ይፋ አድርገዋል::

በአዲስ አበባ በአምስት ወራት ውስጥ ፣ 84 መኪኖች ተሰርቀዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ከሐምሌ 2011 እስከ ኅዳር 2012 ባሉት አምስት ወራት ውስጥ ፣ 84 መኪኖች ተሰርቀው መወሰዳቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአምስት ወራት ውስጥ የመጡትን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ በተደረገ ክትትል 62 ተሽከርካሪዎች በአሳቻ ቦታዎች ላይ ተጥለው የተገኙ ሲሆን፣ እንደ ጎማ እና የኋላ መመልከቻ መስታወት ያሉ ክፍሎቻቸው ተወስደው መገኘታቸውንም ገልጿል።

ቀሪ 22 ተሽከርካሪዎች ላይ ከተፈፀመው ዝርፊያ ውስጥ ፣ከ15ቱ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ አረጋግጠዋል።

አብዛኛዎቹ ሪፖርቶች መኪና የሚያከራዩ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ናቸው ያሉት ሓላፊው፣ መኪና የሚያከራዩ ግለሰቦች የሚያከራዩአቸውን ሰዎች ማንነት ሳያረጋግጡ በመስጠት ፤ በተሽከርካሪዎቹ ለሚፈፀሙ የንጥቂያ እና ዝርፊያ ወንጀሎች ምክንያት ይሆናሉ ካሉ በኋላ ወንጀለኞቹመኪኖቹን ለረዥም ጊዜያት ይዘው በመጥፋት የመኪኖቹን አካላት በመነቃቀል ጥፋት የሚያደርሱ እንዳሉም አጋልጠዋል።

ከዚህ ሌላ በመንደር ውስጥ የሚፈፀም የመኪና ሽያጭ ውል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ነው ያሉት ኮማንደር ፋሲካ፣ የመኪና ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቹን በትውውቅ እና በሰፈሮች ውስጥ በሚፈፀም ውል በሕገወጥ መንገድ ይሸጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የመኪና ስርቆቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚፈፀም ሲሆን፣ በኪራይ የሚንቀሳቀሱ መኪኖች የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመባቸው በኋላ በቀጥታ የሚያዙት የመኪናው ባለቤት ሆነው የተመዘገቡ ግለሰቦች መሆናቸውን እና ፖሊስ በሚያደርገው ምርመራ መኪኖች በሕገ ወጥ መንገድ እንደ ተሸጡ እንደሚደረስበትም አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አረጋግጧል።

ግለሰቦቹ ተሽከርካሪዎቹን ከሸጡ በኋላ ቀሪ ክፍያ ለማግኘት ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የመኪና ስርቆት የተፈፀመባቸው በማስመሰል ለፖሊስ እንደሚያመለክቱም ነው የተነገረው።

በጦር መሣሪያ የተደገፈ ስርቆት፣ የመኪና እና የመኪና አካላት ስርቆት፣ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም የሚፈፀም ዝርፊያ እና የመግደል ሙከራን የመሳሰሉ ዐስር ከባድ ወንጀሎችን በመለየት ኮሚሽኑ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ለመከላከል እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ፤የጦር መሣሪያ በመጠቀም በሩብ ዓመቱ የገንዘብ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ሦስት ዝርፊያዎች መፈፀማቸው እና ሌሎች ኹለት የዝርፊያ ሙከራዎችን መቆጣጠር መቻሉንም ይፋ አድርገዋል::

እነዚህ ግለሰቦች ወንጀሎችን የሚፈፅሙት የከተማዋ ነዋሪ ያለመረጋጋት ስሜት እንዲፈጠርበት ለማድረግ እና ዝርፊያ እና የወንጀል ድርጊቶች የተስፋፉ ለማስመሰል በሚደረግ ጥረት ግነት እንዳስተዋሉ ኮማንደር ፋሲካ ጠቅሰው፣ ወንጀሎቹ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን አመላክተዋል።

ባለፉት ወራት በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጠሩ ግጭቶች እና ያለመረጋጋቶች ወደ ከተማዋ ተዛምተው ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስ ነበር ያሉት ሓላፊው፣ የአዲስ አባባ ፖሊስ ኮሚሽን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር እና የአዲስ አበባ ዙሪያን ከሚያዋስኑ ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር ግጭቶቹ ወደ ከተማዋ እንዳይዛመቱ ለማድረግ መሠራቱንም ገልፀዋል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንጋፋ የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ፣ የወንጀል ድርጊቶቹ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ነፀብራቅ ናቸው ያሉ ሲሆን፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲሁም ሌሎች ለፖለቲካዊ ትርፍ ወንጀሎችን ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ነው የሚናገሩት።

ለውጡን ተከትሎ እንደ ፖሊስ እና ደኅንነት ያሉ ተቋማት ላይ የተደረጉት ለውጦች፣ ተቋማቱን አፈራርሰው እንደ አዲስ ያዋቀሩ በመሆናቸው በተቋማቱ ውስጥ አለመረጋጋት እና ድክመት ይስተዋላልም ብለዋል። ተቋማት ላይ ለውጥ ሲደረግ ያላቸውን ጠንካራ ጎን መሰረት አድርጎ ሊሆን ሲገባው፣ ለውጡ የተደረገው ግን ተቋማቱን እንደ አዲስ በማዋቀር ነው ከማለታቸው በተጨማሪ ፤ በከተማዋ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እና ሥራ አጥነት ወጣቱ ወደ ሱስ እንዲሰማራ አድርጎታል ብለው፣ አስከፊው ነገር ደግሞ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት ብርሃን የሚያሳይ ተስፋ አለመኖሩ ኅብረተሰቡ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ይህም ለወንጀል መስፋፋት ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ አብራርተዋል።

እነዚህን ችግሮች እንደ አገር ለመቅረፍ እና አለመረጋጋቶችን ለማስወገድ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምሁራን የተሳተፉበት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ እንደሚገባም መክረዋል::

በስተመጨረሻም ኅብረተሰቡ ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ ተሽከርካሪዎችን፣ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት እና የሚያስጠረጥሩ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለኮሚሽኑ በማሳወቅ ከፖሊስ ጋር ሊተባበር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል።


የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ ኩባንያ  ጋር ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተፈራረመ

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ (CCECC) ኩባንያ ጋር የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ስምምነት ተፈራርሟል::

ስምምነቱን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ ቡህ እና የሲሲ.ኢ.ሲሲ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጉዎ ቾንግፌንግ በድሬዳዋ ከተማ ፈጽመዋል። ትናንትየተፈረመው ስምምነት በከተማዋ የቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ (CCECC) በመጀመሪያ ዙር በ370 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት የሚያስችለው መሆኑን የድሬደዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

የቻይናው ሲሲ.ኢ.ሲሲ በድሬዳዋ መልካጀብዱ አካባቢ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብቶ የቻይና በተለይም ፣ የድሬዳዋ እህት ከተማ ከሆነችው የኩንሻን ከተማ ባለሀብቶችን ለማምጣት አቅዶ እየሠራ ነው ተብሏል።

አሁን የተደረሰው የ370 ሄክታር መሬት ስምምነት የመጀመሪያ ዙር እንደሆነ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን ፣በአጭር ጊዜ ውስጥ የመሬት ርክክቡ ተጠናቆ የግንባታ ሥራው እንደሚጀመርና በሚጠበቀው የኢንዱስትሪ ፓርክ ከግንባታው ጀምሮ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገምቷል።

ቀደም ሲል ምክትል ከንቲባ አህመድ ቡህ የድሬዳዋ እህት ከተማ በሆነችው ኩንሻን ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ፣ ሁለቱ ከተሞች በቀጣይ የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነት በተለይም የሲሲ.ኢ.ሲ.ሲ ኩባንያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ለማስጀመር እና ኢንቨስትመንትን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም::


ብሔራዊ የመረጃና ደሕንነት ተቋም በዲግሪ ደረጃ የደህንነት ትምህርት ሊሰጥ ነው

ባለፉት 30 ዓመታት ከነበረው ድብቅ የኢሕአዴጋዊ የጸጥታ ተቋም ለየት ብሎ አመራሩ ጭምር በይፋ የሚታወቀው ብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የስያሜ ለውጥ ሊያደርግ መሆኑ ታወቀ።

በሕወሓት መራሹና በጨለማው ዘመን መንግሥት በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መ/ቤት በመላ አገሪቱ ስርዓቱን የሚተቹና የማይደግፉ ንጹሃን ዜጎችን አፍኖ በመውሰድ ዘግናኝ ግፍ ሲፈጽም ከመኖሩ ባሻገር በሽብርተኝነት እየከሰሰ እና የሐሰት ማስረጃ እየፈበረከ እንደፈለገ ሲያስር የቆየ ጨቋኝ ተቋም እንደሆነ አይዘነጋም::

አሁን ላይ ስያሜውን ሊቀይር የተዘጋጀው ብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደመላሽ ገብረሚካኤል ፤ ስር ነቀል ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ላይ ያለው መ/ቤታቸው የስያሜ እና አሠራር ለውጥ የሚያደርግበት ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ይናገራሉ።

ረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ስያሜን ወደ ብሔራዊ መረጃ ማዕከል (ኤን አይ ሲ) እንዲሻሻል ይጠይቃል። በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ከፖለቲካ፣ ብሔር እና ሃይማኖት ጥገኝነት የተላቀቀ ነፃ የመረጃ እና ደህንነት ተቋም የመፍጠር የማሻሻያ ሥራአንዱ አካል እንደሆነም ተገልጿል።

ይህንን ተቋማዊ ማሻሻያውን ተከትሎ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት በአስር አመት ወስጥ ሊደርስበት የሚችለውን ደረጃ የሚያመላክት የአስር አመት ስትራቴጂክ እቅድም ተዘጋጅቷል። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የየወቅቱን የአገሪቱን የሽብር ስጋት ደረጃ የሚያሳይ መዘጋጀቱም ተጠቅሷል።

ተቋሙ ራሱን በሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ ከማብቃት አንፃር በዲግሪ ደረጃ የመረጃ እና ደህንነት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

LEAVE A REPLY