የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 16 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 16 ቀን 2011 ዓ.ም

ግጭት ያልራቃቸው  የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ክልሎች የሰላም ኮንፍረስ ተጀመረ

የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል። የሁለቱ ክልል ህዝቦች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ባለመው ኮንፈረንስ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።

የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ህዝቦችን ግንኙነት በሠላምና በልማት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አቋቁመው የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ናቸው።

በኮንፈረንሱ ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ገመዳ ፈቃዱ “እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ፌዴራሊዝም ስርዓት ተመራጭ ነው” ብለዋል። በፌዴራሊዝም ስርዓት ውስጥ ስምምነት፣ መቻቻል፣ መተባበር፣ መተዋወቅን ማዳበር፣ ተጠያቂነትን መውሰድና ሥራዎችን በጥንቃቄ መፈጸም እንደሚያስፈልግ፣ ሁሉንም ያቀፈ የልማት ተጠቃሚነትን እና ፍትህን ማረጋገጥ እንደሚገባም ዶክተር ገመዳ ገልጸዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመለየት ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ምህሩ፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን የሁለቱን ክልል ህዝቦች ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

“በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው አለመግባባት በፖለቲከኞች የመጣ ነው” ያሉት ተሳታፊዎቹ፣ የሁለቱን ህዝቦች በሠላምና በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመው የጋራ ጽሕፈት ቤት የጀመራቸው ተግባራት እንዲጠናከሩም ጠይቀዋል።

የሚፈጠሩ ግጭቶችን አላስፈላጊ መልክ እንዲይዙ ለማድረግ የሚሠሩ አካላት መኖራቸውን እና ግጭቶችን ሳይሰፉና ጉዳት ሳያደርሱ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል ህዝቦቹ በጋራ ሆነው ለአገሪቱ ለውጥ ጥረት ማድረጋቸውን እንዲያጠናክሩም ተማጽነዋል::

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የሚከሰቱ ችግሮች ዘር የፌዴራል ስርአቱን በአግባቡ አለመተግበርና ከሃገር አንድነትና ሉአላዊነት አንጻር የሚከወኑ ተግባራት ላይ ምንም አይነት ትኩረት ያለመስጠት ሁሉን አቀፍየሃገራዊ ግጭቶችን ማስከተሉን ምሁራን ይገልጻሉ።


ዐቢይ አህመድና ኢሳያስ አፈወርቂ በአ/አ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ የመሠረት ድንጋይ አኖሩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በተለምዶ ሐምሌ 19 መናፈሻ አካባቢ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ነው ከ20 ዓመት በኋላ የሃገራቱን እርቅና ሰላማዊ ግንኙነት ያደሱት ሁለቱ መሪዎች ናቸው የመሠረት ድንጋዩን በጋራ  ያኖሩት።

በሥነ ሥርዐቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኤምባሲ መገንቢያ ቦታው ለኤርትራ ህዝብና መንግሥት የተሰጠ ስጦታ መሆኑን አብስረው፤ የኤምባሲው መገንባት የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የበለጠ መሰረት የሚያስይዝ ነው ብለዋል።

በአሁኑ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት ወቅት ሀገራቱ በርካታ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው ተመልክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንንም ለመጠቀም ተወያይተናል ሲሉም ተደምጠዋል።

የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ከድህነት ለማስወጣት ያለ መታከት እንሰራለንም ሲሉም ማረጋገጫ የሰጡት ዶክተር ዐቢይ የፈረንጆቹ 2020 ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝቦች ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ የብልፅግና መጀመሪያ ዓመት ይሆናልም በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል::

“የአሁኑ የሁለት ቀናት ጉብኝቴ፣ የሁለት ወራት ቆይታን ያህል ነው የተሰማኝ” ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ ጉብኝቱ በበርካታ በድንገቴ አስደሳች ሁነቶች የተሞሉ ነው ደስታቸውን ከፈገግታ ባሻገር በንግግር አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ግልጽነት ይጎለዋል በማለት ቀጥተኛ ያልሆነ ተቃውሞ በማሰማት ላይ የምትገኘው ሕወሀት አሁንም መልዕክተኞችን ወደ ኤርትራ ለመላክ የጀመረችውን እንቅስቃሴ እንደቀጠለች ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሊተገበር የሚገባው የውጭ ግንኙነት በምን መስፈርት በአንድ ክልል ሊተገበር እንደሚችል ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን ግንኙነቱን በሚመለከት ከመንግስት በኩል እስከሁን የተገለፀ ምንም አይነት ነገር አለመኖሩ ግርታን ፈጥሯል።


ለ1ኛ ዓመት ዮኒቨርስቲ ተማሪዎች የታሪክ መማሪያ ሞጁል ላይ ግምገማ ተጀመረ

ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተዘጋጀው የአፍሪካ ቀንድና የኢትዮጵያ ታሪክ መማሪያ ሞጁል ላይ በአዲስ አበባ ግምገማ እየተካሄደ ነው ተባለ።

በግምገማ መድረኩ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የታሪክ መምህራን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፥ ባለፉት ዓመታት ተማሪዎች የሀገራቸውን ታሪክ መማር እንዳይችሉ እንደ አገር በታየው ዳተኝነት ምክንያት ትርክቶች የታሪክን ቦታ ይዘው አለመግባባቶችና ጥርጣሬዎች እንዲያድጉ እድል መፍጠሩን ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ታሪክ በአንድ ወቅት በተወሰነ ቦታ ስለተፈፀሙ ጉዳዮች የሚያትት መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ከእነዚህ ክስተቶች አስተማሪውን ታሪክ ነቅሶ በማውጣት፣ ዛሬን በአግባቡ መረዳትና ቀጣዩን ለመትለም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

በያዝነውና በጨበጥነው እውቀት ሌላ ቁስል መፍጠር ወይም ቁስሉን በመነካካት ሌላ ቁርሾ ማስነሳት ዘመኑ የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ድርጊት ነው ካሉ በኋላ

የትናንቱን ጉዳት በእርቅና በይቅርታ ተሻግሮ ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይገባል ሲሉ ካድሪያዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅራኔና ጥርጣሬ በቀላሉ የሚፈጥሩ ይዘቶች የሞጁሉ አካል አይሆንም ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ ለግምገማ የተዘጋጁ የታሪክ ምሁራን ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቦች አብሮነት አምድ የሆኑት እሴቶች ተገቢውን ክብር በሚሰጥ ደረጃና ቋንቋ መፃፋቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ምሁራኑ በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ተወያይተው ያመጧቸው አስተያየቶች ዙሪያ እስከ ነገ ድረስ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የፊታችን ቅዳሜ በጋራ የተስማሙበትን ሞጁል ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል::

LEAVE A REPLY