በቀን 600 ሺኅ ሊትር ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ
በአዲስ አበባ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ ፣ በቀን 600 ሺህ ሊትር ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በሆራይዘን ፕላንቴሽን ባለቤትነት የሚተዳደረው የሸገር የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ፣ በሚድሮክ ኢትዮጵያ አማካኝነት ቦሌ ክፍለ ከተማ ፣ የተባበሩት አደባባይ አካባቢ የሚገነባ መሆኑም ተረጋግጧል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በዘይት ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር መነሳቱ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ፤ አስተዳደሩ ለግንባታው አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ በማረጋገጥ ፣ ባለሀብቶች እንደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የፋብሪካው መገንባት ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውንየዘይት ምርት በ25 በመቶ እንዲቀንስ ያደርጋል ተብሎ ተገምቷል። በተጨማሪም ፋብሪካው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ መጠን እንደሚያቀርብ ተገልጿል።
ዛሬ በይፋ ግንባታው የተጀመረው የዘይት ፋብሪካ በአንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል።
ኢትዮጵያና ሳዑዲ የፈጸሙትን ስምምነት ተከትሎ 11 ሺኅ ሠራተኞች ተቀባይነት አገኙ
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በተፈራረሙት የሠራተኛ እና አሠሪዎች ስምምነት መሠረት ባለፉት ስምንት ወራት ከ11 ሺህ በላይ የቤት ሠራተኞችን ሰነድ ተቀብሎ ማስተናገዱን ገለጸ።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አብዱላዚዝ አህመድ ሰነዳቸው ከታየላቸው ሠራተኞች መካከል አብዛኛዎች ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው ፤ በሳዑዲ ያለውን የሠራተኛ ፍላጎት መሠረት በማድረግም ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ የሥራ እድል ለማመቻቸት ኤምባሲው ጅዳ ከሚገኘው ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በህጋዊ መንገድ ወደ ሪያድ እየገቡ ያሉ ሠራተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ስልጠና ያገኙ በመሆናቸው ከአሁን በፊት ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮችን በቀላሉ ማለፍ የሚችሉ ናቸው ተብሏል። አምባሳደር አብዱላዚዝ በህጋዊ መንገድ ሠራተኞችን ወደ ሪያድ ከማስገባት ጎን ለጎን ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሪያድ ባለስልጣናት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በአ/አ የእብድ ውሻ በሽታ ቢበራከትም ሰዎች መድኃኒት በሆስፒታሎች ማግኘት አልቻሉም
በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የእብድ ውሻ በሽታ እየተበራከተ ቢመጣም የበሽታው መከላከያ መድኃኒቶች በጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ አለመሆኑ ተገለፀ።
የእብድ ውሻ በሽታ ከታከሙት ሙሉ በሙሉ የሚድን ቢሆንም ከተላላፊ በሽታዎች በገዳይነቱ በግንባርይጠቀሳል። ቀደምትነት በሽታው 90 በመቶ ከውሻ እና 10 በመቶ የውሻ ዝርያ ካላቸው እንሰሳት እንደሚመጣም በዘርፉ ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ባለቤት የሌላቸው ውሻዎች በብዛት እየተሰተዋሉ ናቸው። በተለይ በከተማዋ ለመልሶ ማልማት በተለቀቁ ቦታዎች ላይ ባለቤት የሌላቸው ውሻዎች መበራከታቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች በመናገር ላይ ናቸው።
በሀገሪቱ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብቻ ይሰጥ የነበረው የእብድ ወሻ በሽታ ህክምና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እና በአዲስ አበባ 5 ክፍለ ከተሞች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፤ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ህዳሴ ጤና ጣቢያ እንዲሁም ንፋስ ስልክ ጤና ጣቢያ ወረዳ 12 ህክምና መስጫዎች የእብድ ወሻ በሽታ መድኃኒት ባለመኖሩ ህክምናውን ለመስጠት መቸገራቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቡድን አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ግርማ በአሁኑ ወቅት በበሽታው ተይዞ የሚመጣው ሰው እና የመድሀኒት አቅርቦቱ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የኢትዩጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ ከሚያቀረባቸው መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ የእብድ ውሻ መድኃኒት ከአንድ ዓመት በላይ አልተካተተም ነው ያለው። መድኃቱ ጤና ጣቢያዎቹ በሚልኩት የመድሃኒት ዝርዝር ውስጥ ቢያካትቱት ማቅረብ ይቻል እንደነበር የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ወይዘሮ አድና በርሄ ገልፀዋል።
40 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ኮኬይን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተያዘ
ኡራጓይ በታሪክ እጅግ ግዙፍ የኮይኬን ዱቄት መያዟን ዛሬ ይፋ አድርጋለች። የኮኬይን ዱቄቱ 6 ቶን ይመዝናል ፤ ይህም ለኮኬይን አስተላላፊዎች እጅግ መራሩ መርዶ መሆኑ እየተነገረ ነው።
የባሕር ትራንዚትና የጉምሩክ መኮንኖች እንደገለፁት ከሆነ ፣ ከ6 ቶን ኮኬይኑ ውስጥ 4 ቶን ኮኬይን የተያዘው በሞንቴቪዲዮ ወደብ ላይ ነው። የሶያ ዱቄት ማከማቻ ብልቃጦች ውስጥ ተደብቆ እንደነበረ የተነገረው ይህ ኮኬይን መዳረሻውን ያደረገው ቶጎ፣ ሎሜ እንደነበርም ተረጋግጧል።ቀሪው 1.5 ቶን ኮኬይን ደግሞ ወደቧ ላይ ተይዟል ተብሏል።
በድምሩ በቁጥጥር የተያዘው የኮኬይን መጠን አሁን ባለው ገበያ ቢሰላ በትንሹ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ወይም 1 ቢሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ያወጣል። ይህ ወደኢትዮጵያ ገንዘብ ቢመነዘር 40 ቢሊዮን ብር ይደርሳል።
ኡራጓይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁነኛ የአደገኛ እጽ መተላለፊያ እየሆነች ትገኛለች :: ወደ አውሮፓ፣ አፍሪካና ሰሜን አሜሪካ የሚላላኩ አደገኛ እጾች በኡራጓይ በኩል ለማሳለፍ ሲሞከር ይህ የመጀመርያው አይደለም። ከአንድ ወር በፊት 3 ቶን ኮንቴይነር ኮኬን በሞንቴቪዶ ወደብ አድርጎ ወደ ቤኒን ሊሻገር ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።
4́.4 ቶን የሚመዝነው ኮኬይን ሊያዝ ምክንያት የሆነው የኤክስሬይ ፍተሻ ማሽኑ ምንነቱ የማይታወቅ ነገር በማሳየቱ በተፈጠረ ጥርጣሬ መሆኑም ታውቋል። በዋናነት ጥርጣሬው ሊፈጠር የቻለው ግን ኩባንያው ከዚህ ቀደም የሶያ ፍሬ ዱቄትን ወደ አፍሪካ ልኮ አለማወቁ ነው።
እያንዳንዱ የኮኬይን ግግር ጡብ 1.1 ኪሎ ግራም እንደሚመዝንንና ተመሳሳይ 3000 የኮኬይን ጡብ መያዙን የተናገሩት የባሕር ኃይል ተጠሪው ዲኣጎ ፔሮና ናቸው። የኮኬይን ጡቦቹ ሊጫኑ የነበረው ንብረትንቷ የጣሊያን በሆነች መርከብ ነበር። ኮኬይኑ መነሻው ከየት እንደሆነ እስካሁንም ያልተደረሰበት ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ግን በአንድ በደቡብ ምዕራብ ሶሪያኖ ከተማ በሚገኝ የእንሰሳት ጋጣ ውስጥ እየወጣ ሲጫን እንደነበር የሚጠቁም መረጃ ተገኝቷል።ፖሊስ ይህን የቀንድ ከብቶች ጋጣ በከበበበት ወቅትም ተጨማሪ ኮኬይን ማግኘቱን ገልጿል።
በሞቃዲሾ 90 ሰዎች በአጥፍቶ ጠፊ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሞቱ
ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 18 ቀን ከሰዐታት በፊት በደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ጥቃት በትንሹ 76 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ዛሬ ጠዋት በርካታ ሰዎች ወደ ሥራ በሚሄዱበት ሰዓት ደረሰ በተባለው በዚህ የቦምብ ጥቃት ከሟቾች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
ይህ አደጋ የደረሰበት የሞቃዲሾ ክፍል ፍተሻ የሚደረግበትና በርካታ ሰዎች የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመዘገብ ላይ ናቸው።
የፖሊስ መኮንኑ ኢብራሂም ሞሐመድ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ፍንዳታው እጅግ አደገኛ ነበር ሲሉ፤የመዲና ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶ/ር ሞሐመድ የሱፍ ደግሞ ለአሶሽየትድ ፕረስ 73 አስክሬኖች መቀበላቸውን ተናግረዋል።
ሳካሪ አብዱልቃድር የተባለ የአይንም ምስክር በበኩሉ “ማየት የቻልኩት እዛም እዚም የተበጣጠሰ የሰው አካል ነው፤ የአንዳንዱ ሰው ሬሳ በእሳት በመቃጠሉ መለየትም አይቻልም ነበር” ብሏል።
እስካሁን ድረስ ለጥቃቱ ሓላፊነት የወሰደ አካል የለም። ዘግይተው እየወጡ ባሉ መረጃዎች ደግሞ የሟቾች ቁጥር ከተገለጸውም እጥፍ ሊደርስ እንደሚችል እየጠቆሙ ናቸው። መሐመድ አብዱራዛቅ ተባሉ የምክር ቤት አባል የሟቾቹ ቁጥር 90 እንደደረሰ ዘግየት ብለው አስታውቀዋል።