|| የቀድሞ የፓርላማ አባል ||
ባለፈው ማክሰኞ እለት ቀትር ላይ ተንቀሳቃሽ ስልኬ የመልእክት ጥሪ ድምፅ አሰማ፡፡ የተለመደው የቴሌ ማስታወቂያ መስሎኝ አልተውኩትም፡፡ ሳየው ከአንድ የቀድሞ የኢዴፓ ከፍተኛ አመራር አባል የተላከ ነው፡፡ “ደስ ብሎናል፣ ኢዴፓ አሸነፈ” ይላል መልእክቱ፡፡ ስልክ ደውዬ ምላሽ ሰጠሁ፡፡
ከቀናት በኋላ ደግሞ ሄኖክ ለይኩን የተባለ የኢዜማ አባል፣ የፌስቡክ ወዳጄ፣ ለእኔና ለሙሼ ሰሙ የሽምግልና መልእክት ላከልን፡፡ ይኸው ወዳጄ “አሁን ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ያለ ስጋት ፖለቲካ የሚሰራበት ጊዜ አግኝታለች። ምናልባት ይህ እድል ዳግም የማናገኘው ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም አግኝተነው የማናውቀው ነው… እናም ይህ ጊዜ እንዳያመልጠን ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል… በዚህ ነገር እናንተ ዝም ስትሉ ማየት አልሻምና ይህ ጊዜ እንዳይበላሽ ያለ መድሎ፣ አንተም ተው አንተም ተው እንድትሉ…” ይላል፡፡ ምን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባኝ ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡
ወረድ ይልና “የቀድሞ ፓርቲያችሁ ኢዴፓ በጥረቱ ከምርጫ ቦርድ የሚያስደስት ውሳኔ አግኝቷል። ቦርዱም ኢዴፓውያን በሄዱበት ሁሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ደብዳቤ ሰጥቶ ሸኝቷቸዋል…” እያለ ይቀጥላል፡፡ አሁን ነገሩ እየገባኝ መጣ፡፡ አሁንም ትንሽ ወረድ ሲል “ቢሮን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ ለፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዞላቸዋል። ሆኖም… ለምንድን ነው [ኢዜማ የወሰደባቸውን] ቢሮ ይመለስልን የሚሉት?” በማለት ይጠይቅና “እስቲ ሳታዳሉ፣ ስለ ሀገር ብላችሁ ተናገሩ” ብሎ “ፍርድ እንድንሰጥ” ይጋብዘናል፡፡
ሙሼ ሰሙ እዚያው ፌስ ቡክ ላይ መልስ ሰጥቷል፡፡ ሙሼ ከሰጠው መልስ ውስጥ ልቤን የማረከቺው “የኔ የምትለው ነገር ሁሉ ያንተ መሆኑን በሕግ አግባብ እስካላረጋገጥክ ድረስ ያንተ ያልሆነ ሁሉ የሌላው መሆኑን ማወቅ ለሁሉም ይበጃል” የምትለዋ ናት። የፌስቡክ ወዳጄን ሄኖክ ለይኩንን ይህቺ መልስ አላረካቺው ይሆን?
እኔ ግን ጉዳዩን ወደ ጋዜጣ በማምጣት እንድንወያይበት ፈለግኩ፡፡ በጉዳዩ ላይ ትንሽ አሰብኩበት፡፡ እናም ይህቺን ማስታወሻ ለመክተብ ተነሳሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ኢዴፓ ውስጥ መከፋፈልና ሽኩቻ ነበር፡፡ ነገሩ እልባት ሳያገኝ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ተለዋወጠና “ኢዜማ” የተባለ ፓርቲ የምስረታ ሂደት ጀመረ፡፡ ጥሩ አጋጣሚ የተፈጠረላቸውና በወቅቱ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ጫኔ ከበደ “ኢዴፓን አክስሜያለሁ፣ ከኢዜማ ጋር ተቀላቅያለሁ” ብለው አወጁ፡፡ የኢዴፓን ሀብትና ንብረት ይዘው ወደ ኢዜማ ገቡ፡፡ የኢዴፓን ቢሮዎች ለኢዜማ አስረከቡ… ኢዴፓ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ይበልጥ ተወሳሰበ፡፡ “የለም! ኢዴፓ አልከሰመም” የሚሉ የኢዴፓ አባላት አቤቱታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቀረቡ፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ሲከራከሩ ቆዩ፡፡ ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ “ኢዴፓ አልከሰመም” ተባለ፡፡ ይህንን ውሳኔ ያገኙት ኢዴፓዎች፤ “ከ20 ዓመታት በላይ ስንጠቀምበት የነበረውን ቢሮ ኢዜማ ይመልስልን” ብለው ደብዳቤ ጻፉ – ለኢዜማ፡፡
የፌስቡክ ወዳጄ ሄኖክ እንግዲህ በዚህ ላይ አስተያየት እንድንሰጥ ነው ለእኔና ለሙሼ ጥሪ ያደረገልን፡፡ የወዳጄ ፍላጎት “ኢዜማ በያዘው ይርጋ፡፡ ኢዴፓ ሌላ ቢሮ ይፈልግ” የሚል ነው:: ጥሪ ያደረገልን እኔና ሙሼ፤ ይህንን ፍላጎቱን “እንድናጸድቅለት” ስለፈለገ ነው እንጂ ሎጂኩ ጠፍቶት አይመስለኝም፡፡
እኔ በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ “ፍርድ መስጠት” አልፈለግኩም፡፡ ይልቁንም ለወዳጄ ጥያቄ ማቅረብን መረጥኩ፡፡ “ወዳጄ ሄኖክ ለይኩን ሆይ! አያድርግብህና አንተና ባለቤትህ በአንድ ቀበሌ የመንግስት ቤት ተከራይታችሁ ስትኖሩ… ስትኖሩ… ተጣላችሁ:: ትዕግስት የለሽ የሆነቺው ባለቤትህ፤ አንተን በፖሊስ አስወጣችህና ያንን ፖሊስ አግብታ በቤትህ መኖር ጀመረች፡፡ አንተም “የጋብቻ ውላችንን ሳንቀድ፣ ባለቤቴ እኔና ልጆቼን ከቤት አስወጣቺን፣ ሌላ ሰው አገባች፣ ትዳሩም አልፈረሰም፣ ከቤትም ልንወጣ አይገባም…” ብለህ ለፍርድ ቤት አመለከትክና ስትከራከር ቆየህ፡፡ ፍ/ቤቱ ትዳሩ እንዳልፈረሰ ወሰነ፡፡ ከዚያ በኋላ ምንድነው የምታደርገው? በዚህ የቤት እጥረት ባለበት ዘመን ልጆችህን ይዘህ ወደ ቤትህ መመለስ ነው የምትፈልገው ወይስ አንዴ ወጥቻለሁ ብለህ፣ አልጋህንም ሚስትህንም ለቀማህ ሰው ቤቱን ትመርቅለታለህ?
የቢሮውን ጉዳይ ትተን ይልቅ ወደ ፓርቲዎቹ ጉዳይ እንለፍ፡፡ የኢዴፓ እና የኢዜማ ነገር ከቢሮ “መልስ – አልመልስም” አታካሮ ላቅ ያለ መስሎ ይታየኛል፡፡ በኔ ግምት፤ የችግሩ ምንጭ ሁለቱን ፓርቲዎች ከሚመሩ ሁለት ግለሰቦች (ማለትም ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከልደቱ አያሌው) ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለቱ ፖለቲከኞች ያላቸውን የግል “እልህ፣ ቂምና ቁርሾ” ወደ ፓርቲዎቹ ጎትተው በመውሰድ የፓርቲዎቹን አባላትና ደጋፊዎች በማያውቁትና በማያገባቸው ጉዳይ እንዲነታረኩ ለማድረግ የሚሄዱበት መንገድ አሳሳቢ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት መተባበር ሲገባቸው ዶሴ ይዘው በየፍርድ ቤቱ ላይ ታች የሚሉ ከሆነ ለሀገርም ለህዝብም ኪሳራ ነው፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ ወቅት ወዳጆችና የትግል አጋሮች ነበሩ፡፡ በትግሉ ሂደት የሃሳብ ልዩነት ተፈጠረና ተለያዩ:: ይሄ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት ሊገርም የሚችለው ልዩነት ባይፈጠር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያኔም ቢሆን ልዩነቱ የተፈጠረው በግቡ ሳይሆን ወደ ግቡ በሚደረግ ሂደትና በስልቱ ላይ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ከ15 ዓመታት በፊት የሆነ ነገር ነው፡፡ ያኔም ቢሆን ሁለቱ ፖለቲከኞች የሃሳብ ግጭት የፈጠሩት የጋራ ሀገር ስላላቸው እንጂ በግል ጉዳያቸው በተፈጠረ ፀብ አልነበረም፡፡ ያኔ በነበራቸው በእልህ የተሞላበት መገፋፋት የፓርቲያቸውን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላውን ህዝብ አስቀይመዋል፣ አስከፍተዋል፡፡ በወቅቱ በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ድል እልህ ውስጥ ገብተው በፈጠሩት ገመድ ጉተታ መና አስቀርተውታል፡፡
እነዚህ ፖለቲከኞች የዛሬ 15 ዓመት የሰሩት ስህተት አልበቃቸው ብሎ ዛሬም የንትርክ ነጋሪት መጎሰማቸው አንዳች የተጠናወታቸው ጋኔን ቢኖር ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” እንዲሉ በእልህና በፉክክር ወደ ሌላ የጭቅጭቅ አዙሪት ውስጥ ለመግባት ሰበብ መፈለግ አንድም ህዝብን መናቅ አሊያም ካለፈ ስህተት አለመማር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይመስለኝም፡፡
“በፖለቲካ ዘላለማዊ ወዳጅም ሆነ ዘላለማዊ ጠላት የለም” የምትለዋን እድሜ ጠገብ አባባል የማያውቃት ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር ተለውጧል፡፡ ከስህተታቸው ተምረው፣ ለህዝብና ለሀገር ሲሉ ይቅር ተባብለው፣ እንደገና አብረው በመስራት በምርጫ 97 ያስከፉትንና ያስቀየሙትን ህዝብ ሊክሱት ይገባል፡፡ ስለሆነም፤ የሁለቱም ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ዶ/ር ብርሃኑንና አቶ ልደቱን እንዲሁም የየፓርቲዎቹን ከፍተኛ አመራር አባላት ግፊት ሊያደርጉባቸውና “በቃችሁ፣ ተደራደሩና አብረን የምንሰራበትን መንገድ ፍጠሩ” ሊሏቸው ይገባል፡፡
መጪው ጊዜ የምርጫ ወቅት ነው:: ፓርቲዎች ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በገዢው ፓርቲ በኩል “ዘጠና ዘጠኝ በመቶ አሸነፍኩ” የሚባልበት ዘመን አልፏል፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩልም ቢሆን እንደ ቀደሙት ዓመታት ኢህአዴግ ያደሰውን ግፍና መከራ በመናገር፣ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የሚቻል አይሆንም፡፡ ብዙ የለፋ ብዙ ያገኛል:: ያንቀላፋም ለዘለዓለም ያሸልባል፡፡ እናም በዋዛ ፈዛዛ የሚያልፍ ደቂቃም ሆነ የሴኮንዶች ቅንስናሽ ሊኖር አይገባም፡፡
ሀገሪቱ ወፈ-ሰማይ የፖለቲካ ፓርቲ የምትሸከምበት አቅም የላትም፡፡ ሀገሪቱ አሁን ያላት ተፈጥሮ የቸረቻት የቋንቋ፣ የብሄር፣ የሃይማኖት፣… “ብዝሃነት” አልበቃት ብሎ ከመቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ መፈልፈል ከድጡ ወደ ማጡ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ያለው ሆኖ አይታየኝም፡፡ ኢዴፓ እና ኢዜማ መሰረታዊ የሆነና የሰፋ የርእዮተ-ዓለም ልዩነት የላቸውም:: እናም ዶ/ር ብርሃኑ እና አቶ ልደቱ ማላገጡን ትተው፣ ሁለቱን ፓርቲዎች አዋህደው፣ ጠንካራ አማራጭ ሆነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወንድሜ ሙሼ ሰሙ እንዳለው፤ ኢዴፓም ሆነ ኢዜማ ውዝግቡን በዚሁ ከቀጠሉ የሚፈጠረው የጊዜና የሃብት ብክነት ብቻ ሳይሆን በድርጊታቸው ልክ በሕዝብ ፊት መቅለል ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው፡፡
ለቀድሞ የትግል አጋሮቼ ኢዴፓውያን አንድ መልእክት አለኝ፡፡ ደስታችሁን መግለጻችሁ ችግር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ እሰጣ አገባ ውስጥ አትግቡ፡፡ ለመርህ ተገዢ ሁኑ፡፡ ትልቁን ስዕል ተመልከቱ፡፡ ቂም በቀልን አስወግዱ፡፡ ወደ ውስጣችሁም ተመልከቱ፡፡ ለሃገርና ለሕዝባችን ክብርና ልዕልና ትኩረት ስጡ፡፡ ኢዜማ ውስጥ ላላችሁ ወዳጆቼም ይኸው መልእክቴ ይድረሳችሁ!
ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ስለ ምርጫ አንድ ነገር ከትቤ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ በመጪው ግንቦት ወር ምርጫ ይካሄዳል እየተባለ ነው፡፡ በኔ ግምት ግን በዚህ ዓመት ምርጫ የሚካሄድ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከምርጫው በፊት መከናወን ከሚገባቸው ተግባራት ውስጥ በአዲሱ የምርጫ እና የፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የገለልተኛ አስመራጮች ምልመላና ስልጠና መካሄድ አለበት፡፡ የምርጫ ቁሳቁሶች ግዢና ህትመት መጠናቀቅና መሰራጨት አለበት፡፡ እነዚህ ተግባራት ስለመከናወናቸው በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ከግንቦት በፊት ባሉት ወራት እነዚህን ተግባራት ማጠናቀቅ ከተቻለ እሰየው ነው፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡
ሌላው ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ ነው:: የምርጫውን ዘመን ማራዘም ሳያስፈልግ፣ እስከ ነሀሴ ወር 2012 ዓ.ም ድረስ ማካሄድ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከግንቦት ወር ውጪ ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑ ይታየኛል:: ምክንያቱም ከግንቦት ወር በኋላ ያሉት ሦስት ወራት አንድም ዝናብ ይበዛባቸዋል፤ አሊያም ለአርሶ አደሩ (በተለይ በደጋ አካባቢ) የእርሻ ወቅቶች ናቸው፡፡ በእርሻ ወቅት አርሶ አደሩ በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም፡፡ ብዙሃኑ አርሶ አደር ያልተሳተፈበት ምርጫ ደግሞ የተሟላና ጤናማ ምርጫ ሊሆን አይችልም፡፡ እናም ምርጫው ካልተካሄደ ምን ይደረግ? የምርጫው ጊዜ ይራዘም? ከተራዘመ እንዴት ይራዘም? ማን ያራዝመው? ከተራዘመ እስከ ምርጫው ባለው የሽግግር ጊዜ፣ ሀገር እንዴት ይተዳደር? የሚሉት ጥያቄዎች ከወዲሁ በፖለቲከኞች በዝርዝር ሊጤኑ ይገባል፡፡
ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡