የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 20 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 20 ቀን 2011 ዓ.ም

በሕዝብ ላይ ወንጀል የሠራን አባል አላደርግም ያለት መራራ ጉዲና፣ ጃዋር መሐመድን ወደ ፓርቲያቸው ቀላቀሉ

የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ)  ተቀላቅሏል::

በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሳምንታት በፊት በግፍ ለተገደሉት 90 የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች ግድያ በህግ እንዲጠየቅ የሚሹት ጃዋር መሐመድ ኦፌኮን መቀላቀሉን የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ቀደም ሲል ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው፣ ይልቁንም ከዳር ሆኖ በአገሪቱ ለተጀመረው ለውጥ ድጋፍ ማድረግን እንደሚመርጥ ተናግሮ የነበረው ጃዋር፤ በቅርቡ የሐሳብ ለውጥ ማድረጉን እና ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት መወሰኑን መናገሩ አይዘነጋም:: ጃዋር ፖለቲካውን ለመቀላቀል ቢወስንም ተሳትፎው በየትኛው ፓርቲ እንደሚሆን አለመወሰኑንም በወቅቱ ገልፆ ነበር።

ጃዋር ፓርቲያቸውን እንደተቀላቀለ ከቢሯቸው መረጃ የተሰጣቸው ትናንት እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “ኦፌኮ እገባለሁ ብሎ ለቢሯችን ነግሯል” ሲሉ ለቢቢሲ አስታውቀዋል። ከሦስት ወይም ከአራት ቀናት በፊት ፕሮፌሰር መረራ ባሉበት ጃዋር  መጥቶ የፓርቲያቸውን ጽሕፈት ቤት መጎብኘቱንም መስክረዋል።

ጃዋር መሐመድ ወደ ኦፌኮ ለመቀላቀል ከመወሰኑ ቀደም ብሎ ከአመራሩ ጋር ያደረገው ንግግር እንደነበረ የተጠየቁት ፕ/ር መራራ “አባላት ስንመለምል ንግግር የለም፤ እሱ ራሱም እኮ እዚህ ገብቻለው ሊል ይችላል። እኛም ስብሰባ ላይ እኛን ተቀላቅሏል ብለን ልንናገር እንችላለን” የሚል ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የጃዋርን አባል የመሆን ጥያቄ ተቀብሎት እንደሆነ የተጠየቁት ፕሮፌሰር መራራ”ማንም ኢትዮጵያዊ የእኛ አባል ሊሆን ይችላል፣ የምንከለክልበት የተለየ መንገድ የለንም። ወንጀል የሠራ ወይም በሕዝብ ላይ ወንጀል የሠራ እስካልሆነ ድረስ” በማለት መልሰዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ያላቸው ፕሮፌሰር መራራ በሕዝብ ላይ ወንጀል ያልሠራን ሰው አባል አናደርግም እያሉ በሌላ ጎኑ ለበርካታ ንጹሃን ዜጎች እልቂት መንስዔ የሆነውን ጃዋር መሐመድን መቀበላቸው ብዙዎችን አስገርሟል::

ጃዋር መሐመድ በሥልጣን ላይ ያሉ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች በሚያደርጉለት ከለላና በውስጥ ስምምነት በሰጡት ዋስትና በቁጥጥር ስር ውሎ ጥፋተኛ በሚል አይፈረድበት እንጂ በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ በተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች ከሳምንታት በፊት ለተገደሉት ሰዎች ሕይወት የመጀመሪያው ተጠያቂ መሆኑ ይነገራል።

ጃዋር መሐመድ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩ ጥበቃዎች “እኔ ሳላውቅ ለማንሳት ሙከራ ተደርጓል” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልዕክት ካሰፈረ በኋላ የተፈጠረውን ውዝግብና አለመረጋጋትን ተከትሎ ነበር ለምርጫ እንደሚወዳደር ፍንጭ የሰጠው።

ወደ ፖለቲካው ለመግባት መወሰኑን ተከትሎ የአሜሪካ ዜግነቱን መሰረዝ የሚያስችለውን ሂደት በቶሎ እንደሚጀምር ጃዋር በተደጋጋሚ በተለያዩ ቃለ ምልልሶቹ ጠቅሶ እንደነበር የሚታወስም ነው።

አንዳንድ የዜና ምንጮች ጃዋር ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲን ማነጋገሩንም ጭምር ይናገራሉ:: በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ሊቀመንበርነት የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በፕሮፌሰሩ ይመራ በነበረው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስና (ኦብኮ) በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ በነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ውህደት የተመሰረተ ፓርቲ ነው።


በምሥራቅ ሐረርጌ ቤተክርስቲያንና መስጂድ እያስገነቡ ያሉት ካህን አነጋጋሪ ሆነዋል

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ ስፍራዎች ሃይማኖታዊ ግጭት ያለ ለማስመሰል መስጂድ እና አብያተ ክርስቲያናቴ ቢቃጠሉም ሀቁ ግን ከዚህ ፈጽሞ የራቀ ነው ። መላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም፣ በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስትያንና የቢላል መስጂድን እያሠሩ የሚገኙና በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ መከባበር እንዳለ ማሳያ የሆኑ ሰው ሆነው ተገኝተዋል።

የአገልግሎት ስፍራቸው በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰንዳፋ በኬ ማርያም መሆኑን የሚናገሩት እኚህ ካህን በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኝ መስጂድንና ቤተ ክርስቲያንን በእኩል ቆመው እያሳነጹ ናቸው።

የሚያገኛቸውን ሙስሊምና ክርስቲያን በእኩል ለቤተ እምነቶቹ ማሰሪያ ሲጠይቁ ግር የሚል ቢሆንም እርሳቸው ግን ታሪክ አጣቅሰው ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት አመሳክረው ሓላፊነታቸው የሁሉም ምዕመናን፤ በሙስሊሙም በክርስቲያኑም ወገን፤ መሆን እንዳለበት እያስተማሩ ይገኛሉ::

ከምሥራቅ ሐረርጌ መምጣታቸውን የሚሰማ የመጀመሪያ ጥያቄው በአካባቢው የሚገኙ ክርስትያኖችና አብያተ ክርስትያናት ሁኔታን ቢሆንም ፣ እርሳቸው ደግሞ የላንጌ አካባቢ ሕዝብን ፍቅር ተናግረው አይጠግቡም።

በ2007 ዓ.ም ሐረር የቁልቢ ገብርዔል ገዳምን ለመሳለም በሄዱበት ወቅት ከቁልቢ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስትያንን መመልከታቸውን የሚያስታውሱት ካህን ፤ በአካባቢው ያሉ ክርስትያኖች ኑሯቸው ከእጅ ወዳፍ መሆኑንና አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ የዓመት ቀለባቸውን በዓመት አንዴ የሚጥለውን ዝናብ ጠብቀው እንደሚያመርቱ መረዳታቸውንም ይናገራሉ።

የአካባቢው ክርስትያኖች የሚያመልኩበት ቤተ ክርስትያን ደግሞ እርጅና ተጭኖት እየፈረሰ በመሆኑ እዚያው ቆይተው ለማሠራት ይወስናሉ። በዚያ ቆይታቸው በከተማዋ ውስጥ የሚገኘውን ላንጌ ቢላል መስጂድ ተመለከቱ፤ የቤተ ክርስቲያኑም ሆነ የመስጂዱ መልክ የአካባቢው ማኅበረሰብን ይመስላል። የገንዘብ አቅም በሌለበት አካበባቢ ቤተ እምነቶችም ድሃ ናቸው፣ ሲፈርሱ የሚያስጠግን ቢያዘሙ የሚያቀና ይቸግራል።

አባ አክሊለ ማርያም የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተክርስትያንን አዲስ አበባና አካባቢዋ ከሚገኙ ክርስትያን ወገኖች ገንዘብ በመጠየቅ እያሠሩ ግንባታውም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ በመሄዱ ፤ አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ በ500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የቤተ ክርስትያን ሕንጻ እንዲሁም በቅጽር ግቢው ውስጥ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች መሠራታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ይህንን እያሰሩ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የቢላል መስጂድ በሚገባ አልታነጸም፤ እድሳት ይፈልጋል፤ በአካባቢው ያሉ ሙስሊም ወገኖች ኑሮ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። ክርስትያኖችና ሙስሊሞች በአካባቢው በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ነው የሚኖሩት። ሁለቱም ሰማይ ቀና ብለው አይተው፣ መሬት የሰጠቻቸውን ለቅመው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ናቸውና አባ አክሊለ ማርያም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትሹትን፣ እናንተም አድርጉላቸው የሚለውን መንፈሳዊ ቃል በመከተል እርሳቸውም መስጂዱን ለማሠራት እንደወሰኑ ይናገራሉይናገራሉ።

የቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን በእምነበረድ ታንጾ ፣ ከጎኑ የቢላል መስጂድ በእድሳት እጦት አዝሞ ማየት አልሻም ያሉት ከሰሜን ሸዋ ለቁልቢ ገብርኤል ንግስ ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ተጉዘው ተአምር ለመሥራት የታደሉት ካህን ፤በእምነት ክርስትያን ቢሆኑም ከክርስትና አስተምህሮ መካከል አንዱ የሆነው የሰው ልጅን በሙሉ በእኩል ማገልገል በመሆኑ መስጂዱንም ለማሠራት መወሰናቸው ይገልጻሉ።

በዚህም የተነሳ ለእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማመልከቻ በመጻፍ ለሙስሊም ወንድሞችም መስጂድ ለማሠራት እንደሚፈልጉ ጠየቁ። የእስልምና ጉዳዮችም እንዲህ አይነቱ ተግባር በኢትዮጵያ ውስጥ እስልምና በገባ ወቅት የነበረ መሆኑን በማስታወስና በማድነቅ ፣ የድጋፍ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች እንደጻፉላቸው ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች በበኩሉ፤ በአዲስ አበባ ለሚገኙ መስጂዶች በአጠቃላይ የድጋፍ ደብዳቤ ከጻፈላቸው በኋላ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን በቃለመጠይቃቸው ላይ አብራርተዋል።አባ አክሊለ እንደሚሉት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአዲስ አበባ የሙስሊም ማኅበረሰብ በተሰበሰበ ገንዘብ በላንጌ የሚገኘው መስጂድን መሠረት የማስገንባት ሥራ ተከናውኗል።

ይህንን ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩት መስከረም 2011 ዓ.ም ላይ ሲሆን ደብዳቤ ተጽፎላቸው ወደ ሥራ የገቡት ደግሞ ጥቅምት 2/2011 ዓ.ም መሆኑን ያስታውሳሉ። እርዳታ የማሰባሰብ ሥራውን የጀመሩት ፒያሳ ከሚገኘው ኑር መስጂድ መሆኑን የጠቆሙት አባ አክሊለ፤ የመስጂዱ የበላይ ጠባቂና አስተዳዳሪ ኡስታዝ መንሱር ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ገልፀዋል።

አባ አክሊለ በላንጌ የሚገኘውን መስጂድ ሢያሠሩም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ሲያስገነቡ በእኩል ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀው ቤተ ክርስቲያኑ ፎቅ ስለሆነ መስጂዱም ፎቅ መሆን አለበት በሚል ሐሳብ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

መስጂዱ የምድር ቤት ግንባታው ተሠርቶ መጠናቀቁንና የላይኛውን ክፍል ግንባታ ለማስጀመር ገንዘብ አጥሮ በድጋሚ የእርዳታ ድጋፍ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ከሚገኙ የሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ገንዘብ እያሰባስቡ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

እርሳቸው ክርስቲያን ሆነው መስጂዱን ለማስገንባት በእምነት ገንዘባቸውን የሚሰጡ ሙስሊሞች መኖራቸው የሚያሳየው ምን እንደሆነ አባ አክሊለ ሲናገሩ፣ ዛሬም በሕዝቦች መካከል ያለ መተሳሰብና አብሮ የመኖር ባህል ጠንካራ መሆኑን ነው ይላሉ። ለሰሚም ሆነ ለተመልካች የእርሳቸው ድርጊት ኢትዮጵያና እስልምና ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያሳይ በመግለጽ፣ ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የተደረገላቸው መልካም አቀባበል ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ትምህርት እንደሚሰጥ ያስረዳሉ።

በሃይማኖትም መጻሕፍት ያለው መንፈሳዊ ቃል ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ በመኖር የገነባነው መዋደድና አብሮ የመኖር ባህል ለዚህ ተግባር ጠንካራ አጋዥ እንደሆናቸው አስታውሰው ፤ በድርጊታቸው የሚያገኟቸው ሰዎች ደስተኛ መሆናቸውን በማንሳት እርሳቸውም በሙስሊም ወንድሞቻቸው ተግባር ልባቸው መነካቱን ይገልጻሉ።

“ሰው ሊደሰት የሚችለው ሰውን ሲያገለግል ነው” በማለት በመስጂድ የሚያደርጉትም አገልግሎት ደስታን እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ። “ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ብሆንም ለአንድ ሃይማኖት ብቻ ብቆም እግዚአብሔርን ራሱ ያሳፍረዋል” በማለት ሁሉን በእኩል ማገልገል ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ስለመላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም ሲናገሩ “በካህኑ ጥያቄ መሰረት የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈንላቸዋል። እስካሁንም ከመቶ ሺህ ብር በላይ ለመስጂዱ ግንባታ ተሰብስቧል” ሲሉ መስክረዋል። የእርሳቸውንም ተግባር በተመለከተም “ይህ በጎ ድርጊት የሚያሳየን ሁሌም ሕዝቡ አንድ መሆኑንና ሳይለያይ ለመደጋገፍና ለመረዳዳት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ነው” ብለዋል።

በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን ባለሁለት ፎቅ ሕንፃው ማለቁን፣ ቤተክርስቲያኑም ጉልላቱ ላይ መድረሱን አጥሩም መሠራቱን እና መስጂዱም አልቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጠንክረው እየሠሩ መሆናቸውን ታላቁ ካህን ገልጸዋል።

ምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ እና በኩርፋ ጨለኬ ወረዳዎች የነበሩ ግጭቶችንና ስጋቶችን በማንሳትም በላንጌ ህዝበ ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ጎን በመቆም ፣ አብሮ የመኖር ባህሉንና ትስስሩን ጠብቆ ይህንን ወቅት ማለፉን ካህኑ በተያያዥነት መስክረዋል::


ለምርጫ ቅስቀሳ ፓርቲዎች መገነኛ ብዙኃንን የሚጠቀሙበት የቴክኖሎጂ የአየር ሰዐት ድልድል ተዘጋጀ

በቀጣዮ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን እና ዓላማቸውን በመገናኛ ብዙኃን ለህዝቡ እንዲያስተዋውቁ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአየር ሰዓት ድልድል ለማውጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን የአየር ሰዓት ስርጭታቸውና ከህትመት ገፃቸው ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ያውላሉ። በተያዘው ዓመት ለሚደረገው ጠቅላላ ምርጫም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከሰው ንክኪ በጸዳ መልኩ በሶፍትዌር የታገዘ የአየር ሰዓት ድልድል ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ተናግሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደገለጹት የአየር ሰዓት ድልድሉን ለማድረግ የምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የሚያቀርበውን ቀመር እየጠበቀ ነው። ቀመሩ በየምርጫ ዘመኑ የሚቀያየርና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ንግግር የምርጫ ቦርድ ከስምምነት የተደረሰበትን የአየር ሰዓት ድልድል ቀመር ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ያሳውቃል። በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ የተሰጠውን ቀመር ወደ ተዘጋጀው ሶፍትዌር በማስገባት የአየር ሰዓት ድልድሉን የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

በቅድመ ዝግጅቱ ላይም ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያነሱት ዋና ዳሬክተሩ፤ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ የባለሙያዎች ቡድን ኮሚቴ መዋቀሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም በምርጫ ዘገባ ላይ ለጋዜጠኞችና ለመገናኛ ብዙኃን የሥራ ሓላፊዎች የተለያየ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ሆኖም አሁንም መገናኛ ብዙኃን በአሠራሮቻቸው ስነ ምግባርን ጠብቀው በመሥራት የተለየ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ተብሏል በዳይሬክተሩ ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች በክፍያ ምክንያት ያጡትን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስቀጠል ገንዘብ ሚኒስቴር ፍቃደኛ ሆነ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከክፍያ ጋር በተያያዘ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየፈታሁ ነው አለ።

ተገንብተው ወደ ሥራ ከገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በቀር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፈተና እንደሆነባቸው ይነገራል።ባለሀብቶችም በተደጋጋሚ የሚያነሱት ቀዳሚው ችግር የሃይል አቅርቦት ሆኗል።

የኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ ያለውን መሠረተ ልማት ማሟላት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ግዴታ መሆኑ ይታወቃል። ኮርፖሬሽኑ መፈጸም የሚገባውን ክፍያ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመፈጸሙ ግንበኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል አቅርቦት ችግር በስፋት ተከስቷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሊሴ ነሚ የኃይል እጥረት ዋነኛው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ችግር መሆኑን ጠቁመው ፤ አሁን ላይ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች መፍትሄ እያገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኤሌክትሪክ ኃይል በክፍያ የሚቀርቡ አማራጮች ዘላቂ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ መንግሥት ቋሚ የኃይል አማራጭ ለመፍጠር እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከቻይና መንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረሙንም አስረድተዋል። በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የራሳቸው የኃይል አማራጭ እንዲኖራቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለሙከራ የሚሆኑ ፓርኮች ተመርጠው ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህም የፀሐይ፣ የንፋስ እና የእንፋሎት አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነናበፀሐይ ኃይል አማራጭ ላይ የግሉ ዘርፍ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ተስተውሏል ያሉት ሓላፊዋ ፤ በጥናቱ ውጤት መሠረት ሥራውን ወደ ተግባር መቀየር ይቻል ዘንድ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የአዋጭነት ጥናቶች ከወዲሁ እየተሠራባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።


አማራ ክልል ኩረጃን ለማስቀረት እየሠራሁ ነው አለ

አማራ ክልል ኩረጃን ለማስቀረት መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆችን አጣምሬ እየሠራሁ ነው አለ

ኩረጃን ለማስቀረት የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር፣ የተማሪ ወላጆች ማኅበርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ገለፁ።

የአማራ ክልል መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት እናውጋው ደርሰህ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ላለው ኩረጃ ፈጣንና ዘላቂ መፍትሔ ካልተፈለገለት ኢትዮጵያን ለውድቀት ያጋልጣል ካሉ በኋላ አገሪቱ ብቁ የሰው ኃይል እንዳታዘጋጅ በማድረግ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን አቅም እንደሚያሳጣትም ተናግረዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሓላፊ ሙላው አበበ በበኩላቸው፤ ኩረጃን የሚያበረታቱ የተማሪ ወላጆች እና “የትምህርት ቤታችን ገጽታ እንዳይበላሽ” በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ኩረጃ ሲከናወን በዝምታ የሚያልፉ መምህራን መኖራቸው በግምገማ መረጋገጡን አጋልጠዋል።

ኩረጃን ለመከላከል ለተከታታይ ዓመታት ቢሠራም ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉንና በኩረጃ ሂደት ተሳትፎ ያላቸውን ተማሪዎች፣ ፈታኞች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ጣቢያ ሓላፊዎች ተጠያቂ የሚያደርግ የአፈታተን እና አስተዳደር መመሪያ ቢኖርም ትግበራው ክፍተት እንዳለበትም አስታውቀዋል።

ለኩረጃ መስፋፋት መንግሥት፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ለትምህርት የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን፣ የፈተና ሥርዓትን አለማክበር፤ የመምህራን ተማሪ የማብቃት አቅም አናሳ መሆን እና የተማሪዎች በራስ የመተማመን አቅም ማጣት በምክንያትነት ቀርበዋል::

LEAVE A REPLY