የአዲስ አበባ ወጣት ህይወቱን ሳይሆን ድምፁን ለብልጽግና እንዲሰጥ ዶ/ር ዐቢይ ተማጸኑ
የብልፅግና ፓርቲ የሚሠራው ለትውልድ እንጂ ለምርጫ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
“በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በፓርቲው ፕሮግራም ዙሪያ ሲካሄዱ የነበሩ ማስጨበጫ መድረኮች ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የከተማዋ ወጣቶች ታድመዋል እየተባለ ነው። ይሁን እንጂ ካለፈው የአዲስ አበባ የእሬቻ ዋዜማ በዓልና ጃዋር መሐመድ ላይ እርምጃ አለመውሰዱን ተከትሎ ሸገር ላይ ሙሉ ነጥብ የጣለው የሰበሰባቸውን ወጣቶች ከየት እንዳመጣቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው::
የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ የዜና ምንጮች እንዳደረሱን ጥቆማ ከሆነ ዛሬ አብዛኛው የአዲስ አበባ ወረዳ (ቀበሌ) ሠራተኞች፣ የክፍለ ከተማ ሠራተኞችና የኢሕአዴግ ወጣት ሊግ አባላት በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ትናንት ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል::
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የብልፅግና አስተሳሰብን እና አሠራርን በቀጣይ 50 እና 60 ዓመታት ማሸነፍ ከባድ ነው፤ ማንም እኔን ቢያሸንፍ ከብልፅግና ሐሳብ ወዲያ ግን ኢትዮጵያን ለወራትም ቢሆን ማስተዳድር ይከብደዋል” ካሉ በኋላ፤ “ብልፅግናን በመክሰስ ሳይሆን፤ ከብልፅግና በመማር እና የብልፅግና እሳቤዎችን በማሻሻል ብቻ ነው ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው” ሲሉም የፓርቲያችውን አካሄድና ረዥም ራዕይ በግልፅ አስቀምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም፤ ወጣቶች በምርጫ ወቅቶች ለተወዳዳሪዎች ድምጻቸውን እንጂ ህይወታቸውን መገበር አይገባቸውምም ብለዋል።
ወጣቶች ህልማቸውን ሊነጥቁ ከተዘጋጁ ጉዳዮች በመራቅ የብልጽግና ጎዳናን መከተል ይገባቸዋል ያሉት የብልጽግና መስራች፤ ሰውን አጋድሎ እና አጣልቶ ስልጣን ለመያዝ ያለመ ካለ አስተሳሰቡ ራሱ የቆሸሸ ነው እና ለኢትዮጵያ ስለማይጠቅማት ወጣቶች መንቃት ይኖርባችኋል ሲሉ ምክር ለግሰዋል።
“በሚከሰቱ ግጭቶች ወጣቶች እየተጎዱ ነው፤ ወጣቱን ተገፋፍቶ ወዳልተፈለገ ነገር የሚያስገቡ ሀይሎች ሲሞቱ አስይስተዋልም፤ ወጣት ስለሆናችሁ ለማናችንም ቢሆን ካርዳችሁን እንጂ ህይወታችሁን አትስጡ” ያሉት ጠቅላዮየአዲስ አበባ ወጣቶች ብልፅግናን ከወደዳችሁ ድምጽ ስጡት፤ ካልወደዳችሁት ግን በድምጽ ቅጡት ለማንም ቢሆን ህይወታችሁን አትስጡ ሲሉ ከዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ድጋፍ የማግኛ ተማጽእኖ አሰምተዋል::
የኢህአዴግ ውህደት ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርአት ከመገንባት አኳያ ውህደቱ ሁሉን አካታች መሆኑ እና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ውህደቱ አስፈላጊ መሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል:: በተጨማሪም በተለያዩ ውይይት መድረኮች እንደተገለጸው ብልጽግና ፓርቲ ህዝባዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሀገራዊ አንድነት እና ህብረ ብሄራዊነት መርሆችን የሚከተል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ የህዝቦች ክብር፣ ፍትህና ህብረ ብሄራዊ አንድነት እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት እውን የሚሆንበት ነው ተብሏል።
የቤኒሻንጉሉ ባለሥልጣን በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዛሬ ማለዳ ተገደሉ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር፤ ዛሬ ማለዳ (ሐሙስ ታህሳስ 23 ቀን) በታጠቁ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት መገደላቸው ታወቀ:: የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሓላፊም የባለሥልጣኑ ግድያ በወለጋና በአካባቢው ያለ ከልካይ እየፈነጨ የሚገኘው እና ከኦነግ የተለየው ታጣቂው “ሸኔ ” ቡድን መሆኑን አረጋግጠዋል።
አቶ አብዱላሂ ለመንግሥት ሥራ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ ሳሉ መገደላቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ መለሠ በየነ ጠቁመው፤ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ዛሬ ማለዳ 1፡30 ላይ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ እያሉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ቤንጓ አካባቢ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በጥቃቱ በመኪናው ውሰጥ የነበሩ አንድ ወንድና አንድሴት ላይ ጉዳት መድረሱን እና ተጎጂዎቹ በህክምና እርዳታ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል። አቶ መለስ በቅርቡ አንድ የፖሊስ ሓላፊ በታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውሰው፣ ከክልሉ ተነስቶ አሮሚያ ክልልን የሚያቋርጠው መንገድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ስጋት የነበረበት መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥት ሓላፊዎችን ዒላማ አድርገው በታጣቂዎች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ ስምንት ሓላፊዎች መገደላቸው አይዘነጋም። በጥቃቱ ሌሎችም ሰዎች ሰለባ በመሆናቸው የሟቾች ቁጥር እያየለ ነው የሚሉት ሓላፊው ግድያዎቹ በታጣቂው ሸኔ የተፈፀመ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ባልስለጣናት በሌብነት እንዲዘፈቁ አድርጓል ተባለ
መንግሥት የግንባታው ዘርፍ በቀጣይ 10 ዓመታት የአገሪቱ ዕድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
ሁለተኛው አገር ዐቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የንቅናቄ መድረክ “ተወዳዳሪ ሀገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሓፊዎች እና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል ነው የተባለው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የግንባታው ዘፍር ለአንድ አገር ዕድገት መሰረት ከሆኑት መካከል አንደኛው መሆኑን ጠቁመው፤ ግንባታው ዘርፍ ለሙስና እና ለስርቆት የተጋለጠ መሆኑን እና ከስርቆት ነጻ የሆነ የግንባታ ዘርፍ ሳይኖር ብልፅግና ጋር መድረስ አዳጋች መሆኑን አብራርተዋል። በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ከስርቆትና ከሙስና በፀዳ መልኩና በጥራት ለአገር ዕድገት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ በቀጣይ 10 ዓመታት የግንባታው ዘርፍ በአገሪቱ ዕድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል::
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዘጋጀውና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚቃኘው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄ መድረክ እስከ ነገ የሚቀጥል ይሆናል። የንቅናቄ መድረኩ ዓላማ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በግንባታው ኢንዱስትሪ የሚስተዋሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ግንዛቤና መግባባት በመፍጠር ለኢንዱስትሪው አጠቃላይ ዕድገት የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው መባሉንም ሰምተናል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በፓርላማው ፀደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ሙሉ በሙሉ አፅድቆታል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል። በስብሰባው በሕግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አጀንዳዎችን በጥልቀት እንደመከረባቸው ታውቋል።
የቋሚ ኮሚቴው ተወካይ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክተው ሪፖርት ሲያቀርቡ፤ የሽብር ድርጊት በሰው ህይወት፣ አካል እና ስነ ልቦና እንዲሁም ንብረትና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ አብራርተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሥራ ሓላፊዎች፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የፍትህ አካላት፣ ከህዝብ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዝርዝር ውይይት ማድረጉን አስታውሰው ፤በዚህም ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን እንዲሁምለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦች መገኘታቸውን ነው የተናገሩት።
ረቂቅ አዋጁ መንግሥት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ከሽብር ድርጊት እንዲጠብቅ፣ ጠንካራ የቅድመ መከላከልና ቁጥጥር ሥራዎችን እንዲሠራና አጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያሰጥ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ በመዘርጋት እንዲተገብር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
የመንግሥት አካላት የግለሰቦችን መብትና ነፃነት ከደፈሩ ተጠያቂነት የሚያስከትልባቸውና የሽብር ወንጀል ተጠቂዎች የሚካሱበትንና የሚቋቋሙበትን ሥርዓት የሚፈጥር እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ህግ እንደሚሆንም አስታውቀዋል::
አገሪቱ የምትገኝበት ቀጠና ለሽብር ድርጊት የተጋለጠ በመሆኑና ከውስጥም ከውጭም ስጋቶች በመኖራቸው መንግሥት ወንጀሉን እንዲከላከልና እንዲቆጣጠር የሚያስችለው የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ቋሚ ኮሚቴዎቹ እንደሚፈልጉ በውሳኔ ሐሳባቸው ላይ አመላክተዋል::
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ መስተካከል ይገባቸዋል ያሏቸውን ሃሳቦች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ስብስባው የቀረቡለትን ስድስት ረቂቅ አዋጆች በመመርመር ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር ዕይታ የመራ ሲሆን ፤ የፌደራል መንግሥት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ሥርዓትን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ የሜርኩሪ ንጥረ ነገር ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው የሚናማታ ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ እንዲሁም ዓይነ ስውራን ለንባብ የእይታ ችግር ላለባቸው እና በመደበኛ የንባብ ስልት ለማንበብ አካላዊ ችግር ላለባቸው ሰዎች የቀለም ጽሑፍ ኅትመት ሥራዎችን ተደራሽነት ለማመቻቸት የወጣው የማራካሽ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይም ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በኢትዮጵያና በኳታር መንግሥት መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት እና ጥበቃ ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ በአፍሪካ ሕዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅና በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ የአፍሪካ ካምፓላ ስምምነትን ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አስተያያት ተሰጥቶባቸውና በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ተወስነው ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የተላኩ ረቂቅ አዋጆች መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የኢቢሲ የትግርኛ ፕሮግራም ክፍል ከፍተኛ ተጽዕኖ ደረሰብኝ እያለ ነው፤ ስራ አስኪያጁ ውሸት ነው ብለዋል
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አስተዳደር በትግራኛ ቋንቋ ክፍል ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ሲሉ የትግራኛ ክፍል ባልደረቦች ተናገሩ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የትግርኛ ክፍል ባልደረቦች እንደሚሉት ከሆነ ትግራይን የተመለከተ ፖለቲካዊ ዘገባዎች እንዳይሠሩ በአስተዳደሩ ክልከላ ይደረጋል በማለት ወቀሳ አቅርበዋል ።
ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ጉባኤ ሽፋን እንዳይሰጠው ማድረጉን የኮርፔሬሽኑ የትግረኛ ክፍል ሠራተኞች ለአብነት በማስረጃ አቅርበዋል ።
ኮርፖሬሽኑ ይህ ክልከላ ሲያደርግ የመጀመርያው እንዳልሆነና ከዚህ ቀደምም 50 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈውንና ‘የፌዴራሊዝም ስርዓት የማዳን ጉባኤ’ የሚል ስም የተሰጠውን ኮንፈረንስ ሽፋን እንዳይሰጠው ተደርጓልም ነው ያሉት ሙያተኞቹ ።
ማንነታቸውን መግለፅ ያልፈለጉት የኢቢሲ የትግርኛ ቋንቋ ባልደረቦች አዲሱ የለውጥ መንግሥት ከመጣ ወዲህ በትግርኛ ክፍል ላይ ሳንሱር እና ጫና ይደረጋል ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ንጉሤ ምትኩ ግን ከዚህ የተለየ ምላሽ ነው የሰጡት:: ”ከኮንፈረንሱ ጋር በተያያዘ ማንም እንደዚህ የከለከለ ሰው የለም። በአማርኛ የዜና እወጃ በኩል የፌዴራሊዝም ሥርዓት የማዳን ጉባኤ የተባለውን ኮንፈረንስ መክፈቻውን ዘግበናል። የትግርኛውም ክፍል እንደዘገበው ተከታትያለሁ” ነው የሚሉት::
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ውጪ የተደረገ ምንም አይነት ክልከላ አለመኖሩን ሲያብራሩም” ማንም ቢሆን ይህንን ክልከላ ያደረገ ሰው የለም። ነገር ግን ከኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን ጋር የሚጣረስ ነገር ሲኖር በደንብ ይታያል እንጂ አትዘግቡም ወይም ይህንን ብቻ ዘግቡ የሚባል ነገር የለም።” ከማለታቸው ባሻገር፤ “አሁን ካለው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር የሚጣረስ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ ወይም የህዝቦችን ባህል፣ ማንነትና አብሮ መኖር አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲሆን በኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን መሰረት ውሳኔ እናስተላልፋለን” ሲሉ የጋዜጠኞቹን ወቀሳ አጣጥለዋል።
”ከዚህ ውጪ ግን የትግራይን ህዝብ የሚመለከት፣ የትራይን ህዝብ ጥቅም የሚመለከት፣ በክልሉ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች፣ ህዝቡ የሚያነሳቸው ችግሮችና ሌሎች መዘገብ ያለባቸው ጉዳዮች ሁሉ ሽፋን ያገኛሉ፤ በክልሉም ወኪል አለን።” የሚሉት ዶ/ር ንጉሴ፤ እንዲህ ዓይነቱ ቅሬታ በሥራ ላይ ባሉት የትግርኛ ቋንቋ ባልደረቦች እስካሁን ወደርሳቸው ጋር እንዳልመጣም ገልፀዋል።
በሸገር ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ህንፃ በ831 ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው
በአዲስ አበባ በ831 ሚሊየን ብር ወጪ ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ህንፃ ግንባታ ለማካሄድ ከቻይናው የኮሙዩኒኬሽን እና ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲ ሲ ሲ ሲ) ጋር ስምምነት እንደተፈረመ ሰምተናል።
ስምምነቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ እና በቻይናው የኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ መካከል በዛሬው ዕለት መፈረሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽሕፈት ቤት ካወጣው መግለጫ ተመልክተናል።
ማዕከሉ የትራፊክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የትራፊክ መብራቶችን የቆይታ ጊዜ እንደ ትራፊክ ፍሰቱ መጠን የመቀያይርና ልዩ ልዩ የትራፊክ ፍሰት ማስተካከያ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ሥራም ይከናወንበታል ነው የተባለው ።
በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠት፣ የትራፊክ ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋ እና የደህንነት መረጃዎች ወደሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ተቋማት በጊዜው እንዲተላለፉ ማድረግ ያስችላል መባሉንም ከወጣው መረጃ ታዝበናል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ ፍሰት ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ታምኖበታል። የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ ከመሬት በታች አራት ወለሎች ሲኖሩት፥ ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በተጨማሪ መረጃ ማደራጃ ክፍሎች፣ የወንጀልና የአደጋ መከላከያ መረጃ ቢሮዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን እንደሚያካትትም መረዳት ተችሏል።
የሚገነባው ማዕከል የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎች እና መሰረተ ልማቶች የሚሟሉለት ከመሆኑ ባሻገር በ18 ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱላይ ተገልጿል::