የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 24 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 24 ቀን 2011 ዓ.ም

በጎንደር -ጠገዴ ሕጻናት ግድያ የሚፈለጉት ሰው መቀሌ መሆናቸው ተረጋገጠ

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፤ ጠገዴ ወረዳ ታግተው ከተወሰዱ ስምንት ታዳጊዎች መካከል ስድስቱ መገደላቸው ይታወቃል:: ታዳጊዎቹ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የተወሰዱት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት አካባቢ ማይዳራ በሚባል ወንዝ አካባቢ ከብት በመጠበቅ ላይ እያሉ ነበር።

ዕድሜያቸው ከ10-16 የሚሆኑት ታዳጊዎች፤ ለቀናት ታግተው አጋቾቻቸው የጠየቁት ገንዘብ ሳይከፈል በመቅረቱ በጥይት ተገድለዋል::

ከሟቾቹ መካከል አንዱ ጥጋቡ ደሳለኝ የተባለ የ10 ዓመት ታዳጊ ነው። ጥጋቡ ለቤተሰቦቹ ሦስተኛ ልጅ ሲሆን አባቱን በመስክ ሥራዎች ለማገዝ በተለያየ ጊዜ ትምህርቱን ቢያቋርጥም ሁለተኛ ክፍል ግን ደርሶ ነበር። የጥጋቡ አባት አቶ ደሳለኝ ማለደ “ልጄ በቤተሰቡም ሆነ በትምህርት ቤቱ የተወደደ፣ ታዛዥና ሰው አክባሪ ነበር” ሲሉ በሀዘን በተሰበረ ልብ ተናግረዋል።

ጥጋቡ ከቤት እንደወጣ ባልተመለሰበት ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ትምህርት ቤት አልሄደም ነበር። አባቱ ሰብል ለመሰብሰብ ወደ እርሻቸው በመሄዳቸው እርሳቸውን ለማገዝ እርሱም ከብቶቹን ይዞ ወደ መሥክ ሥራ ተሰማራ። ሰዓቱ ከቀኑ ከ8፡00 ገደማ ቢሆንም ጥጋቡ ግን ወደ ቤቱ ሳይመለስ ቀርቷል።

ማታ ወደ ቤት ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ጥጋቡን ትተው፤ ከብቶቹ ወደ ቤታቸው ቢያመሩም እርሱ ግን የውሃ ሽታ ሆነ። በሁኔታው የተደናገጡት ቤተሰቦች አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ ፍለጋቸውን መጀመራቸውን አባት ለቢቢሲ አስረድተዋል::

“ከዚህ በፊት ህፃናት ተይዘው ባያውቁም፤ በአካባቢው ሽፍቶች በመኖራቸው ይዘውት ይሆናል፤ ምን የበደልኩት ነገር ይኖር ይሆን?” በማለት ሰው እየጠየቁ፣ በርሃና ጥሻውን እያቆራረጡ ሲፈልጉም አድረዋል::

በማግስቱ ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ልጆቹን ያገቷቸው ግለሰቦች ደውለው “አስረናቸዋል” በማለት ልጃቸው ከማን ጋር በምን ሁኔታ እንዳለ ቁርጡ የተነገራቸው አባት ፤ ለወረዳው ፖሊስ ጣቢያ “ልጄ ታግቷል” ሲሉአመልክተዋል።በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ከአጋቾቹ ስልክ ተደውሎ ‘ስምንት ሕፃናት ይዘናል፤ ለእያንዳንዳቸው 120 ሺህ ብር ይዛችሁ ኑ’ ሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም በኃዘን ድባብ ሆነው ገልፀዋል።

“እኛ ድሆች ነን። ብር የለንም፤ ምንስ ተገኝቶ ነው? ፤ ምንስ በድለናችሁ ነው?”  በማለት ቢጠይቁም “ብር ነው የምንፈልገው ሌላ ጉዳይ የለንም፤ ገንዘብ አላችሁ፤ ተካፍለን እንብላ” ሲሉ እቅጩን እንደተነገራቸውም ጠቁመዋል። በሁኔታው ግራ የተጋቡት ቤተሰቦች በተደወለበት ስልክ እየደወሉ “ብር አላገኘንም፤ እያሰባሰብን ነው፤ እባካችሁ ልጆቹን ስደዱልን” እያሉ ልጆቹ እንዳይጎዱና እንዳይገርፉ ሲለምኑ፤ አጋቾቹም ሲደውሉ በዚህ መልክ ሰንብተው ነበር::

“ገንዘብ ይዛችሁ ካልመጣችሁ እርምጃ እንወስዳለን” እያሉ ያስፈራሯቸው እንደነበር የገለፁት አቶ ደሳለኝ አጋቾቹ ለልጆቹም ስልክ እየሰጡ “ገንዘብ ይዛችሁ የማትመጡ ከሆነ፤ አታገኙንም” እንዲሉ እንዳስገደዷቸውና “ልጆች ናቸው። ምን በደሏችሁ?፤ እኛ አልበደልናችሁ፣ እባካችሁ!” እያሉ እየተለማመጡ ቢቆዮም ግን ይገድሏቸዋል የሚል ሐሳብ ፈፅሞ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ያሳለፉትን ቀናትም “በአፋችን እሳት በሆዳችን እሳት እየወጣ ነው የሰነበትነው” ያሉት አባት በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ታህሳስ 19 ቀን ልጃቸው ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር እንደተገደለ ከወረዳው ፖሊስ ተደውሎ መስማታቸውን ገልጸዋል። በልጃቸው ላይ ይህ ከሆነ በኋላ፤ እንኳን ለልጆቻቸው ለራሳቸውም ስጋት እንዳደረባቸው፤ ቀሪዎቹ ልጆቻቸውም ቤት ውስጥ እንደሚውሉም ነው ይፋ ያደረጉት።

የጠገዴ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ተወካይ ሓላፊ ኢንስፔክተር እሸቴ ገ/ማሪያም ከግድያው ጋር በተያያዘ ዘጠኝተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና አሁንም ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከቤተሰብ የልጆቹ መጥፋት ጥቆማ እንደደረሳቸው፤ አጋቾቹ ደውለውበታል የተባለውን የስልክ መስመር ለማጣራት ወደ አካባቢው ኢትዮ ቴሌኮም መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ጽፈው፣ በዛ መልክ ተጣርቶም የስልክ መስመሩ ባለቤት ማንነት ስለተነገራቸው ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሲጠየቅ “ለአጎቴ ሸጨለታለሁ” የሚል ምላሽ መስጠቱን አብራርተዋል። የስልክ መስመሩ የተሸጠላቸው አጎት የሚገኙበትን ሌላ ስልክ ፖሊስ ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ማጣራት፤ ግለሰቡ መቀሌ ከተማ እንደሚገኙ ቢታወቅም

ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለመመርመር የሚገኙት በሌላ ክልል ውስጥ በመሆኑ ጉዳዩን የፌደራል መንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይል እንዲይዘው በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአካባቢው ‘ሽፍታዎች’ አልፎ አልፎ አሽከርካሪዎችን፣ ግለሰቦችን በማገት ገንዘብ የመጠየቅ ልማድ እንዳለ ያስታወሱት ኢንስፔክተሩ፤ ከዚህ ቀደምም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሽፍቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።

ኢንስፔክተር እሸቴ እንደሚሉት፤ ከህፃናቱ ግድያ ጋር በተገናኘም በአካባቢው ሽፍታ ተብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች  ቤተሰቦችም ተሰውረዋል።

በአካባቢው በቀል ስላለ እርሱን ሽሽት መሰወራቸው፣ እንዲሁም ከግድያው ከተረፈው ልጅ ከሰሙት ቃል ግድያውን የፈፀሙት ሽፍታዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ሌላ ፍንጭ እንደሰጣቸውም ይናገራሉ። እስካሁንም ስምንት የሚሆኑ የሽፍታ ቤተሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በአካባቢው በተለያየ ምክንያት የሸፈቱ ‘ሽፍታዎች’ የሚታወቁ ቢሆንም፤ እነርሱን አድኖ ለመያዝ ግን የአካባቢው መልከዓ ምድራዊ ሁኔታና ግለሰቦቹ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ አዳጋች ሆኖ መሰንበቱን ነው ሓላፊው የገለፁት።

በአማራ ክልል ከምሽት 1 ሰዐት እስከ ንጋት 1 ሰዐት ነዳጅ መሸጥ ሊከላከል ነው

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ በህገ ወጥ መንገድ የሚሸጠውን ነዳጅ ለመከላከል መዘጋጀቱን ገለፀ።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከማደጉ ጋር ተያይዞ የነዳጅ ፍላጎተ መጨመሩን ጠቁመው፤ ሆኖም የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ችግር በመከሰቱ ችግሩን ለመፍታት የፌደራል መንግሥት ከዜጎች ግብር እየሰበሰበና ነዳጅ ላይ ድጎማ እያደረገ ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ሲያቀርብ መቆየቱንም አስታውቀዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ የመጣውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን ነዳጅ በአግባቡ በመጠቀም በተቀናጀ እና በተባበረ መልኩ በመሥራት በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ለማድረስ ይሠራል ነው ያሉት።

ነዳጅን በፍትሃዊነት ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ እኩል አለማከፋፈል፣ የአቅርቦት መቆራረጥ፣ የጥቁር ገበያ መኖር ለነዳጅ እጥረት መከሰት ምክንያት መሆኑ በመነገር ላይ ነው። አሁን ላይ በክልሉ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ ማታ ማታ በህገ ወጥ መንገድ የሚሸጠውን ነዳጅ ለመከላከል ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ አንድ ሰዓት ነዳጅ እንዳይሸጥ ለመከልከል ታቅዷል ነው የተባለው።

በአዲስ አበባ 16 መንገዶችና ድልድዮች ተጠናቀዉ ተመረቁ

ለቀጣዮ ምርጫ የነዋሪዎቹን ድጋፍ ለማግኘት ደፋ ቀና እያለ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንገዶች ባለስልጣን  አማካይነት ተገንብተው የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እና ድልድዮችን አስመርቋል።

ባለሥልጣኑ ያስመረቃቸው ፕሮጀክቶች 16 ሲሆኑ፤ የነባር መንገዶችን ደረጃ ማሻሻልና ጨምሮ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታንም ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

የተመረቁት መንገዶቹ 25 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና ከ10 እስከ 30 ሜትር ስፋት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።ለመንገዶቹና ድልድዮች ግንባታ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገና ወጪውም በከተማ አስተዳደሩየተሸፈነ መሆኑ ተረጋግጧል።

የእነዚህ መንገዶች መገንባት የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ በመቅረፍ የከተማውን የመንገድ ሽፋን ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተገለጸው::

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፕሮጀክቱ በከተማዋ የተጀመሩ የመንገድ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንደሚጠናቀቁ ማሳያ ነው ካሉ በኋላ ፤ የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ከዋና ዋና መንገዶች ግንባታ በተጨማሪ የመጋቢ መንገዶች ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጭምር ገልፀዋል::


ኢትዮጵያ በጎርፍ ለተጎዱ ሶማሊያዊያን  የመድኃኒት እርዳታ ሰጠች

ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ ሂር ሸባሌ ክልል በበለደወይን አካባቢ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሶማሊያዊያን ኢትዮጵያ አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ የሚሰጡ ሃኪሞችን እና 10 ቶን የመድኃኒት ድጋፍማድረጓ ታውቋል።

እርዳታውን በሶማሊያ የኢፌዲሪ ልዩ አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጦፋ ለበለደወይን ዞን አስተዳደር አስረክበዋል፡፡በእርዳታ ርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ የሸባሌ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የክልሉ ፓርላማ ምክትል አፈጉባኤ እና በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት አመራሮች  ተገኝተዋል ተብሏል፡፡

አምባሳደር ጀማሉዲን ሙስጦፋ በዚህ ወቅት በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ፣ ኢትዮጵያ  ከሶማሊያ ህዝብ ጎን በመቆም ቀጣይ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለቸ ብለዋል።

የሂር ሸባሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙሀመድ አብዲ ዋሬ በኢትዮጵያ በኩል ስለተደረገው አስቸኳይ የነፍስ አድን ድጋፍ እና በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት የክልሉን ፀጥታና ደህንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ በጎርፍ የተገዱ ሶማሊያዊያንን ለመታደግ  ላደረገው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


አሜሪካ ዜጎቿ በፍጥነት ከኢራቅ እንዲወጡ አሳሰበች

ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኩድስ ኃይል አዛዥ በአሜሪካ ኃይል ኢራቅ ውስጥ መገደላቸው ተነገረ። ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ቁንጮ ከሚባሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።

ፔንታጎን (የአሜሪካ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት) ጀነራል ሱሊማኒ “በፕሬዝደንቱ ትዕዛዝ” ተገድለዋል ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ጀነራሉ የተገደሉት አሜሪካ በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ አየር ማረፊያ ላይ በወሰደችው የጦር እርምጃ እንደሆነም ተገልጿል። ይህን ተከትሎም ሃይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ካሃሜኒ በአሜሪካ ላይ አጸፋዊ እርምጃ ይወሰዳል በማለት በይፋ ዝተዋል።

የጀነራሉ መገደል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል። የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጃቪድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ አይኤስ፣ አል ኑስራህ፣ አል-ቃይዳ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ሲዋጋ የነበረውን ጀነራል የመግደል እርምጃ እጅግ አደገኛ እና የሞኝ ውሳኔ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ጀነራሉ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተገደሉ በኋላ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ውጥረቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አይሏል።በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፤ ዜጎች በተቻላቸው ፍጥነት ከኢራቅ ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል። ኤምባሲው በቅርቡ በተቃዋሚዎች የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ ምንም አይነት አገልግሎት እንደማይሰጥ አስታውሶ፤ የአሜሪካ ዜጎች ወደ ኤምባሲው በፍጹም እንዳይቀርቡም መልዕክት አስተላልፏል።

ከተቻላቸው በአየር ካልሆነ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት በየብስ ከኢራቅ እንዲወጡ አስጠንቅቋል።

ኢራቅ፤ በኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ ሶሪያ እና ቱርክ ትዋሰናለች። ከኢራቅ በአየር መውጣት የማይችሉ አሜሪካዊያን፤ በየብስ ሳዑዲ ሁነኛ አማራጫቸው እንደሆነች ይታመናል። የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ የእስራኤል ጦር በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተሰምቷል።

ኢራን የጀነራሏን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አጋር በሆነችው እስራኤል ላይ በሌሎች ቡድኖች አማካኝነት ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ግምት እየተሰነዘረ ነው:: በሂዝቦላ ወይም ሃማስ አማካኝነት አልያም ደግሞ ኢስላሚክ ጅሃድ በተሰኘው ቡድን በጋዛ በኩል እስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል የሚሉት ግምቶች ከፍ ያሉ ሆነው ተገኝተዋል።

የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር እና መከላከያ ሚንስትሮች እስራኤል በተጠንቀቅ ላይ እንዳለች ይፋ አድርገዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ቤይናሚን ኔታኒያሁ በግሪክ የነበራቸውን ጉብኝት አቋርጠው ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውም እየተዘገበ ነው።

ጀነራል ሱሊማኒ በኢራን መንግሥት ውስጥ ሁለተኛው ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው ነበሩ። እርሳቸው የሚመሩት ኃይል ተጠሪነቱ በቀጥታ ለኃይማኖታዊ መሪው አያቶላ አሊ ካሃሜኒ ሲሆን ጀነራሉ በኢራናውያን ዘንድ እንደ ጀግና የሚታዮ መሆናቸውን ተከትሎ አያቶላ የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ በኢራን የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አውጀዋል።

እስካሁን ድረስ ፕሬዝደንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም። ይሁን እንጂ የጀነራሉ መገደል ይፋ ከሆነ በኋላ ምንም ሳይሉ የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው በመንግሥታቸው ትዕዛዝ ግድያው መፈጸሙን ያረጋግጣል እየተባለ ነው::

LEAVE A REPLY