መቀሌ የመሸገው ህወሓትና ፌደራል መንግሥቱ ዳግም ላይገናኙ ተለያዮ
ያከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ከተገፋ በኋላ ከለውጡ ቡድን ጋር ለሰከንድ መስማማት ያቃተው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፤ ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ያደረገውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ አቋሜን ያንፀባርቃል ያለበትን መግለጫ አውጥቷል።
የአገሪቱ እና የቀጠናው ሰላም ያሳስበኛል የሚለው ህወሓት አንዳንድ የውጭ መንግሥታት እና ኃይሎች በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆኑ በመግለጫው ቢያነሳም ፣ የትኞቹ ኃይሎች እንደሆኑ ግን በይፋ መግለጫው ላይ ያስቀመጠው ነገር የለም።
«እነዚህ የውጭ መንግሥታት እና ኃይሎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ እያሳደሩት ያለው አሉታዊ ጫና የአገራችንና የአካባቢውን ጥቅም ስለሚጎዳ ከውስጥ ጉዳያችን እጃቸውን ያውጡ» በማለት መልእክት ያስተላለፈው ህወሓት ፤ ይህ ካልሆነ ፤ የአፍሪካ ኅብረትና መንግሥታት ይህንን ጣልቃ ገብነት ተረድተው የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ ነው ያለው።
በቅርቡ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ተዋህደው ብልፅግና ፓርቲ መመሥረቱን የተቃወመውና ብልፅግና ፓርቲን እንደማይቀላቀል ያሳወቀው ህወሓት፤ ኢህአዴግ የፈረሰበት አካሄድ ህጋዊ ያልሆነ እና ፀረ ዲሞክራሲያዊ ነው በማለትየዶክተር ዐቢይን አዲስ ፓርቲ “ጥገኛ እና ህጋዊ ያልሆነ” በማለት አብጠልጥሎታል።
በትግራይ ህዝብ ትግል የተሸነፉ ኃይሎች እንደገና በመሰባሰብ በአገሪቱ የተገነባው ህብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ለማፍረስ እያደረጉት ባሉት መተናነቅ የትግራይ ህዝብና ህወሓትን ጠላት በማድረግ ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል እየሠሩ ነውም ሲል ከሷል።
ህወሓት በይፋ ብልፅግና ፓርቲን እንደማይቀላቀል ባሳወቀበት ጉባኤ “ከእንደኛ ዓይነት ፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ግንባር እና ውህደት እስከ መፍጠር የሚደርስ ትግል እና መደጋገፍ እናደርጋለን” በማለት ቀጣይ አቅጣጫው ምን እንደሆነ አመላክቷል:: ሆኖም ድርጅቱ ከየትኞቹ ፌደራሊስት ኃይሎች ጋር ጥምረት እንደሚፈጥር ግን ድፍንፍን አርጎ ማለፉን የመረጠ ይመስላል::
ህወሓት በጉባኤው ለኤርትራ ህዝብም መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፤ “የኤርትራ ህዝብ እና የትግራይ ህዝብ አንድ ቋንቋ፣ ተመሳሳይ ባህል ያለው እና በጋብቻ የተሳሰረ ወንድማማች ህዝብ ነው። ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ግን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከሰላም እና ልማት ይልቅ፣ መግባት ወደ ማይገባን ጦርነት በመግባት የማያስፈልግ ኪሳራ ከፍለናል” በማለት የድርጅቱን ስህተት ወደ አገራዊ ስህተትና ግጭት ቀይሮ አቅርቦታል።
“ባለፈው ዓመት በሁለቱም አገራት መሪዎች የተጀመረው ግንኙነት ተስፋ የነበረው ቢሆንም በሂደት ግን ተስፋ የተጣለበት ግንኙነት ተቋርጣል። የተጀመረው ተስፋ የሚሰጥ ወንድማማችነት እና ዝምድና በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተና ለሁላችንም ጠቃሚ እንዲሆን ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ የሚጠብቅባቸው ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።” ብሏል በመግለጫው::
ኢህአደግን የመሰረቱ የአራቱ ድርጅቶችን የጋራ ሀብት ህግና ሥርዓት በተከተለ መንገድ ድርሻውን እንደሚያስመልስም በአቋም መግለጫው አንጸባርቋል:: ድርጅቱ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚኖረው ግንኙነትም ህግና ህገ-መንግሥትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ያመለከተው የህወሓት መግለጫ ከዚህ ውጭ የሚኖር እንቅስቃሴ ተቀባይነት አይኖረውም ነው ያለው።
በአርማጭሆ ሕጻናትን ፣ ሾፌሮችንና ግለሰቦችን ያገቱ 50 ሰዎች ተያዙ
በአርማጭሆ አካባቢ ሕጻናትን፣ ሾፌሮችን እና ግለሰቦችን በማገት ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወደ 50 የሚደርሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነገረ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በእዚህና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም በአርማጭሆ ህጻናትና ሾፌሮችን በማገትና ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈም በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት እና በንግድ ተቋማት ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘም 80 ያህል ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል “ሕጋዊ የሆነውን መጅሊስ ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች እና በመስጂድ ቃጠሎ የተሳተፉ ይገኙበታል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ፤ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል ጎን ለጎን ጉዳት የደረሰባቸውን መስጂዶች እና የንግድ ተቋማትን በመገንባት እና ተጎጂዎችን በማቋቋም ረገድ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃላቸውን ሰጥተዋል::
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ በነበረ አለመረጋጋት ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በተመለከተ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም ስለጉዳዩ የፌደራል ፖሊስ መረጃ የለኝም ማለቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ አራት የሚሆኑ ተማሪዎች እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት መታገታቸውን መረጃ እንደደረሳቸው አልሸሸጉም።
መረጃውንም ለፌደራል ፖሊስ እና ለኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውንና ጉዳዩን እንደሚከታተሉት አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፤ በአማራ ክልል የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የክልሉ የፀጥታ ኃይል የክልሉን ፀጥታ ለማስጠበቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ይፋ አድርገዋል።
ኅብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የክልሉን ሰላም እንዲያስጠብቅ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፤ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል::
ሰባት የውጭ ዜጎች ጥረታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችን ባዛር ላይ ሲሸጡ ተያዙ
ሰባት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በባዛሮች ላይጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ ምርቶችን ሲሸጡ ተደርሶባቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተሰማ፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ስምንት ዓይነት የባህላዊ መድኃኒቶች ፤ ጸጉርን ለማከምና ለማሳጅ ይረዳል በሚል ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እነዚህ ምርቶች ያልተመዘገቡ፣ የማይታወቁ ፣ጥራትና ደህነንነታቸው ያልተረጋገጠ በመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም አስጠንቅቋል፡፡
ባለስልጣኑ በድንገተኛ ቁጥጥሩ ወቅት የያዛቸው እና ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ያሳሰበው ምርቶች፦
ካስቱሪር ሄርባል ሄር ( KASTURIR HERBALHAIR )
ንላንባሪ ካስቱራ ሄርባል ( NEELAMBARI KASTURA HERBAL )
ንላምባሪ ሄርባል ኦይል ( NEELAMBARI, HERBAL OIL )
ካስቱሪ ሄርባል ሄር ኦይል ( KASTURI HERBAL HAIR OIL)
ንላምባሪ ሄርባል ( NEELAMBARI, HERBAL)
ኤች ኤች አይ ኤን ኬ ኤን አይ ( HHINKNI)
ሳንጂቪን ሄርባል አዩስቸር ( SNNSEV,N HYREBALE Ayu)
ንላምባሪ ሄርባል ማሳጅ ( NEELAMBARI,HERBAL MASSAGE) መሆናቸው ተረጋግጧል::
ፈጽሞ መግባባት ያልቻሉት ኢትዮጵያ ፣ ግብጽና ሱዳን ነገ በአ/አ ይወያያሉ
በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ አደራዳሪነት ቀደም ሲል ተደጋጋሚ ውይይቶች ቢያካሂዱም ፈጽሞ መግባባት ያልቻሉት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሦስትዮሽ ውይይት ታህሳስ 29 እና 30 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገና ሐሙስ የሚካሄደው ውይይት የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በተገኙበት እንደሚከናወን ነው የተጠቆመው፡፡ይህ የቴክኒክ ስብሰባ፣ በግድቡ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ዙሪያ ትኩረቱን በማድረግ የሚካሄድ መሆኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ውይይት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ፣ ካይሮ ፣ ካርቱም እንዲሁም በዋሽንግተን መካሄዱ አይዘነጋም፡፡