ታክሲ- ነክ ነገሮች || በእውቀቱ ስዩም

ታክሲ- ነክ ነገሮች || በእውቀቱ ስዩም

ትናንትና ከካዛንችስ አዋሬ ምኒባስ ተሳፍሬ ስሄድ አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ ክፉኛ ይታከከኛል።

እርድናን ከእርጅና አስተባብሬ የያዝኩ እኔ ወንድማችሁ ይቺን አጭር ማሳሰቢያ ለቀቅሁበት።

“ጀለስ ጭር ያለ ቦታ የሚያስደስትህ ከሆነ ኪሴ ውስጥ መግባት ትችላለህ።  መብትህ ነው።  ስርቆትን ግን አታስበው!! ዶላሬን ስዊዝ ባንክ አኑሬዋለሁ።  አይፎኔ ቤት ጥየው መጥቻለሁ።  ፍላሼን እንደ ማተብ አንጥልጥየዋለሁ። ባጠቃላይ በዚች ሰአት መስረቅ የምትችለው ቀልቤን ብቻ ነው። “

2 – አዲሳባ ያለው የራይድ ታክሲ አገልግሎት ካሜሪካው ኡበር የተቀዳ ይመስለኛል።  ግን ካሜሪካው አቻው ብዙ ልዩነት አለው። አማሪካ “ ኡበር “ ለመጥራት ሂሳብ ቅድምያ በካርድ መክፈል አለብሽ።  ጥሪውን ከሰረዝሽ ደሞ ኪስራው ባንቺ ነው።

ያዲሳባ ራይድ እንዲህ ያለ አሰራር የለውም። እና ድምፃዊ ጌቴ አንላይ እንዳለው “ሁኔታው ለኔ ተመቸኝ “

በቀደም ራይዶች ጋ ደወልኩ፤

ከመሸጋገርያ ሙዚቃ በሗላ

” እባክዎ መነሻዎ የት ነው?” አለችኝ ቪትስ አክፋፋይዋ!

“አዋሬ በድሩ በለጨ ፊትለፊት ቁምያለሁ:: ደሞ አንቱ ባትይኝ ደስ ይለኛል” አልሁ፤

“መድረሻዎት?

“ጃንሜዳ”

” ባቅራቢያ ያለ አሽከርካሪ ይደውልሎታል”

” አመስግናለሁ አንቱ ኦፕሬተር”

የነጂውን ስልክ በመጠበቅ ላይ እያለሁ::

አንዲት መኪና ከፊቴ ቆመች፤

” በውቄ ና ግባ ልሸኝህ”

አይኔን አላሸሁም::

አመስግኘ ገባሁና መንገዴን ተያያዝኩት፤ ትንሽ ቆይቶ የራይዱ አሽከርካሪው ደወለ:: ምስኪን!!

” ይቅርታ!! የሚሸኘኝ ዘመድ አግኝቼ እየሄድኩ ነው” አልኩት::

ሰውየው ጦፈ።

“ታድያ እዚህ ድረስ ለምን ታጉላላኛለህ?”

“መናደድ አያስፈልግም። ለተጉላላህበት ያስራምስትብር ሞባይል ካርድ ይላክልሀል።

ሰውየው ስልኩን ዘጋው፤ በቅርብ ርቀት ቢያገኘን ኑሮ የኦክስጂን መሳቢያየን ይዘጋልኝ ነበር፤

በነገራችን ላይ ሰማያዊ ላዳ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ያገልግሎት ዘመኑን የጨረሰ ይመስላል:: አንድ ሰማያዊ ላዳ የሚነዳ ወዳጄ ራይድ የተጀመረ ሰሞን የሰፈሩ ጎረምሶችን አሰተባብሮ የራይዶችን መኪና ጎማ ሲያስተነፍስ ይውል ነበር።  ከሰባት ወር በሗላ ሳገኘው ግን ራሱ ተንፍሷል።

” ራይዶችን እንዴት ታያቸዋለህ?”

ስለው የመለሰልኝ መልስ አንጀት ይበላል፤

” እነሱ በዳታ እኛ በጌታ እንተማመናለን”

LEAVE A REPLY