የግብፅ እና የኢትዮጵያ ስምምነት አልተሳካም
ዛሬ በአዲስ አበባ ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው የህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት አልተሳካም
በተለያዩ ሶስት ውይይቶች መቀራረብ መቻላቸው ሲገለጽ የሰነበተው ውይይት ግብጽ አዲስ ይዛ በመጣችው ያልተጠበቀ ሂሳብ ምክነያት ነው ሊፈርስ ይቻለው ተብሏል።
ግብጽ በአራተኛው ስብሰባ ላይ ይዛ ያቀረበችው የውሃ ሙሌት ጊዜ እስከ 21 ዓመት የዘለቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ከ4 አመተ እስከ 7 ዓመት ጊዜ ህዳሴ ግድብን ለማሟላት መዘጋጀቷን አስታውቃለች።
በአዲስ አበባው ድርድር ግብጽ ይዛ ያቀረበችው ሂሳብ ከዚህ በፊት ከነበሩት ድርድሮች የተለየና ላለመስማማት ቆርጣ መነሳቷን አመልካች መሆኑ ነው የተነገረው። በተለይ የውሃ ሙሌቱ ከ 12 እስከ 21 ዓመት የሚወስድ ጊዜ መጠየቋ እንግዳ እንደሆነ ነው ባለሙያዎች የገለፁት።
ድርቅ በሚከሰት ጊዜ ሊለቅ የሚችል የውሃ መጠንም ላይ ሃገራቱ ስምምነት ሊደርሱ ካለመቻላቸውም በላይ የደረቅ ትርጉም አፈታትና አተረጓጎም ላይም መግባባት አለመቻላቸው ተመልክቷል። ግብጽ 40 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በታች ሲሆን ድርቅ መሆኑ ታውቆ ውሃ ይለቀቃል ስትል ኢትዮጵያ በበኩሏ 35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ነው ድርቅ መባል ያለበት ስትል ተከራክራለች።
አራት ዮንቨርስቲዎች በ470 ተማሪዎችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰዱ
የ2012 የትምህርት ዘመን ከተጀመረ አምስት ወራት ቢሞሉትም ከወራት በፊት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን የተማሪዎች ግጭት ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቱ ተስፋፍቶ የሞትና የአካል ጉዳት ያስከተሉ ግጭቶች ሲስተናገዱ ከመሰንበታቸው ባሻገርየመማር ማስተማር ሂደቱም ተስተጓጉሎ ቆይቷል።
ዩኒቨርሲቲዎቹም በግጭቱ ተሳትፎ አላቸው ያሏቸውን ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው እየተነገረ ነው። እርምጃ ከወሰዱት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጎንደር ዩኒቨርስቲ አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው በፌሰስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ መሰረት በዩኒቨርሲቲው በተከሰተው አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲቆራረጥ ቆይቷል።
ተቋሙ ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረጋቸው ውይይቶችም አንዳንድ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና የጤና ባለሙያዎች የተከሰተውን ሁከት በማነሳሳት፣ የህይወት እና የአካል ጉዳት እንዲደርስ በተለያዩ ደረጃዎች አሉታዊ አስተዋፅኦ በማድረግ፣ በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጣቸውም ችላ በማለት ሁከት እንዲስፋፋ በማሰብ ሠራተኞችን በማነሳሳት እና ቀስቃሽ መልእክቶችን በመበተን ተሳታፊ ሲሆኑ መቆየታቸውን መረዳት ችያለው ብሏል ዩንቨርሲቲው።
በመሆኑም ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 2 ተማሪዎች ለአንድ አመት፣ 39 ተማሪዎች ለሁለት አመት፤ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው (ከዩኒቨርሲቲው) እንዲሰናበቱ መወሰኑን ዘግበን ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ለ7 መምህራን ቀላል የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን እና ለ8 የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ከሥራ እንዲሰናበቱ ወስኗል።
ሌላኛው ግጭት ተነስቶ ሁለት ተማሪዎች የሞቱበት ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን አውከዋል ያላቸውን 335 ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና መምህር ላይ እርምጃ ወስዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን እንደገለጹት በብሔርና ሃይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሥራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሦስት ጊዜ መቋረጡን ተናግረው ፤ ባለፉት ሁለት ወራት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞችና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱንም አረጋግጠዋል።
ከነዚህ መካከል 12 ተማሪዎችና ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አንድ መምህር ከሥራ መታገዱን እና ለ320 ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል።
እርምጃ የተወሰዳባቸው ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና መምህሩ በዩኒቨርስቲው ውስጥና ውጭ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነው መገኘታቸው በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ግጭቶች በተደጋጋሚ ተነስተው በተለያዩ ጊዜያት የተማሪዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያየ ተሳትፎ በነበራቸው ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ሁለት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ፤ ሰባት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሦስት ዓመት፣ ስምንት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው የታገዱ ሲሆን፤ አንድ ተባሮ የነበረ (በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያልነበረ) ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ ዩኒቨርሲቲው ክስ መስርቶበት በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ወስኗል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሌላኛው በግጭት ሲታመስ የነበረ ተቋም ነው። ይህንን ተከትሎም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ታኅሳሥ 27/2012 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ባለፉት ሁለት ወራት ከተፈጠረዉ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ ትምህርት እንዲስተጓጎል ፍላጎት ባላቸዉና ሁኔታዎችን በመጠቀም ችግር የፈጠሩ 51 ተማሪዎችን በመለየት እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።
በዚህም 31 ተማሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸዉ ሲሆን፣ 20 ተማሪዎች ላይ ከ1 አመት እሰከ ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መርሃ-ግብር ማገድ የሚደርስ የዲሲፕሊን ቅጣት ርምጃ መወሰዱን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።
ከተቋማዊ ለዉጥ ሂደቱ ጋር በተገናኘ በአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዙርያ የምክትል ፕሬዝዳንት እና የ3 ዳይሬክተሮች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎችም የ3 ሓላፊዎችን ለዉጥም አድርጌያለሁ ብሏል ጅማ ዩኒቨርሲቲ::
አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ወራት በተከሰቱት ግጭቶች ተሳትፎ ነበራቸው ባሏቸው ከ470 በላይ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ እርምጃ እንደወሰዱ ታውቋል::
በረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ለተመሰረተባቸው ክስ መከላከያ አቀረቡ
የጥረት ሀብትን በመመዝበርና ሙስና በመፈጸም ተጠርጥረው ለእስር የተዳረጉት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ዐቃቤ ህግ ለመሰረተባቸው ክስ የመከላከያ ማስረጃ በዛሬው ዕለት አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በተከሰሱባቸው ክሶች ላይ የመከላከያ ማስረጃ ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር::
ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ሰነድ እና አሉን ካሏቸው 11 የቃል ምስክሮች ውስጥ ሦስቱን ዛሬ አቅርበዋል። የተከሳሽ ጠበቆች በአንደኛው ክስ ካቀረቧቸው አራት የቃል ምስክሮች አንዱ በማረሚያ ቤት እንደሚገኝ በመጥቀስ ፣ በሁለተኛው ክስ በጽሑፍ ያቀረቧቸው የቃል ምስክሮች ግን ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ጠበቆች የቃልና የሰነድ የመከላከያ ማስረጃቸውን ለፍርድ ቤት ሲያስገቡ ለዐቃቤ ህግ በተገቢው ጊዜ እንዳልሰጡ አስረድቷል። በመሆኑም የቃል ምስክሮች ከሰነዶች ተነስተው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሠጡ ስለሚችሉ ሰነዶችን መርምሮ ለመከራከር ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ምስክሮች ከአዲስ አበባ የመጡ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአላስፈላጊ ወጪ እንዳይዳረጉ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሠጡ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ጠበቆች ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም የቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት ዳኞች ሲያቀርቡ ለዐቃቤ ህግም ማቅረብ እንደነበረባቸው አስታውሶ ፤ የቃል ምስክሮች ከሰነዶች ተነስተው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሠጡ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ለጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል::
በአ/አ የትራፊክ ክፍያ ከሰኞ ጀምሮ በአምስት ባንኮች እንዲሆን ተወሰነ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ክፍያ አገልግሎት ከሰኞ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ባሉ አምስት ባንኮች መሰጠት እንደሚጀምር ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የትራፊክ ክፍያን በዘመናዊ መንገድ መቀየር በሚቻልበት አግባብ ላይ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የትራፊክ ክፍያ አገልግሎት የ”ለሁሉ” አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብቻ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፣ ይህም አሽከርካሪዎች እንዲጉላሉ እና ረዥም ወረፋ እንዲጠብቁ ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው። ይህን አሠራር በዘመናዊ መንገድ ለመቀየርም የከተማ አስተዳደሩ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አሽከርካሪዎች የትራፊክ ክፍያዎችን በአቅራቢያቸው ባሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የአቢሲኒያ ባንክ እና የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ ክፍያ መፀጸም ይችላሉ ነው የተባለው።በተጨማሪም የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም የትራፊክ ቅጣት መክፈል የሚችሉበት አዲስ አሰራር በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመዘርጋት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየተሠራ ነው ተብሏል።
ሌሎች ዘመናዊ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ክፍያዎችን መፈጸም በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ እየተሠራ መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደቡብ አፍሪካ ገቡ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀኑ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታህሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በጊኒ ሪፐብሊክ እንዲሁም በኢኳቶሪያል ጊኒ ራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የለውጡ መሪና የብልፅግና ፓርቲ ፈጣሪ በኢኳቶሪያል ጊኒ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ጋር የተወያዩ ሲሆንየአገሪቱን የክብር ኒሻንም ተሸልመዋል። ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥ እና ሰላምን ከማስፈን አንጻር በአፍሪካ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተበረከተ መሆኑም ታውቋል።
ከፕሬዚዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ አገራት በባሕል እና ቱሪዝም ዘርፍ አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም ተፈራርመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀደም ብለው በጊኒ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር መወያየታቸው እና የኮናክሪን ወደብ መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የጊኒ ሪፐብሊክ እና የኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል።የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸው በፕሬዚዳት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ የሚካሄድ ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ።
በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸውም ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።በተጨማሪም በኢምፔሪያል ወንደረርስ ስታዲየም በሚኖረው የዳያስፖራ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉም ነው የተገለጸው።