ደምቢዶሎ ውስጥ በታጣቂዎች ታግተው ከነበሩት ተማሪዎች 21 ተለቀቁ: 6ቱ አሁንም እንደታገቱ ነው
በደምቢ ዶሎ ከታገቱ ተማሪዎች መካከል 21 መለቀቃቸው ተገለፀ በታጣቂዎች ከታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውስጥ ሃያ አንዱ መለቀቃቸውን እና ቀሪ 6 ተማሪዎችን ለማስለቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ሴክሬተሪያት ሓላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እገታ ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ በሁኔታው ዙሪያ ለኢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ንጉሱ በማብራሪያቸው፤ ሰሞኑን በደምቢ ዶሎ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 16 በሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች የፀጥታ ችግሮች እንደነበረ በማንሳት፤ በዚህም ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ወደየቤታቸውና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎቹን ለቀው ሄደዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲዎቹ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የቦርድ አመራሮች እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም አስታውሰውከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲዎችን ሁኔታ የሚያይና የማረጋጋት ሥራ የሚሠራ ቡድን መዋቀሩን፤እንዲሁም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ማስከበር ሥራ እንዲሥራ ትእዛዝ ተላልፎ የማረጋጋጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ችግር ከተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ሲከሰት በስጋት ከጊቢ ወጥተው ጉዞ ላይ ያሉ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ መታገታቸውን ገልፀዋል። የታገቱ ተማሪዎችን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በማንም ላይ ጉዳት ሳይደርስ ማስለቀቅ ተገቢ በመሆኑ እና የመንግስትም ቀዳሚ ሥራ በመሆኑ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢው ወጣቶች፣ ከመከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር ጋር ሢሠራራ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 13 ሴቶች እና 8 ወንዶች፤ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላም መለቀቃቸውን ያረጋገጡት አቶ ንጉሱ ፤ እስካሁን አንድ የአካባቢውን ወጣት ተማሪ ጨምሮ 6 ተማሪዎች ታግተው እንዳሉ በስፍራው ስራውን ከሚያስተባብረው የፀጥታ መዋቅር መረጃ አግኝተናል ካሉ በኋላ ጉዳዩን በሰላማዊ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እና ልጆቹ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዲወጡ ለማድረግ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት እንዲሁም የፀጥታ አካላት ተገቢውን ስራ እየሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ አካላት በቁጥርም ደረጃ የተለያዩ መረጃዎችን እየሰጡ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤በአካባቢው መንግስት ያሰማራው የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የአካባቢው የፀጥታ መዋቅር በጋራ የገመገመው እስካሁን አንድ የአካባቢውን ወጣት ተማሪ ጨምሮ 6 ተማሪዎች እንደታገቱ መረጋገጡን ነው ያስረዱት።
ቀሪዎቹን ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለማስለቀቅ፤ መንግስትም የአካባቢው ኅብረተሰብም እየሰሩ ነው ብለዋል።
በተሻሻለው አዋጅ መሠረት መንግሥት የጦር መሣሪያ ለዜጎች መሸጥ ሊጀምር ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን መብትና ደህንነት ለማስከበር የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥርን በተመለከተ አዲስ ሕግ ማውጣት አስፈልጎኛል ባለው መሠረት ረቂቅ አዋጁም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ትናንት ታህሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጸድቋል።
“ተቆጣጣሪ ተቋም” ተብሎ የሚጠራው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ውክልና የተሰጠው የክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሥሩ ብሔራዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሥራ ክፍል አደራጅቶ አዋጁን እንደሚያስፈጽምም ተገልጿል።
ለመሆኑ ይህ ሕግ ምን ይላል? ማን፣ ምን፣ እንዴት መታጠቅ ይችላል በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ ቢቢሲ ዝርዝር ዘገባ አቅርቧል:: በዚህም መሠረት ለግለሰብ የሚፈቀደው አንድ አነስተኛ ወይም አንድ ቀላል የጦር መሳሪያ ብቻ ነው። ለድርጅትም የሚፈቀደው የጦር መሳሪያ አይነት አነስተኛ ወይም ቀላል የጦር መሳሪያ ሲሆን፤ ዝርዝሩ እና የጥይት ብዛት በተቆጣጣሪው ተቋም በሚወጣ መመሪያ ይወሰናል ነው የተባለው።
የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተጠየቀበት የጦር መሳሪያ ከዚህ ቀደም በሌላ ሰው ስም ፈቃድ ያልወጣበት እና የጦር መሳሪያው ወንጀል ያልተሠራበት መሆን አለበትም ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
በተቆጣጣሪ ተቋሙ የሚወጣውን ዕድሜ የሚያሟላ፣ ቋሚ አድራሻ እና መተዳደሪያ ገቢ ያለው
ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፍቃድ ከጦር መሳሪያ አያያዝ ጋር ያሉ ሕጎችን ግዴታዎች መወጣት የሚችል ፣ ለጦር መሳሪያ ፍቃድና እድሳት አስፈላጊውን ክፍያ የሚከፍል ፣ ከሚኖርበት አካባቢ አስተዳደር መልካም ሥነ ምግባር ያለው ለመሆኑ የትብብር ደብዳቤ ማቅረብ የሚችል የመሣሪያ ፍቃድ ማግኘት ይችላል።
በሌላ ጎኑ በዚህ አዋጅ መሰረት ከተፈቀደለት ሰው ውጪ ማንኛውም ሰው፤ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ እና መለዋወጫዎች ወይም አብረው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን፣ ወደ ሀገር ማስገባት እና ማስወጣት፣ መያዝ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ መደለል፣ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ ማዘዋወር . . . ከተከለከሉ ተግባራት መካከል የተካተቱ በመሆናቸው በጥብቅ ይከለከላል።
የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የማይቻልባቸው ሥፍራዎች ደግሞ:-
ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው ሥፍራዎች
በምርጫ ሥፍራዎች
ሆቴል፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ሙዚየሞች እና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች
በትምህርት እና ሃይማኖት ተቋማት ግቢ ውስጥ
ሆስፒታል፣ መሥሪያ ቤቶች . . . የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች መሆናቸው በአዋጁ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። መሳሪያ ታጥቀው ከላይ ወደ ተጠቀሱት ሥፍራዎች መግባት ካሰቡ በቅድሚያ የጦር መሳሪያውን ለተቋማቱ የጥበቃ ሠራተኞች ማስረከብ ግድ ነው።
የጦር መሳሪያ ፍቃድ የማይሰጣቸው ተቋማት:-
የፖለቲካ ፓርቲ፣
የሃይማኖትና የእምነት ተቋም፣
የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበር፣ እና
የትምህርት ተቋም ናቸው:: ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ለጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው የጦር መሳሪያ ውጪ ማንኛውም ዓይነት የጦር መሳሪያ ፍቃድ አይሰጣቸውም።
በልማድ ለታጠቁ የህብረተሰብ ክፍሎች የጦር መሳሪያ ፍቃድ ስለመስጠት:-
በተለምዶ የጦር መሳሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ እና የጦር መሳሪያ የያዙ ሰዎች፤ የያዙት የጦር መሳሪያ በዚህ አዋጅ ያልተከለከለ አይነት እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተቆጣጣሪው ተቋም በአካባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በአካል ቀርበው ፈቃድ ሲጠይቁ ለአንድ ሰው አንድ የጦር መሳሪያ ፈቃድ በዚህ አዋጅ መሰረት ይሰጠዋል ነው የተባለው። በተገለፀው ጊዜ ገደብ ውስጥ ፈቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ ለተቆጣጣሪው ተቋም ገቢ መደረግ አለበት፣ በቁጥጥር በተገኘም ጊዜ ይወረሳል።
የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም ሰው የፍቃዱ አገልግሎት ጊዜ ከማብቃቱ ከ60 ቀናት በፊት የእድሳት ጥያቄውን ለተቆጣጣሪው ተቋም ማቅረብ አለበት። ተቆጣጣሪው ተቋም ጥያቄው እንደቀረበለት በፍጥነት የፍቃድ መስጫ መስፈርቶቹ መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ፍቃዱን ያድሳል።
መሳሪያው ወንጀል የተፈፀመበት መሆኑ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ ወይም ባለፍቃዱ ይህን አዋጅ ተላልፎ ሲገኝ
ባለፍቃዱ ሲሞት፣ ያለበት አድራሻ ሳይታወቅ ሲቀር ወይም በፍርድ ወይም በሕግ ችሎታውን ሲያጣ፣
የጦር መሳሪያው በተለያዩ ምክንያቶች ከባለቤቱ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ሲታወቅ መሣሪያው እንዲወረስ ይደረጋል::
በአዋጁ መሠረት ፍቃድ የተሰጠው ማንኛውም የጦር መሳሪያውን ሲይዝ የፍቃድ ወረቀቱን አብሮ የመያዝ፣ ፍቃድ ካገኘበት የጥይት መጠን በላይ በአንድ ጊዜ አለመያዝ፣ የሚቻል እስከሆነ ድረስ የጦር መሳሪያው በግልፅ ሊታይ በማይችል ሁኔታ መያዝ፣ የጦር መሳሪያው ሲበላሽ፣ ሲጠፋ፤ ሲሰረቅ፣ ሲቀማ ወይም በማንኛውም ምክንያት ከቁጥጥሩ ውጪ ሲሆን ለተቆጣጣሪው ተቋም ወዲያውኑ ማሳወቅ፣ የጦር መሳሪያ በማናቸውም መልኩ ለሌላ አሳልፎ ያለመስጠት ግዴታዎች ይኖርበታል::
ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት አስጊ ሆኖ የተገኘን ማንኛውንም ፍቃድ ያለውንም ሆነ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቀን ሰው ያስፈታል፤ ይወርሳል አዋጁ። መንግሥታዊ ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም አማካኝነት በዚህ አዋጅ መሰረት የጦር መሳሪያዎችን ከውጪ ሀገር ማስገባት፣ ማከማቸት፣ ማዘዋወር፣ መሸጥ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ፍቃድ ይሰጣል።
የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 481 የተጠበቀ ሆኖ፤ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተውን ክልከላ እና ግዴታ የተላለፈ ከአንድ አመት እስከ ሦስት ዓመታት በሚደርስ ቀላል እስራት እና ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መጠን ይቀጣል።
የተፈጸመው ወንጀል ብዛት ባለው የጦር መሳሪያ ሲሆን ቅጣቱ ከአምስት አመት እስከ አስራ አምስት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሀምሳ ሺህ እስከ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ከፍ ይላል። በሕጋዊ መንገድ ያገኘውን የጦር መሳሪያ የሸጠ በማስያዣነት የተጠቀመ፣ ያከራየ ወይም በውሰት ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፈ ማንኛውም ሰው ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣም አዋጁ ደንግጓል።
ኒልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ የጎበኙትን ቦታ ለማልማት መታሰቡን ዶ/ር ዐቢይ ተናገሩ
ብልፅግና ፓርቲ በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለአህጉሪቱ እድገት ከኤ ኤን ሲ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ገለፁ
በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ (ኤ.ኤን.ሲ) 108ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ተካፋይ ሆነዋል።
ክብረ በዓሉ በኪምበርሊ የተካሄደ ሲሆን የኤ ኤን ሲ እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በብልፅግና ፓርቲ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁመልዕክት በማስተላለፍ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ አፍሪካውያን የላኩትን ሰላምታ አቅርበዋል። በዚሁ ወቅት ኤ ኤን ሲ ትውልዶች እየተቀባበሉ የገነቡት ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው ደቡብ አፍሪካውያን አፓርታይድ እንዲያበቃ ያደረጉትን ትግል ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ እንደሚያደንቁ እንዲሁም ፤ በኤ ኤን ሲ አመራርም ደቡብ አፍሪካ የበለጠ እኩልነት የሰፈነባት እና የበለፀገች ሀገር እንደምትሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ግንኙት ከበርካታ አስርት ዓመታት በፊት በዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት መጀመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ በሚያደርጓቸው ታሪኮች የተሳሰሩ መሆናቸውንም መስክረዋል።በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ እንደ አገራቸው እየኖሩ መሆኑን እና ደቡብ አፍሪካ ለዚህ እንግዳ ተቀባይነቷ እና ለኢትዮጵያውያን በራፏን በመክፈቷ እናመሰግናለን ሲሉም ተደምጠዋል።
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በማንሳት ፣ ስለ ኢትዮጵያ የተናገሯቸውን በማስታወስ ኢትዮጵያ ዛሬም ማንዴላ ለታገሉለት ነፃነት እና ሰብዓዊነት እንደምትቆም አብስረዋል። ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ የቆዩበትን ስፍራ ታሪካዊነቱ ተጠብቆ ሁለቱ አገራት በጋራ እንዲያለሙትም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፓርቲያቸው ብልፅግና ፓርቲ በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ብሎም ለአህጉሪቱ ብልፅግና ከኤ ኤን ሲ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ ነው በሀገሪቱ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመሪዎች ደረጃ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የደቡብ አፍሪካ መንግስት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በነገው እለት በጆሃንስበርግ በስቴዲየም ከህዝቡ ጋር እንዲገናኙ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በቡሌ ሆራና ሀዋሳ ሦስት ተማሪዎች ሲገደሉ ስምንቱ ደግሞ በጥይት ተመተዋል
በዮንቨርስቲዎች በኩል በህገ ወጦች ላይ እርምጃ ቢወሰድም ግድያና ጥቃቶች ሊቆሙ አልቻለም:: ትናንት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተቀሰቀሰ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ሲያልፍ ፣ በርካቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የዩኒቨርሲቲው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሰይፉ አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉም ታውቋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ተማሪዎች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭት የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አርማየም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊዋ በዩኒቨርሲቲው ግጭት አለመኖሩን ገልፀው፤ ከትናንት በስቲያ አመሻሹ ላይ ሱራፌል ሳሙኤል የተባለ የአንደኛ ዓመት ተማሪ በተማሪዎች ማደሪያ ኮሪደር ላይ ወድቆ መገኘቱን ካለመሸሸጋቸው ባሻገር ፤ “ተማሪው በተገኘ ሰዓት ደም እየፈሰሰው ነበር። ወዲያውኑ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተወሰደ፤ ነገር ግን በጣም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም” በማለት ክስተቱን አብራርተዋል።
ተማሪው በስለት የመወጋት አደጋ እንዳጋጠመው የጠቆሙት አመራር፤ ለተጨማሪ ምርመራ አስክሬኑ ወደ ሚንሊክ ሆስፒታል መላኩን እንዲሁም ከተማሪው ሞት ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ወደ 44 የሚደርሱ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ገልጸዋል። ሟች ተማሪ፤ የእርሱ የዶርም ልጅ ከነበረና አሁን ተጠርጥሮ በተያዘ ተማሪ መካከል የግል ግጭት እንደነበራቸውም አክለዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወዲህ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት መቋረጡን በማስመልከት የቡሌ ሆራ ዮንቨርስቲ ተማሪዎች ጠዋት 2፡30 አካባቢ ሰልፍ እንደወጡ ተማሪዎች ይናገራሉ:: ሰልፉ ሰላማዊ ነበር።
ይሁን እንጅ የዩኒቨርሲቲ ግቢ ፖሊሶች “ቀጠቀጡን” ያለ የቡሌ ሆራ ዮንቨርስቲ ተማሪ በዚህም ስምንት ሰዎች በጥይት ሲመቱ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን ለቢቢሲ ይፋ አድርጓል።
ሕይወቱ ያለፈው ተማሪ በጥይት የተመታው በግቢው ‘ዲኤስቲቪ’ የሚባል አካባቢ ነው በማለት የተናገረው ተማሪ
“ተተኩሶብናል፤ የግቢው ፖሊስ መሳሪያ ይዞ ባይረብሽ በሰላም ወጥተን በሰላም እንገባ ነበር” ከማለቱ በተጨማሪበዱላ እና በጥይት ጉዳት የደረሰባቸውም በርካቶች እንደሆኑ ገልጿል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሰይፉ፤ በግጭቱ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን እና አንድ ተማሪ በጥይት እግሩ ላይ ተመትቶ ወደ ሃዋሳ ሆስፒታል ተልኳል ብለዋል። ተማሪዎቹ በአራቱ የወለጋ ዞኖች ለምን የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት ተቋረጠ፣ ለምን በኮማንድ ፖስት ሥር ሆነ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው እንደነበርም ገልፀዋል።
ዳይሬክተሩ ተማሪዎች ሰላማዊ አካሄድ አልነበራቸውም፤ ድንጋይ መወርወር፣ መስታወቶችን መሰባበር ላይ ነበሩ ሲሉ ይከሳሉ። “ተማሪ ላይ አልተተኮሰም ፤ ወደ ላይ ነበር ሲተኮስ የነበረው፤ በተማሪ ጀርባ የገባ እና በተማሪዎች ውስጥ ሆኖ የሚተኩስ አካል እንደነበር ነው የፀጥታ አካላት እየገለፁ ያሉት” ሲሉም መረጃውን አጣጥለዋል።
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲም እንዲሁ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን ችግር በመቃወም ከትናንት በስቲያ ምሽት በተነሳ ግጭት በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። ይህንን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ባላቸው 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተማሪዎች ሁለቱ ከትምህርታቸው ሲሰናበቱ፤ 75 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል ከትምህርታቸው ታግደዋል። በቅርቡ የጅማ፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋት ተሳትፎ ነበራቸው ባሏቸው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።
የአፋርና አማራ ክልል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በሰመራ ተጀመረ
የአፋርና አማራ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ዛሬ በሰመራ ከተማ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ “የአፋር እና የአማራ ሕዝቦች ሥነ ልቦናዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ጅማሮ ከሉሲ ዘመን ይቀድማል” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አብሮ በሚኖር ማኅበረሰብ ቀርቶ በቤተሰብ ውስጥ እንኳን ግጭት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማመላከት አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶች እንደነበሩ አስታውሰው ፤ ግጭቶችን በማኅበራዊ መስተጋብሮቹ የመፍታት አቅም ያላቸው ህዝቦች እንደመሆናቸው የአሁኑ የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት መድረክ ዓላማው ይህንኑ ማጠናከር እንደሆነም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ በበኩላቸው “መልከ ብዙ ችግሮቻችን እየፈታን እና የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እየሞላን ከቀጠልን የማንወጣው ፈተና፣ የማናልፈው መሰናክል እና የማይናድ የጥላቻ ግንብ አይኖርም” ሲሊ በጉባዔው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቱ የተለያዩ ጥናተዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ለሁለት ቀናት ይቀጥላል።