ዩኒቨርሲቲ ምንድን ነው? || መስፍን ወልደ ማርያም

ዩኒቨርሲቲ ምንድን ነው? || መስፍን ወልደ ማርያም

( ይህ ጽሑፍ ከተጻፈ ወደ ሃምሳ ዓመታት ይጠጋል )

|| ከፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ብሎግ የተወሰደ||

የዚህ አጭር ጽሑፍ ርዕስ የሚያቀርበው ጥያቄ ለብዙ ሰዎች ቀላል መስሎ ይታይ ይሆናል፡፡ ግን በጣም ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ሊቃውንትም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በየዘመኑ ታላላቅ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ በዘመናችንም ቢሆን ክርክሩ በጋለ መንፈስ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግን ዩኒቨርሲቲ የሚለው ቃል አዲስና የውጭ ቃል ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ የሚለው ቃል ያለው ትርጉምና ያዘለው መንፈስ ግን ለኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ባዕድ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡ ይህንን በኋላ እንነጋገርበታለን፡፡

ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኋላ የሚደረስበት የትምህርት ደረጃ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የትምህርት ቤት ነው ማለቱ አይበቃም፡፡ እንዲያውም ሊያሳስት ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትን ወይም የሒልተን ሆቴልን ለአላያቸው የገጠር ነዋሪ ትልልቅ ቤቶች ናቸው ብሎ መግለጹ እነዚህ ሕንፃዎች በዓይነታቸው የገጠሩ ነዋሪ ከሚያውቃቸው ቤቶች ፍጹም የተለዩ መሆናቸውን አያስረዳውም፡፡ መገመት የሚችለው የሚያውቀውንና ያየውን ተመርኩዞ በመሆኑ ትልቅ ቤት ማለት እሱ በባላገር ውስጥ ከአያቸው ቤቶች ከፍና ሰፋ ብለው የሚታዩ ይመስሉታል፡፡ ዩኒቨርሲቲንም ከፍተኛ ትምህርት ቤት ስንለው በዓይነቱ ከአንደኛና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ለመረዳት አንችልም፡፡ በአንደኛ ክፍል የአለውንም ፊደል ቆጣሪ በዩኒቨርሲቲም ውስጥ በልዩ ጥናት ላይ የሚገኘውን ጎልማሳ በአማርኛ ተማሪ እያልን እንጠራቸዋለን፡፡ እንደዚሁም ፊደል የሚያስቆጥሩትንና በዩኒቨርሲቲም ውስጥ የሚያስጠኑትን አስተማሪዎች እንላቸዋለን፡፡ ፊደል መቁጠሩም ትምህርት ነው፤ በዩኒቨርሲቲም የአለው ጥናት ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህም ለሁለት ልዩ ልዩ ተግባሮችና ሁናቴዎች በአንድ ቃል መጠቀማችን የአለውን ትልቅ ልዩነት ይሰውርብናል፡፡

በዩኒቨርሲቲ የሚገኙት አሁን ተማሪዎች የምንላቸው ሰዎች በዕድሜ የጐለመሱ፣ በአእምሮ የበሰሉ ከመሆናቸው የተነሣ በገዛ ራሳቸው ለመሥራት፣ለማሰብና ለመመራመር የሚችሉ ናቸው፡፡

ተማሪዎች በማለት ፈንታ አጥኚዎች ልንላቸው ይገባል፡፡ በማሰብና በመሥራት፣ በመመራመርና በመከራከር የአእምሮአቸውን ችሎታ የሚያጠነክሩ፣ አስተሳሰባቸውን የሚያቃኑ፣ ለሥራ ያላቸውን ፍቅር የሚያጸኑ ሰዎች ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ራሳቸውን ለመቻል የተዘጋጁ በአእምሮ ኃይል የሚያምኑና በተራቀቀ መንገድ ለማሰብ የሚችሉ ሰዎች ናቸው ብለን ተስፋ እናደርግባቸዋለን፡፡ በአካባቢአቸው ያለውን ማናቸውንም ነገር፣ ልማዱን፣ እምነቱን፣ ወጉንና ሥርዓቱን፣ የኑሮን ትግልና ችግር ለመጠየቅና ለመመርመር የሚደፍሩ ሰዎች እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ በጭፍን የሚታመነውን፣ በጭፍን የሚነገረውንና በጭፍን የሚሠራውን በአእምሮ ብርሃን፣ በእውቀት ፋና፣ በጥበባዊ የምርምር ዘዴ የሚጠያቀቁና የሚመራመሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ጥረቱ ሁሉ እነዚህ ሰዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ በማናቸውም የሕይወት ረድፍ መሪዎችና አገልጋዮች ለመሆን የሚያስችላቸውን የተሻለ አእምሮ፣ የጠራ ኀሊናና ብሩኀ ዓይነ-ልቡና ያገኛሉ ተብሎ ነው፡፡ በየዕውቀት ረድፋቸው የሰውን ልጅ ኑሮ ለማሻሻልና እውቀትን ለማስፋፋት የሚጥሩ ሰዎች የማንም አገርና መንግሥት ምሰሶዎች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከሌሉት አንድ ኀብረተ-ሰብ የሚያስፈልገውን ንቅናቄ ሊያደርግና ሊሻሻል አይችልም፡፡

የእውቀትንና የጥበብን ተፈላጊነት ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ንግሥት ሳባ በሚጥም ቋንቋ ገልጻው በክብረ ነገሥታችን ተጽፎ ሲነበብ ቆይቶአል፡፡ ባሕር አቋርጣ ወደማታውቀው አገር ለመሄድና ከንጉሥ ሰሎሞን ጋር ለመገናኘት የገፋፋት ለእውቀትና ለጥበብ የነበራት ኃይለኛ ፍቅር ነው፡፡

አንሰ እፈቅድ ጠበበ ወልብ የኒ ተኀሥሣ ለአእምሮ፣ እስመ ተነደፍኩ በፍቅረ ጥበብ ወተሰሕብኩ በአሕባለ አእምሮ፤ እስመ ትሄይስ ጥበብአመዝገበ ወርቅ ወብሩር፣ ጥበብስ ትሄይስ ኧምነ ኩሉ ዘተፈጥረ ዲስ ምድር፡፡ … ወመንግሥትቸኒ ኢይቀውም ዘእንበለ ጥበብ ወብዕልኒ ኢይ ትዐቀብ ዘእንበለ ጥበብ ወአገርኒ ኢይጸንኅ ኀበ ኬደ ዘእንበለ ጥበብ ወልሳንኒ ኢይትፈቀር ዘ ተናገረ ዘእንበለ ጥበብ፡፡

ክብረ በነገሥቱ እንደሚነግረን ንግሥት ሳባ ወደኢየሩሳሌም የሄደችው እንደዚህ ዓይነቱ የጥበብና የእውቀት ፍቅር ገፋፍቶአት ነው፡፡ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በዚች በኢትዮጵያ ንግሥት ላይ ያደረው የእውቀት ፍቅር በሌሎቹም ነገሥታትና በሕዝቡም ላይ ቢያድር ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የትና የት በደረሰች ነበር፡፡

በመሠረቱም ዩኒቨርሲቲ እንደንግሥት ሳባ የጥበብና የእውቀት ፍቅር ያደረባቸው ሰዎች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ አእምሮ የሚሳልበት፣ ኀሊና የሚጣራበትና ዓይነ ልቡና የሚብራራበት እንደደብር ያለ ቅዱስ ቦታ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማንም ሰው በአካላዊ ኃይል ወይም በጡንቻ እንዲጠቀም የማይፈቅድበት፣ ሰው ሁሉ በአስተሳሰብ በሕግና በማስረጃ ብርታት የሚመራበት፣ በሥራው ውጤትና ጥራት የሚመዘንበትና የሚከበርበት፣ ሁሉም ሥራዬ ብሎ እውነትንና ፍትሕን የሚከታተልበት ዓለም ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፍርሃትና ይሉኝታ ሥፍራ የላቸውም፡፡ የማይጠረጠርና የማይጠየቅም ነገር የለም፡፡ ለጊዜው መልስ የማይገኝ መስሎ ቢታይም የማይጠየቀውን ለመጠየቅ፣ የማይጠረጠረውን ለመጠርጠር ደፋር አእምሮና ንጹህ ኀሊና ያሻል፡፡ዩኒቨርሲቲ ልዩ ዓለም ነው፡፡ እያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ አባል የተጣለበትን አደራ የሚፈጽመው ያለበትን ኃላፊነትና ግዴታ በመረዳት ነው እንጂ በተወሰነ የሥራ ሰዓት ቁጥጥር ውስጥ በመሆንና በበላይ ባለሥልጣን ፍራቻ አይደለም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለሥልጣን ማለት ለጥበብ፣ ለእውቀት፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ ማስረጃን የጨበጠ፣ በአእምሮው ኃይልና በኀሊናው ንጽሕና ጓደኞቹ ክብርን ያጐናጸፉት ነው፡፡

አእምሮና ኀሊና በትእዛዝ ይደርቃሉ እንጂ አይለመልሙም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ዓለም ውስጥ ፍርሃት የአእምሮ ድርቀት ምክንያት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሰው ሁሉ ከፍርሃት ነፃ ሆኖ አእምሮው ያሳሰበውንና ኀሊናው ያመዛዘነውን ለመናገር፣ ለመጻፍና ለማሳተም መቻል አለበት፡፡ አእምሮ እንዲበለጽግ፣ እውቀት እንዲስፋፋ፣ ጥበብ እንዲያፈራ፣ አንዱ ትውልድ በሌላው ትውልድ እየተሻሻለና እየታደሰ እንዲሄድ ለሚፈልግ ሕዝብና መንግሥት ልዩ የአእምሮ ነፃነት ያላቸው ሰዎች በግድ ያስፈልጉታል፡፡ አእምሮ በፍርሃት ከታፈነና ኀሊና በጥቅም ከተሸጠ ዩኒቨርሲቲ የሚባለው መንፈሱን፣ ነፍሱን፣ ሕይወቱን እንዳጣ በድን የሚቆጠር ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ልዩ የአእምሮ ነፃነት የዩኒቨርሲቲ ነፍስ ነው፡፡ ያለዚህ ነፃነት ዩኒቨርሲቲ ሕይወት አግኝቶ ለመንቀሳቀስና ተግባሩን ለመፈፀም አይችልም፡፡ ሀሳብ ከሀሳብ ጋር እየተፋጨ አዲስ ሀሳብ እንዲፈጠር፣ አዲስ ዕውቀት ከአሮጌው ዕውቀት ጋር እየተጋጨ አዲስ የሥራ ዘዴ ወይም ጥበብ እንዲገለጥ፣ አዲስ መንፈስ ከአሮጌው መንፈስ ጋር ፊት ለፊት እየገጠመ ሕይወት እንዲታደስ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ያስፈልጋል፡፡ ማጥናትና መመራመር እውነትን ለመፈለግ፣ ዕውቀትን ለማስፋፋትና ጥበብን ለማዳበር ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚካሄደው ጥናትና ምርምር የአንድ ሰውን ሕይወት ብቻ ለመለወጥ አይደለም፡፡ አካባቢውን፣ የአገሩን ሕዝብ በሙሉ፣ አንዳንዴም ዓለምን በሙሉ የሚነካ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ያሻል፡፡ ይህ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ሦስት ዋና ዋና ዘርፎች አሉት፡- አንደኛው የንግግር ነፃነት ነው፤ ሁለተኛው የመጻፍና የማሳተም ነፃነት ነው፤ ሦስተኛው የድርጅትና የማኀበር ማቋቋም ነፃነት ነው፡፡ እውነቱን ከውሸቱ፣ ክፉውን ከበጎው፣ ድርጊቱን ከግል አስተያየት፣ እምነትን ከእውቀት፣ ፍሬውን ከገለባው እየለዩ ለማጥናትና ለመመራመር የሚቻለው፣ አዲስ ሀሳብ የሚፈተነውና በመነቃቀፍ የሚታረመው፣ ዕውቀት የሚሰራጨው የአእምሮ ነፃነት ሲኖር ነው፡፡ አዲስ ሀሳብ አዲስ ኃይል በመሆኑ ጊዜው ኃይልና ሥልጣን የሰጣቸው ሰዎች የግል ጥቅማቸውን በሚከላከሉት ጠባብ አስተያየታቸው የአእምሮ ነፃነት ለኀብረተሰቡ በጠቅላላ የሚሰጠውን ጥቅም እንዳያዩ ዓይናቸውን ይጋርዱታል፡፡ ካርል ማርክስ የሚባለው ፈላስፋ እንዲህ ይላል፤ “ነፃነት በጣም የሰውነት ባሕርይ መሆኑን የነፃነት ተቃዋሚዎች እንኳን ይረዱታል፡፡… ማንም ሰው ነፃነትን አይቃወምም፤ ቢበዛ የሚቃወመው የሌሎችን ሰዎች ነፃነት ነው፡፡”

በእውነቱ የነፃነትን አስፈላጊነት ለኢትዮጵያውያን ለማስረዳት ባሕር ተሻግሮ ፈላስፋ መዋስ አያሻም፡፡ የአእምሮ ነፃነትም ቢሆን ኢትዮጵያዊ መሠረት አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲም ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የዝብርቅርቅ ዘመን ስለሆነ ስምና ግብር መለየት ያቅተናል፡፡ ለምሳሌ፡- የኛው የራሳችን የሆነውን ጎፈሬ የአለመሠልጠን ምልክት መሰሉን በተውነውና በረሳነው በስንት ዓመት ጥቁር አሜሪካኖች ስሙን ለውጠው ሲያጌጡበት በማየታችን እኛም በክርስትና ስሙ “አፍሮ” ብለን እንደአዲስ ነገር ተቀብለነዋል፡፡ የሚያስደንቀውም ስሙ በመለወጡ ዋናው ጎፈሬ መሆኑን አለመረዳታችን ብቻ አይደለም፤ እንደባዕድ ነገር ተቆጥሮ መነቀፉ የባሰ ነው፡፡ እንዲሁም የዜማ ቤቱን፣ የመጽሐፍ ቤቱን፣ የቅኔ ቤቱን፣ ዩኒቨርሲቲ ብለው ቢያቀርቡልን በግብር አንድ መሆናቸውን እንድንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ የእኛዎቹ በጭራሽ ሃይማኖታዊ መሆናቸውና ወደዓለማዊው ትምህርት አለመግባታቸው የዩኒቨርሲቲ ግብራቸውን አይለውጠውም፡፡ የአውሮፓም ዩኒቨርሲቲዎች ሲጀምሩ ልክ እንደኛዎቹ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ነበሩ፤ ለውጡ ቀስ እያለ የመጣ ነው፡፡ ስለአእምሮ ነፃነትም ክብረ ነገሥት እንዲህ ይላል፡፡-

ኢኮነ ሠናየ ሐሚዩቱ ለንጉሥ እምሕዝብ አለ እምታሕቴሁእስመ ፍዳ ለእግዚአብሔር ውእቱ፣ ወባሕቱ ካህናትስ አምሳለ ነቢያት አሙንቱ ወባሕቱ ረድፋደ ይሄይሱ እምነቢያት እስመ ተውሀቦሙ ምሥጢራት ከመ ይኾንኑ ፀሐየ ጽድቅ፣ሱራፌል አለ ተፈጥሩ አምእሳት ዘኤይክሉ እኂዘ ምሥጢራቾ ዘእንበለ በጐጠጣት ለካህናትስ ስሙዬሙ ፀወ፤ ወዓዲ ለካህናት ስሙዬሙ ማኀቶተ፤ ካዕበ ስመዬሙ ብርሃኖ ለዓለም፤ ወካዕበ ስሙዩሙ ፀሐየ ዘያበርህ ጽልመት እንዘክርስቶስ ፀሐየ ጽድቅ ውስጥ አልባቢሆሙ ወካህንስ ዘቦቱ ልቡናይገሥይ ለንጉሥ በአንተ ምግባራቱ ዘርእየ፤ወዘኤርአየስእግዚአብሔር ይፈትን ወአልቦ ዘይወቅስ፡፡… ወአንተኒ ኦካህን ለእመ ርኢከ ዕውቀ ኀጢአተ ለብዕሴ ኢትኀፈር ገሥጾቶ ኤያፍርህክ ሰይፍ ወኢስደት፤… ወአንተኒ ገሥጾ ወመሀሮ ለዘይኤብስ፡፡ ²

ካህናት በባህላችን መምህራን ናቸው፤ ስለዚህም ክብረ ነገሥቱ ጨለማን የሚያስወግዱ የዓለም ብርሃን ይላቸዋል፡፡ ልቡና ያለው ካህን /መምህር ማለቱ ነው፤/ በአየውና በተመለከተው ነገር ንጉሥንም ይገሥጻል፡፡ ስሕተትን ለማረም ስደትም ሆነ ሠይፍ ሳያስፈራህ ተናገር ይላል፡፡ ምዕራባውያን የአእምሮ ነፃነት የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡

ለመማር፣ ለማደግና ለመሻሻል የሚፈልግ ሰው የነገሩትን ሁሉ፣ ያነበበውን ሁሉ እንደመምጠጫ ሳይቀበል፣ በገዛ አእምሮውና በገዛ ኀሊናው አብላልቶ፣ አመዛዝኖና አንጥሮ እውነቱን ከውሸቱ፣ በጎውን ከክፉው እየለየ የሚያስብ ነው፡፡ የዛሬ ሦስት መቶ ዓመት ግድም የነበረ ወልደ ሕይወት የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ እንዲህ ይላል፡፡-

ወአንተስ ለእመ ሐተትኮሙ ለመጻሕፍት ፍጡነረክበ ስሙ ጥበብ እሱም ዘኤይስነዐው ምስለ ልቡና ዘወሀበነ እግዚአብሔር ለኃሢሠ ጽድቅ ወባሕቱ እንሰ ኤይብለከኩሉሙ ሰብአ ወኩሉሙ መጻሕፍት ይሔሰው ዘልፈ አላ አብላከ ይኮሉ የሐሰው ወደአንተዘ ኢተአምር ለአመይነቡ ጽድቀ ወሚመ ሐሰተ እንበለ ለሊከ ትሕትት ዘተ ብህለ ወዘተጽሐፈ ከመ ታአምር ጥዩቀ ዘይደልወደ ትአመን ወትለቡ ውስተ ግብረ እግዚአብሔር፡፡…እስመሐሰት ኢኮነ እምእግዚአብሔር አምላክ ጽድቅ፤… አላ እም ስሕተት እውአመጽልሑተ ሰብእ ውእቱ፡ ³

በዚህ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አስተሳሰብ እግዚአብሔር የሰጠንን የአአምሮና የኀሊና ሀብት ለመመራመርና እውነቱን ከውሸቱ ለመለየት ሳንጠቀምበት ብንቀር የእግዚአብሔርን ስጦታ አራክሰን ወደስሕተት እንወድቃለን፡፡ የእውነት አምላክ እግዚአብሔር፣ ይላል ፈላስፋው፣ የውሸት ምንጭ ሊሆን አይችልም፤ የውሸት ምንጮች ስሕተትና ሰውን መጥላት ናቸው፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ የሚባለውም የወልደ ሕይወት መምህር አስተሳሰቡ እንዲሁ ነበር፡፡

ዩኒቨርሲቲ የአእምሮና የኀሊና ባሕርይ ነው፤ ዩኒቨርሲቲ በመጠየቅና በመመራመር ውጤት የሚታይ ሥራ ነው፡፡ ይህ ባሕርይና ይህ ሥራ እንደጎፈሬ ወይም እንደሽሩባ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በእንጨትና በቅጠልም ቢሠራ፣ በጋዝም ሆነ በኮሬንቲ ቢሠራ የእንጀራ መጋገሪያ ከሆነ ምጣድ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች አፍሮ የሚሉትም ሌላ ስም ስላገኘ ጎፈሬነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን አይተውም፡፡ እንዲሁም የቅኔ ቤቱን፣ የዜማ ቤቱን፣ የመጻሕፍት ቤቱን አጠቃልለን ዩኒቨርሲቲ እያልን በውጭ ስሙ ብንጠራው ስሙ ባዕድ ስለሆነ ባሕርዩና ሥራውም ባዕድ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ከክብረ ነገሥት በትንሹ ጠቅሼ ለማስረዳት እንደሞከርሁትም የትምህርት፣ ማለት የአእምሮና የኀሊና ነፃነት ለኢትዮጵያ ከአሜሪካ የመጣ አዲስ ሀሳብ አይደለም፡፡ የቆየና ከአሜሪካም በፊት እኛው ዘንድ የነበረ ነው፡፡ ወደኋላ የቀረነውም የትምህርት ነፃነት ሀሳብ ባለመኖሩ ሳይሆን በሀሳቡ ሙሉ ኃይል ሳንጠቀምበት በመቅረታችን ነው፡፡ የትምህርት ነፃነት ኃይል ለትንሽ ልጅም እንኳን የሚገባ ቀላል ሀሳብ ነው፤ ይህ ማለት በትምህርት ስለት ያወጣውን አእምሮ ነፃነት መንፈግ ፍርሃትን የተመረኮዘ የግል ጥቅምን ብቻ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ የአንድ ሕዝብን የወደፊት ዕድል የሚቀጭ ጠባብ አስተያየት ነው፡፡ ለዚያውም ስለት የሚዶለዱመው ሲሠራበት ብቻ ነው፡፡

¹ እኔ ጥበብን እወዳለሁ፤ ልቤም እውቀትን ትሻለች፣ በጥበብ ፍቅር ተነድፌአለሁና በእውቀትም ገመድ ተስቤአለሁና ጥበብ ከወርቅና ከብር ክብር/መዝገብ/ ትበልጣለችና፡፡ ጥበብስ በምድር ላይ ከተፈጠረው ሁሉ ትበልጣለች፣ መንግሥትም ቢሆን አለጥበብ አይቆምም፣ሀብትም /ብዕል/ ያለጥበብ አይቆይም፣ አገርም በሄደበት ሁሉ አለ ጥበብ አይበረታም፣ አንደበትም አለጥበብ የተናገረው አይወደድለትም፡፡ክብረ ነገሥት፣ ምዕራፍ 24

² ፍርድ /ፍዳ/ የእግዚአብሔር ነውና ከታች ያለው ሕዝብ ንጉሥን ቢያማ ጥሩ አይደለም፡፡ ካህናት ግን የነቢያት አምሳል ናቸውና እንዲያውም የእውነትን ጸሐይ እንዲጠብቁ ኃላፊነት /ምሥጢራት/ ተሰጥቶአቸዋልና ከነቢያት ይበልጣሉ፡፡ ከእሳት የተፈጠሩት ሱራፌል በጉጠቶች ካልሆነ በቀር /ምሥጢራትን/ መያዝ አይችሉም፡፡ ካህናትንማ ጨው አደረጋቸው፣ አናት አደረጋቸው፣ የዓለም ብርሃን አደረጋቸው፣ የእውነት ጸሐይ የሆነው ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ አድሮአልና ጨለማን የሚያበራ ፀሐይ አደረጋቸው፡፡ ልቡና ያለውስ ካህን በአየው ሥራ ንጉሥንም ይገሥጻል፤ ያላየውንስ እግዚአብሔር ይመርምረው እንጂ እሱን የሚወቅሰው የለም፡፡… አንተስ ካህን ሆይ ያንድን ሰው ጥፋት በግልጽ ያየህ እንደሆነ ለመግሠጥ አትፍራ፣ ሰይፍም ሆነ ስደት አያስፈራህ፤የሚሳሳተውን ገሥጸህ አስተምረው፡፡ ምዕራፍ 49

³ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ፣ ሐተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ አክሱማዊ ወወልደ ሕይወት አንፍራዛዊ 1948 ዓ/ም. ገጽ 36

LEAVE A REPLY