አጼ ቴዎድሮስ አልሞቱም || ቴዲ – አትላንታ

አጼ ቴዎድሮስ አልሞቱም || ቴዲ – አትላንታ

የቴዎድሮስ ራዕይ ቲያትር በአሜሪካ ከተሞች በታየበት ወቅት በየከተማው ወረፋ ነበረ። በትንሽ ትልቁ፣ በሴቱ ወንዱ በተጋፍቶ ታየ። ትልቅ አገራዊ መልክት ያነገበ ቲያትር ነበር። በግራ ጆሮ የሰማነውን በቀኝ ካላወጣነው በቀር፣ በቲያትሩ በኩል የተላለፈው የአጼ ቴዎድሮስን መልክት ከልብ ሰምተን ቀይሮን ከሆነ ኢትዮጵያ ተስፋ አላት።

እኔ በግሌ አጼ ቴዎድሮስን እንግሊዞች አልገደሏቸውም፣ በእንግሊዞች ምክንያትም አልሞቱም እላለሁ። በጦርሜዳ ፣ በጠላት ፊት እጅ አልሰጥም ብሎ መሞት እኮ ለኛ አገር አርበኞች ብርቅ አይደለም። ያ ደግሞ ሞቱ ብለን የምንቆጭበት አይደለም። አጼ ቴዎድሮስ ለምን ሞቱ፣ ራዕያቸውስ ምን ነበረ? ብለን ብንጠይቅ መልሱን እናገኘዋለን።

የተበታተነችውን ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ ሞቱ። ከግራ ሲሰፉት ከቀኝ እየተተረተረ ቢያስቸግራቸው ቁጡ ሆኑ። እሽኮኮ አርጉኝ፣ መቶ ዓመት ልግዛችሁ አላሉም። አገራቸውን በሥልጣኔ ለማበልጸግ፣ ይበልጡኑም ደግሞ፣ በዘመነ መሳፍንት የተበታተነውን አገር፣ በአንድ አስተዳደር ስር፣ የጎሳና የዘር ሽኩቻ ሳይኖር፣ ሁሉም እኩል ሆኖ ተከባብሮ፣ አንተ የጳውሎስ ነህ፣ አንተ የጴጥሮስ ነህ መባባል ሳይኖር፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ፣ አንዷን ኢትዮጵያ አገሬ ብሎ እንዲጠብቅና እንዲያበለጽግ ለፍተው፣ በክብር አረፉ።

በዛሬው ቀን የተወለዱበት 201ኛ ዓመት ይታሰባል። ህይወታቸው ካለፈ ደግሞ 151 ዓመት። እሳቸው እንደተመኙት፣ እንደታገሉለት እና እንደፈለጉት በጎሳና በመንደር ሳንከፋፈል ኢትዮጵያን አንድ አርገን፣ እኛም አንድ ሆነን ከቆየናቸው አጼ ቴዎድሮስ አልሞቱም። ሁሉም ለጎጡ ሳይሆን “ለኢትዮጵያ” የሚል ራዕይ ካለው አጼ ቴዎድሮስ አልሞቱም።

አጼ ቴዎድሮስ ለመኖር ለመኖር አንድ ቁራጭ ዳቦ እና አንዲት ጣሳ ውሃ ይበቃቸው ነበር። አገራቸው ተበታትና በማየታቸው ተቆጭተው በሃይልና በጉልበት ሲነሱ፣ የተመኙት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ቁጡ ፣ ጨካኝ ሆኑ የሚያስብል ሥራም አይሰሩም ነበር፣ እንግሊዝ ቢመጣም እንኳን ቢቻል በዘዴ፣ ባይቻል ደግሞ ሁሉም አግዟቸው ሊመልሱት ይችሉ ነበር። ሲሞቱ ያሰቡት፣ ያሰቡት እንዳልሆነ አውቀው ነበር። ዛሬ በመንፈስ ሲያዩን እንዲሁ በዘርና በጎሳ እየተባላን፣ እየተቧጨቅን እና ሁሉም በጎሳው ስም ያጠረውን ቦታ ብቻ አትንኩብኝ የሚል መሆኑን ሲያዩ ሞታቸውን ሊመርጡ ይችላሉ።

የሳቸውን ራዕይ ማሳካት ካልቻልን ደግሞ፣ በየቀኑ እንደአዲስ እየገደልናቸው ነው። በእንግሊዝ ማሳበባችንን እናቁም። የዛሬ ሥራችንን እና የሳቸውን ራዕይ ልዩነት ማየት ከቻልን፣ የገደልናቸውና እየገደልናቸውም ያለነው እኛው መሆናችንን ማሰብ አያስቸግርም።

ስልሳ እና ሰባ ዓመት ብቻ እንደምንኖር እየታወቀ፣ ልክ ዘላለም የምንኖር ያህል ስንፋጭና ርስ በርስ ስንናከስ፣ የጎሳ ፓርቲ ፈጥረን፣ የጎሳ ድርጅት መስርተን በጎሳችን ሥር ተወሽቀን፣ በጎን ደግሞ የአጼ ቴዎድሮስን ፎቶ ይዘን በቴዲ አፍሮ “ካሳ – የቋራው አንበሳ” ብንጨፍር ትዝብቱ ለራሳችን ነው።

ግን ሁሉን ለመቀየርና አዲስ ታሪክ ለመጻፍ፣ አጼ ቴዎድሮስንም ከመቃብር ለማንሳት ጊዜ አለን። ከመንደር እና ከጎሳ ፖሊቲካ እንውጣ። ለአጼ ቴዎድሮስ ነፍስ ረፍትና እፎይታ የምንሰጠው ያን ጊዜ ነው።

LEAVE A REPLY