“አፍቃሪ ህወሓት” ጋዜጠኞቹ የታሰሩት የፍቃድ ደብዳቤ ባለማግኘታቸው ነው ተባለ
ሁለት የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ጋዜጠኞች ለሥራ በተጓዙበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለእስር መዳረጋቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።ለእስር የተዳረጉት የአማርኛ ክፍል ባልደረቦች ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እና የካሜራ ባለሙያው በኃይሉ ውቤ ናቸው።
ኤጀንሲው በአሶሳ ከተማ በሚካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ላይ ሽፋን እንዲሰጥ በቀረበለት ጥሪ መሠረት ፤ ሁለቱ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው መላካቸውን የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ በቀለ ይናገራሉ።
“ጋዜጠኞቹ ቅዳሜ ዕለት ነው የሄዱት፤ እሁድና ትናንት ሲዘግቡ ውለው፤ ትናንት ጥር 4/2012 ዓ.ም ምሽት 3፡00 አካባቢ ካረፉበት ሆቴል ፖሊሶች መጥተው ወሰዷቸው” በማለትም የተያዙበትን ሁኔታ ገልጸዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ አበራ ባየታ በአሶሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በኩል የተያዙ ጋዜጠኞች መኖራቸውን አረጋግጠው፤ የተያዙበትን ዝርዝር ምክንያት ግን እንደማያውቁ ነው የተናገሩት።
የአሶሳ ከተማ አስተዳዳር ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ ዋና ኢንስፔክተር እስማኤል አስፒክ በበኩላቸው “ጋዜጠኞቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደብዳቤ ይዘው ስላልተገኙ ነው” ብለዋል። ዋና ኢንስፔክተር እስማኤል፤ ሁለቱ ጋዜጠኞች የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትን ለመዘገብ ከኤጀንሲው አዲስ አበባ ቅርንጫፍ መላካቸውን እንደነገሯቸው ጠቅሰው፤ ጋዜጠኞቹ ወደ አሶሳ ሲመጡ ደብዳቤ ባለመያዛቸው እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለ ሁለቱ ጋዜጠኞች ወደ ክልሉ መምጣት የሚያውቀው ነገር ባለመኖሩ መታሰራቸውን አረጋግጠዋል።
ጋዜጠኞቹ መጡበት ወደተባለው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢደውሉም ገና ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ ስለ ጉዳዩ መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና ወደ ከተማው ፖሊስ በተደጋጋሚ ቢደውሉም ማብራሪያ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል። ጉዳዩንም ለክልሉ መንግሥት እንዳሳወቁና የክልሉ መንግሥት እየተከታተለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ጋዜጠኞች በመሆናቸው ያለ ደብዳቤ በመታወቂያ መሥራትና በነፃነት መንቀሳቀስ አይችሉም ወይ? ለሚለው ጥያቄም ኢንስፔክተሩ፤ “አሠራሩ እንደዚያ ነው፤ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ለአንድ ሥራ ወደ አንድ ቦታ የተንቀሳቀሰ ሰው ‘ፈለሥራ ጉዳይ ነው የመጣው የሚል ደብዳቤ መያዝ አለበት ነው የሚለው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በጉዳዩ ላይ ከመገናኛ ብዙኃኑ ጋር ያደረጉት የመረጃ ልውውጥ ስለመኖሩ የተጠየቁት ዋና ኢንስቴክተሩ፤ ፖሊስ ኮሚሽን ከትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ ካለው ቅርንጫፍ ጋር በጉዳዩ ላይ በስልክ እየተነጋገረ መሆኑን አስረድተዋል:: በአሶሳ ትናንት ማምሻውን የተያዙት ዳዊት ከበደና በኃይሉ ውቤ በበርካታ እውነተኛ ጋዜጠኞች “አፍቃሪ ህወሓት ወሬ አቀባዮች” በሚል የሚታሙ ከመንበረ ሥልጣኑ የተገፋው የወያኔ ቡድን ታማኝ በመሆን ለዓመታት በርካታ የሀሰት ዜናና ትርክቶችን ሲያቀርቡ የቆዮ ናቸው።
አስከሬን አስቆፍራ ያስወጣችው አማኝ 2 ሺኅ ብር ብቻ ተቀጣች
በኦሮሚያ ክልል ቦሰት ወረዳ ፣ ወለንጪቲ ከተማ ከሞተ ሁለት ሳምንት የሆነውን የሁለት ወር ህፃን “ከሞት እንዳስነሳ ራዕይ ታይቶኛል” በማለት መቃብር ያስቆፈረችው አማኝ በማጭበርበር መቀጣቷ ታወቀ።
ህጻኑ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሞተ በኋላ ራዕይ ታይቶኛል ያለችው ሴት፤ የህጻኑን እናት እና አንዲት ሌላ ሴት በመያዝ ወደ መቃብር ሥፍራ በመሄድ፣ ቆፍረው ማውጣታቸውን የቦሰት ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ዋና አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ ደምሴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
”ግለሰቧ እንደ ለቅሶ ደራሽ በመሆን ወደ እናት ቤት በመሄድ ልጅሽ አልሞተም፤ በሕይወት ነው ያለው፤ ከሞት እንዳስነሳውም ራዕይ ታይቶኛል” በማለት መቃብር ሥፍራም ሄዳ ጸሎት ማድረግ እንደምትፈልግ ትነግራታለች። እናትም እውነት መስሏት ተያይዘው ወደ መቃብር ሥፍራው ሄደዋል።
መቃብር ሥፍራ ከደረሱ በኋላ ህጻኑን ቆፍራ አውጥታ እዛው ስትቀመጥ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተመልክተው ለፖሊስ ጥቆማ በማድረጋቸው ፖሊስ በቦታው ደርሶ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ኅብረተሰቡን አስተባብረው አስክሬኑ እንዲቀበር አድርገዋል ነው ያሉት ሓላፊው።
ፖሊስ ጉዳዩን ሲከታተለው ቆይቶ ግለሰቧ ለፈጸመችው ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርባ ተገቢውን ቅጣት እንዳገኘች ዋና ኢንስፔክተር ካሰኝ ደምሴ ገልጸዋል:: በብይኑ መሰረትም ጥፋተኛ መሆኑ ስለተረጋገጠ በ2000 ብር ተቀጥታለች ነው የተባለው።
አማኟ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላት ሓፊነት ምን ነበር? የተባሉት ኢንስፔክተሩ፤ ”ከታሪኳ እንደምንረዳው አማኝ ነች እንጂ፤ አገልጋይም ወይም ሌላ ነገርም አይደለችም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከተቀበረ ሁለት ሳምንታት የሞላውን ህጻን ፈጣሪ ራዕይ አሳይቶኛል በማለት አስክሬኑ ተቆፍሮ እንዲወጣ መደረጉ የአካባቢውን ነዋሪ በጣም ያስቆጣና የተከበረውን የመቃብር ቦታ ክብር የሚነካ እንደሆነ እየተገለጸ ነው። ፍርድ ካገኘችው ይህች ሴት በተጨማሪ እናት እና አማኟንይዛት የመጣች አንዲት ሌላ ሴት በወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን ሁለቱ ጥፋተኛ አለመሆናቸው ስለተረጋገጠ በነጻ መሰናበታቸውም ታውቋል።
እናት ለፖሊስ በሰጠችው ቃል እንደ ማንኛውም ለቅሶ የሚደርስ ሰው ወደ ቤት ከመጣች በኋላ ‘ራዕይ ታይቶኛል፤ ልጅሽን አስነሳለሁ’ ብላ በመጀመሪያ ቤት ውስጥ ጸሎት ካደረገች በኋላ ወደ መቃብር ሥፍራው ሄደን አስክሬኑን አወጣነው። ያው የእናት አንጀት ሆኖብኝ አመንኳት” ስትል ክስተቱን አስታውሳለች።
ራዕይ ታይቶኛል ያለችውን አማኝ ወደ ቤት ይዛት የመጣችው ሌላኛዋ ሴት ከልጁ አባት ጋር በአንድ መሥሪያ ቤት አብረው እንደሚሰሩም ያስረዱት ዋና ኢንስፔክተሩ ፤ አስክሬኑ ተቆፍሮ በወጣበት ወቅት “እንዴት አንድ ጤናማ ሰው ከተቀበረ ሁለት ሳምንት የሆነውን አስክሬን አውጥቶ፤ ይዞ ይቀመጣል?” በሚል የአካባቢው ነዋሪ በመረበሹ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበር ይፋ አድርገዋል።
የነበረከት ስምዖን መከላከያ ምስክሮች ቃል መሰማት ተጀመረ
የጥረት ኩባንያን ሀብት በማንአለብኝነት በማባከንና በሌብነት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው የነበረከት ስምዖን የመከላከያ ምስክሮች ቃል የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማድመጥ ጀመረ።
ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 30 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ዐቃቤ ህግ አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለተመሰረተባቸው ክስ ያቀረቧቸውን የመከላከያ ቃል ምስክሮች ለማዳመጥና የሰነድ ማስረጃዎች ለመመልከት ለጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም።
በወቅቱ ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎትም የተከሳሽ ጠበቆች በ4ቱ ክሶች አሉን ያሏቸውን የሰነድና 11 የቃል መከላከያ ምስክሮች አቅርበዋል። ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በተሰየመው ችሎት ደግሞ የተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች የምስክር ቃል ከማሠማታቸው በፊት ተከሳሾች የተከሰሱበትን ቃል በማቅረባቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹን ቃል ለማዳመጥ ተለዋጭ ለጥር 5 ቀን 2012ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎትም የተከሳሽ ጠበቆች አሉን ካሏቸው 11 የቃል ምስክሮች አራቱን ያቀረቡ ሲሆን ሦስቱ ግን ሊቀርቡላቸው እንዳልቻሉ አስረድተዋል። በዚህ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች ካቀረቧቸው አራት የቃል ምስክሮች ውስጥ የአንደኛውን ቃል አድምጧል።
የቃል ምስክሩ በደቨንቱስ ስማርት ሜትር የውሃና የመብራት ብክነት አቅርቦት መቆጣጠሪያ ሥራ መጀምር አስመልክቶ የምስክርነት ቃሉን አሰምቷል። የምስክርነት ቃሉን ያሰማው የመከላከያ ምስክር ፕሮጀክቱ ወደ ማምራት ስራ መግባቱን ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል ነው የተባለው።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ጀመረ የተባለው የደቨንቱስ የስማርት ሜትር በውሃና ኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ የጥረት ቦርድ ያልወሰነበት እና የጥራት ማረጋገጫ የለውም በማለት ተከራክሯል። የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤትም ቀጣይ የተከሳሽ ጠበቃ መስቀለኛ ጥያቄን ለመስማት ከሰዓት በኋላ ቀጠሮ በያዘው መሠረት የቀሪዎቹ ምስክሮች ቃልም ከሰዓት በኋላ መደመጡን የደረሰን መረጃ ያሳያል።
በርካታ የስልክ ገመዶችን (ኬብሎችን) የዘረፉተጠርጣሪዎች ተያዙ
የኢትዮ-ቴሌኮም ንብረት የሆኑ በርካታ የስልክ ገመዶች በስርቆት አከማችተው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ከመሬት ውስጥ ተቆፍረው የወጡ የስልክ ገመዶችን አከማችተው የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ ጋዝ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
በተጨማሪ መርካቶ ኢትዮጵያ ዳቦ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ተጠርጣሪ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ የኢትዮ ቴሌኮም ንበረት የሆኑ የስልክ ገመዶችን ቆፍሮ እያወጣና እየቆረጠ ሰርቆ ለመውሰድ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ይፋ አድርጓል:: በአሁኑ ወቅትም ወንጀሉን በፈጸሙት ተጠርጣሪዎ ች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ፖሊስ በማያያዝ ገልጿል።
በቅዱስ ጳውሎስ የመካንነት ሆስፒታል ጥንዶቹ ልጅ ለማግኘት በቁ
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነት ሕክምና ማዕከል ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ጥንዶች በተደረገላቸው ዘመነኛ ሕክምና ልጅ ማግኘታቸው ተሰማ።
ለሰባት ዓመታት በጋብቻ ሲኖሩ ልጅ ማፍራት ያልቻሉት ጥንዶቹ ፥ ሆስፒታሉ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ባስጀመረው የመካንነት ሕክምና ማዕከል በተደረገላቸው ክትትል የመጀመሪያ ልጃቸውን ማቀፍ ችለዋል። ጥንዶቹ ልጅ ማግኘት የቻሉት የኢንትሮ ቪትሮ ፈርትላይዜሽን በተባለ ህክምና ሲሆን ፤ በቀጣይ ወራቶች 70 የሚደርሱ እናቶችም በዚህ ሕክምና ልጃቸውን ያቅፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የመካንነት ችግር ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ ቢታመንም በተወሰነ መልኩ ምርመራዎችን ከማድረግ የዘለለ በበቂ ሁኔታ የሕክምና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል የተደራጀ የሕክምና ተቋም አልነበረም። ለዚህ ሕክምና በመንግሥት የጤና ተቋም ደረጃ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመጀመሪያው ነው።
ቀደም ሲል ብዙ ጥንዶች በከፍተኛ ወጪ ለሕክምናው ወደ ውጪ አገር ለመሄድ ይገደዳሉ:: በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይባክን ነበር። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሆስቲታሉ በአገር ውስጥ የማይገኙ ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ሆስፒታሉ አስታውቋል።