ከመቀሌ ወደ ሳምረ የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ 4 ቀን ቢሞላውም የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም
ከመቀሌ ከተማ ወደ ሳምረ የሚወስደው መንገድ ወረዳችን ይመለስልን በሚሉ የሕንጣሎ ነዋሪዎች ደንጎላት በሚባል አካባቢ ከተዘጋ አራተኛ ቀን ሞልተታል።
ሕንጣሎ ወጀራት ተብሎ ይጠራ የነበረው ወረዳ ለሁለት ተከፍሎ፤ ወጀራት ራሱን የቻለ ወረዳ ሲሆን፣ 11 ጣቢያዎች ያሉት ሕንጣሎ ደግሞ ሒዋነ ከምትባል ሌላ ወረዳ ጋር እንዲካተት ተደርጓል። ሒዋነ ከምትባለው ወረዳ ጋር እንዲቀላቀሉ የተደረጉት የሕንጣሎ ነዋሪች፤ እራሳችንን የቻለ ሕንጣሎ የተባለ ወረዳ ሊኖረን ይገባል እንጂ ከሒዋነ ወረዳ ጋር መቀላቀል የለብንም የሚል ቅሬታ አሰምተዋል።
ከነዋሪዎቹ እንደሰማነው አሁን በተጀመረው አዲስ የአስተዳደር መዋቅር፤ ወጀራት ከ1-9 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ሕንጣሎ ግን ሒዋነ ወደሚባል ወረዳ እንዲቀላቀል ተደርጓል። ነዋሪዎቹ የራሳችን ወረዳ ይኑረን፤ በቅርብ አገልግሎት እንድናገኝ ይሁን በማለት ነው። ምላሽ ካልተሰጠን ተቃውሟችን ይቀጥላል፤ ወደ ቤታችን አንመለስምም ብለዋል::
“የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ባመጣው አዲስ አሠራር ፤ ነዋሪዎች ከ10 ኪሎሜትር በላይ ርቀው መገልገል የለባቸውም ሲሉ ነበር። እኛ ግን አሁን ተባረን አገልግሎት ለማግኘት የምንጓዘው ትንሹ ርቀት 30 ኪሎ ሜትር ነው” በማለት አቋማቸውን ለቢቢሲ ያስረዱት የአካባቢው ነዋሪዎች ፤ መንገድ መዝጋት መፍትሄ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄም፤ “መንገድ መዝጋት ፍትሃዊ ባይሆንም ፍትህ ስላጣን ነው መንገድ የዘጋነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ከእኛ መካከልም መቀሌ መሄድ ያለባት አራስ አለች፤ ሕመምተኛ አለ፤ ነገር ግን መሠረታዊ ሕይወታችን አደጋ ላይ ስለወደቀ ነው ይህንን ጊዜያዊ ችግራችንን ብንቋቋም ይሻላል ያልነው። ወረዳችንን አሳልፎ ለሌላ መስጠት ተገቢ አይደለም” በማለት የሚከራከሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ኮሚቴ ወኪል አቶ ደሱ ጸጋዬ ይህንን ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ስድስት ወራት መቆጠራቸውን አስታውሰዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ቅሬታቸውን ለማቅረብ ያልሄዱበት፤ ያልደረሱበት ቦታ የለም። በወረዳ እና በዞን የሚገኙ የፍትሕም ሆነ የፀጥታ አካላትን ቢያዳርሱም ነገር ግን ያገኙት ምላሽ የለም። “እኛ መንግሥት በደነገገው ሕግ መሠረት ሁሉንም አሟልተናል። አንደኛ ከ115 ሺህ ሕዝብ በላይ ነን። ሁለተኛ መንግሥት ‘ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የወረዳ አገልግሎት ማግኘት የለበትም’ ነው የሚለው እኛ ግን ከ30 በላይ ኪሎ ሜትር በላይ ሄደን ነው ይህንን አገልግሎት የምናገኘው፤ ስለዚህ የልማት ጥያቄያችን እንዲመለስልን ነው የምንፈልገው” ሲሉ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ይህንን ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ መንፈቅ ቢሞላቸውም፤ የፖለቲካ አስተዳዳሪዎችን መልስ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም ጆሮ የሰጣቸው የለም። “በተቃራኒው በዞንና በወረዳ ፖሊስ አማካኝነት ያስፈራሩን ገቡ፤ ለተቃውሞ የወጡ ነዋሪዎችም መንገድ በመዝጋታቸው ወደ ገበያ የሚሄዱ ከብቶች ሳይቀሩ መንገድ ላይ ነው የዋሉት፤ መንገድ ዝግ ነው፤ ይሄው እንዲህ ከሆነ ቀናት ተቆጥረዋል” በማለትም ያለውን እውነታ በግልጽ አስቀምጠዋል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ መንገዱ በመዘጋቱ ከትናንት በስቲያ እስከ 150 የሚደርሱ መኪኖች መንገድ ላይ ሲጉላሉ እንደነበር ታውቋል።
የነዋሪዎቹን ጥያቄ አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል አማካሪ አቶ ተሾመ፤ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ተመልሷል ነው ያሉት። “ወረዳቸው ተመልሶላቸዋል፤ የእነርሱ ጥያቄ የወረዳው ዋና ከተማ ደንጎላት ትሁን ወይስ ሒዋነ የሚል ነው” በማለት ይህንን ጥያቄ የሚመልሰው ደግሞ የወረዳው ምክር ቤት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጥያቄያቸው አልተመለሰልንም የሚሉት ነዋሪዎች፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲያነጋግሯቸው ነው የሚፈልጉት ይህ ለምን አልሆነም? ለሚለውም “ዝም ተብሎ የሚመጣበት ቦታ አይደለም፤ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሌላ ሥራ ተጠምደዋል፤ በቀጠሮ ከመጣችሁ ትስተናገዳላችሁ አልናቸው፤ እንዴት እናድርግ? ” በማለትም ተከራክረዋል::
7ኛው የአድዋ የእግር ተጓዦች ዛሬ በአዲስ አበባ የአሸኛኘት ሥነሥርዓት ተደረገላቸው
በየዓመቱ ታላቁንና የአፍሪካ ኩራት የሆነውን የአደዋን በዓል ከአዲስ አበባ እስከ አደዋ በእግር በመጓዝ የሚያከብሩየአድዋ ተጓዦች የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ተካሄደላቸው።
ዛሬ (ቅዳሜ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደው የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የአድዋ ተጓዦች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ አባት እና እናት አርበኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታዳሚ መሆናቸውን በስፍራው የተገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ መረጃውን አድርሶናል።
በአሸኛኘት ስነ ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ “ስለ አድዋ ሳሰብ ስሜታዊ እሆናለሁ ፣ ያንንም ስሜት የፈጠረብኝ የአባቶቼ የማሸነፍ ስሜት ነው” ካሉ በኋላ የሚሰማኝም ስሜት የማሸነፍ እና ሁልጊዜ የመራመድ ስሜት ነው ሲሉ ለተጓዦቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“አባቶቻችን እና እናቶቻችን ከኢትዮጵያ ጫፍ ጫፍ ተነስተው በጀግንነት ለፈተና ሄደው ፈተናውን አሸነፉ ” ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፤ አሁን ወደ አድዋ ሲሄዱ ሰላምን እና አንድነትን ለመስበክ እንደሆነም ተናግረዋል። “ይሄኛው ፈተና ከባድ መሆኑን፤ መሞት ወይም መግደል ሳይሆን ልብን መማረክ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በጉዟቸው በሚረግጧቸው በእያንዳንዱን የኢትዮጵያ መሬት ፍቅር እና አንድነትን ስበኩ ብለዋል።
አድዋ ከማሸነፍ፣ ከሞመት እና ከመግደል ባለፈ አንድነት እና ፍቅር እንደሆነም ለዓለም አሳዩ በማለት በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ታከለ ኡማ ፤ የአድዋን ማእከል በአዲስ አበባ ከተማ የሁሉም ኢትዮጵያ ማእከል እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ያለውን ሀብት አሰባስቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን እንደሚያጠናቅቅም በይፋ አረጋግጠዋል።
በተግባር ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው
በሥራ ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በአዲስ ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሥራ ላይ ያለውን ስርዓተ-ትምህርት ለመቀየር የአስር ዓመታት ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱን በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጃጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ላይ አበራርተዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታት በአዲስ የሚተካው ስርዓተ-ትምህርት የተማሪዎችን ስነ-ምግባር ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ወርቁ ደግሞ ስርዓተ-ትምህርቱ እየተዘጋጀ ያለው ከፍኖተ ካርታው በተገኙ ምክረ ሃሳቦች መሆኑን ነው ያመላከቱት። በተጨማሪም የካንብሪጅ ኢንተርናሽናል ግምገማን ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች በተገኙ ምክረ ሃሳቦችና ተጨማሪ አስተያየት መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።
በዘርፉ በተዘጋጀ የባለሙያዎች ምክክር መድረክ ከአገሪቱ ሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች፣ የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅት ሓላፊዎች፣ ከሁለተኛና ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን፣ የመምህራን ኮሌጆችና ከአምስቱ የመምህራን ማሰልጠኛ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በአሜሪካ የሚኖሩ የጎንደር ተወላጆች በ20 ሚሊዮን ብር ፋሲለደስ ት/ቤትን ሊያስፋፉ ነው
በአሜሪካ የሚኖሩ የቀድሞ የፋሲለደስ ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትምህርት ቤቱን የመማሪያ ክፍል ጥበት ችግር ለመቅረፍ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ፤ ባለ ሁለት ደርብ ህንፃ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።
የመማሪያ ክፍል ህንፃ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ዝግጅት ላይ ተገልጿል።
የጎንደር- ፋሲለ ደስ ትምህርት ቤት በየጊዜው ካለው የኅብረተሰቡ የመማር ፍላጎትና ከተማሪዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በአንድ ክፍል 100 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር የተገደዱበት ሁኔታ በግልጽ ታይቷል።
ይህ ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን ጥራት ያጓደለው መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢቆይም መንግሥት እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ማሻሻያ ሳያደርግ ቆይቷል::
የዘንድሮውን የጥምቀትን በዓል ለማክበር የመጡት የቀድሞ ተማሪዎችና ተወላጆች በዓሉን በትውልድ ስፍራቸው ለማክበር ከማሰባቸው ባሻገር የፋሲል ከፍተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤትን ማስፋፊያ ድጋፍ ለማድረግ በመዘጋጀታቸውተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ግንባታውን በይፋ አስጀምረዋል።
በጊነስ ቡክ ላይ የሰፈረው የዓለም አጭሩ ሰው ሕይወቱ አለፈ
በዓለም ደረጃ ጊነስ ቡክ ላይ አጭሩ ሰው ተብሎ የሰፈረው ኔፓላዊው ካሃጌንደራ በ27 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ መሆኑ ተሰማ።
በምድር ላይ ካሉ ሰዎች የመጨረሻው አጭር ሰው የሆነው ካሃጌንደራ ታፓ ማጋረ፣ 67.08 ሴንቲ ሜትር ብቻ ነበር የሚረዝመው።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪልን ጨምሮ የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጭሩ ካሃጌንደራ በሳምባ ምች በሽታ አርብ ዕለት ሆስፒታል ውስጥ መሞቱን ወንድሙን ዋቢ በማድረግ ዜናውን ይፋ አድርገዋል።
የዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ አጭር ሰዎችን መንቀሳቀስ የሚችሉ እና የማይችሉ በማለት በሁለት ምድብ ከፍሎ ይመዘግባል። በዚህም መሰረት ካሄንደራ መንቀሳቀስ የሚችለው አጭሩ ሰው ሆኖ የተመዘገበው 18ኛ የልደት በዓሉን ሲያከብር ነበር።
59 ሴንቲ ሜትር ብቻ የሚረዝመው የፊሊፒንስ ዜጋ የሆነው ጁንሬይ ባላዊንግ ደግሞ መንቀሳቀስ የማይችለው የዓለማችን አጭሩ ሰው በሚል በጊነስ ቡክ ላይ ስሙ ሰፍሯል።
ካሄንድራ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሲሰፍር፤ “እኔ ራሴን እንደ ትንሸ አልቆጥርም። እኔ ግዙፍ ሰው ነኝ” በማለት ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል። ካሄንድራ ከእርሱ ያጠረ እና መራመድ የሚችል ሌላ ኔፓላዊ መገኘቱን ተከትሎ መንቀሳቀስ የሚችለው አጭሩ ሰው የሚለው ማዕረጉን ተነጥቆ የነበረ ቢሆንም ፣ 54 ሴንቲ ሜትር ይረዝም የነበረው ግለሰብ መሞቱን ተከትሎ ካሄንድራ 2015 ላይ መልሶ ማዕረጉን አግኝቷል::