የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም

ሐረርና ጎንደር ከተሞች የዘንድሮን ጥምቀት በዓል በሐዘን ድባብ ውስጥ ሆነው አጠናቀቁ

ከእሁድ ዕለት ጀምሮ ለሦስት ቀናት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተከበረውና ዛሬ የተጠናቀቀው የብርሃነ ጥምቀቱ በዓል በጎንደር እና ሐረር ከተሞች ውስጥ ከባድ የሀዘን ድባብን ፈጥሮ አልፏል:: በሐረር ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር ። በዚሁ ዙሪያ የሐረሪ ክልል የፀጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ናስር ይያ ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

”የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ለማክበርና አካባቢውን ለማስዋብ የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን በሚያደርጉበት ወቅት በዓሉን የማይመለከትና ሕግ የማይፈቅደውን ባንዲራ ለመስቀል ሙከራ ያደረጉ በመኖራቸው አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር” የሚል አስገራሚ አስተያየት ሰንዝረዋል።

”ይህንን ተከትሎም ትናንት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ወጣቶችና ቄሮዎችን በማስተባበርና የፀጥታ ኃይሎችንም በማቀናጀት ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ችለናል” ብለዋል። ኃላፊው አንድ ሁለት ሰዎች ሰንደቅ አላማውን ለመስቀል በሚሞክሩበት ወቅት ሌሎች ደግሞ ‘ይህን አትሰቅሉም’ በሚል ግርግር ተፈጥሮ ነበር ሲሉ ውዝግቡንና የክርስትና እምነት ተከታዮቹን ትክክለኛ አካሄድ አጣጥለዋል።

”እነዚህ ግርግሩን የፈጠሩት ሰዎች እምነትን ከእምነት ማጋጨት፤ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ነው እቅዳቸው። በሁሉም አካባቢዎች ታቦት በሰላም ወጥቶ ይገባል። ነገር ግን መስጂድና ቤተክርስቲያን በቅርበት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ችግር ለመፍጠር ተሞክሯል” ያሉት አመራር ፤ ትናንት በሐረር አለመረጋጋት እንደነበርና ተኩስም እንደተሰማ በስፋት እየተነገረ መሆኑ ሲነገራቸው ጠዋት ላይ አንዳንድ ግርግሮች ተፈጥረው የነበሩ ቢሆንም ከሰዓት ከተማው ሙሉ ለሙሉ ተረጋግቷል በማለት መልሰዋል።

”ዛሬ ታቦት በሚገባበት ወቅት አራተኛ በተባለው አካባቢ ተገቢ ያልሆነ ጭፈራና ንብረት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀምረው ነበር። አካባቢው ቤተ ክርስቲያንም መስጂድም ያለበት ከመሆኑ አንጻር በሃይማኖት ስም የተደረገው ነገር ተገቢ አይደለም። ነገር ግን ተፈጥሮ የነበረው ነገር በቁጥጥር ስር ውሏል” ሲሉ አክለዋል።

ንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ውጪ እስካሁን የተጎዳ ሰው አለመኖሩንም ተናግረዋል። አቶ ናስር የጉዳት መጠኑን በትክክል ለመግለጽ ባይችሉም፤ ወደ ስምንት የሚጠጉ ቤቶች ድንጋይ ተወርውሮባቸው መስታወቶች እንደተሰባበሩ መረጃው አለኝ ነው የሚሉት::

ትናንት ጠዋት ታቦት የሚሸኙ ሰዎች መንገድ ተዘግቶባቸዋል ስለመባሉ ” ማንም መንገድ የተዘጋበት የለም፤ ማንም መንገድ የዘጋም የለም :: ታቦት እንዳያልፍ አልተከለከለም፤ መንገዱም ክፍት ነው። ይሄ ተግባር ውዥንብር ለመፍጠርና ሕዝቡን በእምነት ስም ለማነሳሳት የሚደረግ ጥረት ነው” በማለትም አብራርተዋል። ከሁለቱ ቀናት ክስተት ጋር በተያያዘ እስካሁን ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ምዕመናን በዓሉን አክብረው ወደቤታቸው ገብተው፣ ከተማዋም ሰላማዊ እንቅስቃሴዋን እንደቀጠለች አቶ ናስር ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የጥምቀት በዓል ማዕከል እንደሆነች የሚነገርላት የጎንደር ከተማም ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ አሳዛኝ ክስተት አስተናግዳለች።

በጎንደር ጥንታዊው የአፄ ፋሲል ገንዳ አካባቢ እየተካሄደ የነበረው የጥምቀት በዓል ታዳሚያንን እንዲያስተናግድ ተሰድሮ የነበረ የእንጨት ርብራብ ተደርምሶ ቢያንስ 10 ሰዎች ሕይታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል። ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የጥምቀት በዓልን ለማክበር የሄደው ሳሙዔል ባህሩ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች በቃሬዛ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ተመልክቻለሁ ብሏል። ከባለቤቱ ጋር ጥምቀትን ለማክበር የሄደው ሳሙዔል ከአደጋው በኋላ ከፍተኛ ድንጋጤ በምዕመናኑና ቀሪው የጎንደር ሕዝብ ዘንድ መፈጠሩንም አልሸሸገም።

የጎንደር ከተማ ሰላም እና ፀጥታ ሓላፊ አቶ ተስፋ መኮንን የእንጨት ርብራቡ በ’ባለሙያዎች’ የተሠራ ነው፤ አደጋው የተከሰተው በእንጨት ርብራቡ ደካማነት አይመስለኝም ካሉ በኋላ “ወጣቶች ወደ ላይ ወጥተው ማክበር ፈልገው ሲወጡ እንጨቱ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኖበት ነው የተደረመሰው።» ሲሉ የአደጋውን መንስዔ አብራርተዋል::

የአማራ ክልል ፖሊስ ቃል-አቀባይ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ 100 ያክል ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አብዛኛው ቀላል ጉዳት ነው፤ የሞቱ ሰዎች ቁጥር የጠራ መረጃ የለኝም በማለትም ሰኞ አመሻሽ ላይ ይፋ አድርገዋል ።ተጎጂዎቹወደ ጤና ተቋማት ተወስደው ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ በዓሉ እንዲጥል መደረጉንም አስታውቀዋል።


አቡነ ማትያስ በጎንደር የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጎንደር የጥምቀት በዓልአከባበር ላይ በደረሰው የርብራብ መደርመስ አደጋ ፣ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች እና ለተጎዱ ወገኖች መፅናናትን ተመኙ።

ፓትሪያርኩ በትናንትናው ዕለት በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የደረሰውን የርብራብ መደርመስ አደጋ አስመልክተው ዛሬ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመግለጫቸው የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በበርካታ አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ችግሮች እንደነበሩ የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በተለይም በጎንደር ከተማ ሰዎች እንዲቆሙበት የተሠራው ርብራብ ተደርምሶ አደጋ መድረሱን ሰምተናል በአሳዛኝ መልኩ ሰምተናል ብለዋል።

በዚህ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ እንዲሁም ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናን መኖራቸውን ተረድተናል ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች፣ ቤተሰቦች መጽናናትን እንዲሁም አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ብርታትን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በቅዱስ ሲኖዶስ ስም ተመኝተዋል::


የጎንደሩን ማማ ለ10 ዓመታት የሠራው አናፂ የመደርመሱ ምክንያት የሕዝብ ብዛት ነው አለ

በዓለም የቅረስ መዝገብ (ዮኔስኮ) የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በጎንደር ሲከበር በተለይ እንግዶች ባሕረ-ጥምቀቱን የተሻለ ቦታ ሆነው እንዲያዩ በማሰብ ለዓመታት የእንጨት ማማ እየተሰራ እዚያ ላይ እንዲቀመጡ የሚደረግበት ማማ ተንዶ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ዘንድሮ የእንግዳው ቁጥር ሊጨምር ይችላል በማለት ከአሁን በፊት ከነበረችው አንዲት ማማ በተጨማሪ ሦስት ማማዎች መሠራታቸውን የጎንደር ከተማ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ሓላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ተናግረዋል። ማማው የተሠራው ከአሁን በፊት ሢሠራው በነበረው አናፂ መሆኑን የገለጹት አቶ አስቻለው የተሠራውም ከዚህ በፊት በተሠራበት የእንጨት መጠን መሆኑን አስረድተዋል።

“ከዚህ በፊትም እንግዶችን ለማስቀመጥ ሲባል ተመሳሳይ ማማ በመሥራት እንደግዶችን እናስተናግድ ነበር ዘንድሮ የተደረመሰው ማማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ማማው ላይ ስለወጣበት ነው” ያሉት ሓላፊ ፤ ሰዉ ማማው ላይ በፊት ለፊት በኩል ለመውጣት ሲሞክር በጥበቃዎች በመከልከሉ፣ከኋላ በኩል ብዙ ሰው ተንጠላጥሎ ስለወጣበት ሚዛኑን ስቶ መውደቁን ይፋ አድርገዋል።

ማማውን የሠራው አናጺ አቶ ወንድም በቀለ በዚሁ በአፄፋሲል የመዋኛ ገንዳ ለጥምቀት በዓል ማድመቂያ እየተባለ ላለፉት አስር ዓመታት ማማውን ሢሠራ መቆየቱን ይናገራል። በሥራውም ተመሳሳይ ዲዛይን እንደሚጠቀም ጠቁሞ “የዘንድሮውን ማማ የሠራሁት አምና በሠራሁበት እንጨት ልክ ነው” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል። በአብዛኛው ከአሁን በፊት ዘንድሮ የተሠራውን ማማ ለሚቀጥለው ዓመት የተጎዳውን እንጨት በመቀየር ሢሠራ እንደቆየም አስረድቷል።

ዘንድሮ ከተጨመሩት ሦስት ማማዎች መካከል አንዷን የሠራት ደግሞ  አናፂ ወንድም ነው። ባለፈው ዓመት የተሠራችው ዘንድሮም ጥቅም ላይ የዋለችውን ማማም የሠራው ይኸው አናፂ ነው። እርሱ አምና የሠራት እና ሌሎች ጓደኞቹ ዘንድሮ የሠሯቸው ሁለት ማማዎች በድምሩ ሦስት ማማዎች ለእንግዶች የተዘጋጁ ስለነበሩ በልካቸው ብቻ ሰው እንዲይዙ ተደርገው ምንም ጉዳት አላደረሱም። ነገር ግን አንዷ እርሱ ዘንድሮ የሠራት ማማ ለሕዝቡ የተሠራች ስለነበረችና ሕዝቡም ያለገደብ ስለተሰቀለባት አደጋውን ለማስተናገድ ተገድዳለች ብሏል።

“በፊት ለፊት በኩል ያለውን መከላከያ እየጠበቀው ስለነበር በአብዛኛው ከኋላ የመጡ ሰዎች ናቸው መጥተው የሰፈሩበት። እዚያ ላይ የቆሙት የጥበቃ ሰዎች ማስቆም ነበረባቸው። ምክንያቱም የሌሎቹ መቀመጫዎች ይበቃል ተብሎ በልካቸው ብቻ ሰው ስለተቀመጠ ምንም የደረሰባቸው ነገር የለም። ነገር ግን ይሄኛው ከኋላ የመጣ ሰው ስለወጣበት “ውረዱ” ሲባሉም የሚሰማ በመጥፋቱ ሚዛኑን ስቶ ተደርምሷል” ያለው የጎንደሩ አናፂ ፤ “እስካሁን ከሠራሁት በተለየ መልኩ ዘንድሮ የተሻለ አድርጌ ነው የሠራሁት፣ በተደጋጋሚ አረጋግጨዋለሁ” በማለት የሠራው ማማ ጥራቱን የጠበቀ እንደነበር ገልጿል።

የጎንደር ከተማ የሰላም ግንባታና የሕዝብ ደህንነት መምሪያ ሓላፊ አቶ ተስፋ መኮንን በበኩላቸው ፤ የአደጋው ምክንያት የጥራት ማነስ ይሁን አይሁን ወደፊት በባለሙያ ተጣርቶ የሚገለጽ እንጂ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ነው ለማለት አልችልም ነው ያሉት።

በአደጋው የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የሟቾችን ቁጥር በተለያየ አሃዝ ቢገልጹትም አቶ ተስፋ ግን በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 10 መሆናቸውን እና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተረጋግጧል ብለዋል። እንደ አቶ ተስፋ ገለጻ በአደጋው 147 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተላኩ ሲሀን ከነዚህ መካከል 67 የሚሆኑት ወዲያውኑ ታክመው ወደቤታቸው ተመልሰዋል። 80 የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን ሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው ነው። ከነዚህ መካከል 2 ተጎጅዎች በጣም የከፋ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን አስታውቀዋል::


የደቡብ ምክር ቤት የተለያዮ ውሳኔዎችን ዛሬ አሳለፈ

የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 209ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔ አሳልፏል ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የማዕድን ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ላይ በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው ይፋ ያደረገው። በተለይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ልዩልዩ ማዕድናት የሚመረቱ ቢሆንም ከማዕድን ምርቶቹ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን ምክር ቤቱ ገምግሟል።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት የማዕድን ሥራዎች ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየት የባህላዊ፣ የልዩ አነስተኛና የአነስተኛ ደረጃ ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የሮያሊቲ፣ የመሬት ኪራይና የገቢ ግብር ክፍያዎችን መጠንና የአከፋፈል ሁኔታዎችን በዝርዝር በመመልከት የቀረበውን ደንብ አጽድቋል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ የከተማ ቀበሌ አደረጃጀት አስመልክቶ በቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ በመወያየትም አጽድቆታል።በክልሉ የሚገኙ ከተሞች የቀበሌ ምክር ቤቶች እና ይህንን መሰረት አድርጎ ስለሚደራጀው የከተማ ምክር ቤት መስተዳድር ምክር ቤቱ በዝርዝር መክሮ ውሳኔ አሳልፏል።

በከተሞች ነዋሪውን ኅብረተሰብ በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እና ያልተማከለ አስተዳደርን በመተግበር በነቃ ህዝባዊ ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የክልሉን ከተሞችና የከተማ ቀበሌያትን በአዲስ መልክ በማዋቀር በየደረጃው ምክር ቤቶችን ማደራጀት እንደሚያስፈልግም መስተዳድር ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልሉን መንግሥት አስፈጻሚ አካላት አደረጃጀትና አሠራር መመሪያ የተመለከተ ሲሆን የክልሉን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በዘርፍ በማደራጀት ውጤታማነታቸውን እየገመገመ ለመምራት እንዲያስችል የቀረበውን መመሪያ መርምሮም ማፅደቁን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል።


39ኛው የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ መልእከተኞች ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀመረ

39ኛው የአፍሪካ  ኅብረት ቋሚ መልዕክተኞች ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ በኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ተጀምሯል።በመደበኛ ጉባኤው ላይ የኅብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባኤ “ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ነው የሚገኘው።

በጉባዔያቸውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በዚሁ አዲስ አበባ ለሚካሄደው ለኅብረቱ ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ጉባኤ አጀንዳዎችን እንደሚያረቅም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

36ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤቱ ጉባኤ በፈረንጆቹ የካቲት 6 እና 7 2020 ይካሄዳል። ከዛ በኋላ በተመሳሳይ መሪ ቃል የካቲት 9 እና 10 ቀን 2020 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄድ መሆኑን የተያዘው ቅድመ ፕሮግራም ያሳያል።

LEAVE A REPLY