ኦፌኮ ጃዋርን በአባልነት የተቀበለበትን ህጋዊ ማስረጃ እንዲያቀርብ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ
በቅርቡ ኦፌኮን (የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ) የተቀላቀለው ጃዋር መሐመድ በምን ዓይነት የህግ አግባብና ማስረጃ ፓርቲውን ሊቀላቀል እንደቻለ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጥ ምርጫ ቦርድ ኦፌኮን መጠየቁ ተሰማ፡፡
የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (omn) ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ሲሆን፣ ይህንን የውጭ ዜግነቱን መልሶ የኢትዮጵያ ዜግነት ለመውሰድ እየሞከረ እንደነበር ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ነገ ድረ ገጽ ታማኝ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ መ ዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህ ህጋዊ አካሄድ ባልተጠናቀቀበት እና የግለሰቡ የዜግነት ጉዳይ መቋጫ እልባት ሳያገኝ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ተቀላቅሎ መታወቂያ መውሰዱም ይፋ ሆኗል፡፡
አነጋጋሪውን ጉዳይ ተከትሎ በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኦፌኮ ደብዳቤ ጽፎ፤ ጃዋርን ፓርቲው በአባልነት የተቀበለበትን ህጋዊ ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡ ፓርቲው በበኩሉ ጃዋርን በሚመለከት ማስረጃ እንዲያቀርብ በደብዳቤ ማሳሰቡን የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ገልፀዋል፡፡
“እሱ የእኛ አባል ሲሆን ለምን ይህ ጥያቄ እንደተነሳ ባይገባኝም፣ እኛ ደብዳቤ ጽፈንለታል” ያሉት ፕ/ር መረራ እንዴት የዜግነት ማረጋገጫ ሳያቀርብ፣ በህግ ባልተፈቀደ መልኩ ጃዋር መሐመድን በመቀበል መታወቂያ እንዲወስድ አደረጋችሁ? ለሚለው ጥያቄ “እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው፤ የአገሩን ቋንቋ ይናገራል፣ ፊቱም ኢትጵያዊ ይመስላል፤ መንግሥትም ይህን ያውቃል” የሚል በፌዝ የታጀበ መልስ ለዋዜማ ራዲዮ ሰጥተዋል፡፡
በጃዋር ዜግነት ላይ ከመንግሥት የሚነሳው ጥያቄ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ያካተተ ሊሆን ይችላል በማለት የተናገሩት መረራ ጉዲና ጃዋር በቅርቡ ዜግነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ ለምርጫ ቦርድም በጊዜው ምላሽ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡
ጃዋር መሐመድ ከኦፌኮ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳለው በመግለጽ ፓርቲውን የተቀላቀለው ይህንን የጠበቀ ትስስር መሰረት አድርጎ እንደሆነ ሊ/መንበሩ ቢገልፁም፤ በርካታ ፖለቲካ ተንታኞች ጃዋር የኦነግ ደጋፊና አባል እንደሆነ በማስታወስ፣ በቀጥታ ይህን በብዙኃኑ ሕብረተሰብ የሚጠላ ድርጅት በይፋ ከመቀላቀል ይልቅ፤ ኦነግና ኦፌኮን አጣምሮ፣ በኦፌኮ አባልነት ከጀርባ ዋነኞቹን የኦሮሞ ድርጅቶች የመዘውር እቅድ ነድፎ ያደረገው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዶር አብይ አህመድ ሹም ሽር አደረጉ
የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) ከሚኒስትርነት ስልጣናቸው ተነሱ።
ከአንድ አመት በፊት የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር ሆነው ተሹመው የነበሩት የህወሃት የመንግሥት ተወካይ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ከካቢኔ የተነሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ወይዘሮዋ የተነሱት ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ይፋ ከሆነ በኋላ ህውሀት ከውህደቱ በማፈንገጧ ህወሃትን ከመንግስት መዋቅር ለማጥፋት የተውሰነ ነው የሚል ግምት እየተሰጠ ነው።
በሌላ በኩል የትምህርት ሚኒስቴር ሆነው እንዲሰሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ የተሾሙ ሲሆን ዶክተር አብርሃም በላይ ደግሞ የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚንስትር ሆነዋል።
በድሬደዋ ለጥምቀት ሰው በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ፖሊስ አመነ
ጥር 11 ቀን የተከበረውን ዓመታዊው የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በድሬድዋ ከተማ በእምነቱ ተከታዮችና በሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ከፀጥታ አካላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባትየሰው ሕይወት የጠፋ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ ንብረት መውደሙ ተገልጿል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በከተማዋ የጥምቀት በዓል በአብዛኛው ቦታዎች ታቦታት ወደ የደብራቸው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሥርዓት የተመለሱ ቢሆንም የአቡነ ጎርጎሪዮስ ታቦት በሚገባበት ወቅትና በሌሎች በዓሉን ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ጉዳት መድረሱን ጠቁማል፡፡
የግጭቱን መንስኤ እያጣራሁ ነው ያለው የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በጥምቀት በዓል በአጠቃላይ የሚከተሉት ጉዳቶች ደርሰዋል ብሏል፡፡
የደረሱ ጉዳቶች፡–
1 ሰው በድንጋይ ተመቶ ሕይወቱ አልፏል
7 ሰው በጥይት ተመቷል
2 መኪና በእሳት ተቃጥሏል
2 መኪና ተሰባብሯል
1 የከብቶች መኖ መጋዘን በእሳት ተቃጥሏል
1 መኖሪያ ቤት በእሳት ተቃጥሏል
14 የፖሊስ አባላት ላይ ድብደባ ተፈፅሟል
3 መደብር ተዘርፏል፣ ቁጥራቸው ያልተለየ መኖሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል፤ ያለው
የድሬድዋ ፖሊስ ኮሚሽን በቀጣይ የተጣሩ ዝርዝር ሪፖርቶችን የያዘ መግለጫ እሰጣለሁ ብሏል፡፡
ኤርትራና ናይጄሪያ ጨምሮ 4 አገራት የአሜሪካ የጉዞ እግድ ሊጣልባቸው ነው
ፕ/ት ዶናልድ ትራምፕ ኤርትራን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ አገራት ላይ የጉዞ ክልከላ ሊያደርጉ መሆኑ ታወቀ፡፡ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የጉዞ እገዳ ይጣልባቸዋል የተባሉ አገራት ዝርዝርን ተመልክተናል ያሉ ባለስልጣናትን ምንጭ በማድረግ የጉዞ እገዳው ሰላባ ይሆናሉ የተባሉት የአፍሪካ አገራት ኤርትራ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ መሆናቸውን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
ስዊትዘርላንድ– ዳቮስ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም የምጣኔ ሀብት መድረክ ላይ ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ፤ አራት የአፍሪካ አገራት ላይ እገዳ ለመጣል ማቀዳቸውን ቢያረጋግጡም፣ የአገሪቱን ስም ከመግለፅ መቆጠብን ነው የመረጡት፡፡
“ዘ ፖለቲካ” ደግሞ የአገራቱ ዝርዝር የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልሆነ በማስታወስ፣ ለውጥና ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ዘግቧል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት አራቱ የአፍሪካ አገራት በተጨማሪ ቤላሩስ፣ ሞያንማር (በርማ) እና ክሪጊስታን የጉዞ እገዳ ሊጣልባቸው የሚችሉ አገራት ይሆናሉ ሲል ዘ ፖለቲኮ ቅድመ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ሊያፀድቁት እንደሚችሉ የተገመተው እና በረቂቅ ላይ የሚገኘው ሕገ እገዳ የተጣለባቸውን አገራት ዜጎች ሙሉ በሙሉ ከጉዞ የሚገድብ እንዳልሆነና በተወሰኑ የቪዛ ዓይነቶች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ብቻ ገደብ የሚጥል ነው ተብሎለታል፡፡
በቀጣይ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውዝርዝር ውስጥ የተካተቱት አገራት በምን መስፈርት ተመርጠው የጉዞ እገዳው እንደተጣለባቸው ግልጽ ባይደረግም፤ የአሜሪካ የስነሕዝብ እና ጤና ዳሰሳ ጥናት አሃዞች እንደሚያሳዩት የእነዚህ አገራት ዜጎች አሜሪካ ከደረሱ በኋላ ከተፈቀደላቸው ቀን በላይ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ባልደራስን ጨምሮ ለ4 ፓርቲዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
በእስክንድር ነጋ የሚመራው “ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ” የእውቅና ሰርተፍኬት ከተሰጣቸው አዲሶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሀል አንዱ መሆኑን የቦርዱ መግለጫ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ቦርዱ የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ መውሰዳቸውን አረጋግጧል፡፡
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ የምዝገባ ሰርተፍኬት ማግኘት የሚቻለው ማመልከቻ በጽሑፍ የምዝገባ ጥያቄ፣ ለአገር አቀፍ ቢያንስ 200፣ ለክልላዊ ፓርቲ ቢያንስ 100 አመልካቾች የፈረሙበት የስብሰባ ቃለ ጉባዔ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡
በተጨማሪም የሚመሰረተው ፓርቲ ጊዜያዊ ስም ማዘጋጀት ሲችል እና የምርጫ ህጉን እና ተያያዥ ህጎችን የሚያከብር ስለመሆኑ ማረጋገጫ እና ቦርዱ የሚወስነውን የአገልግሎት ክፍያ መፈፀም ሲችል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ የዕውቅና ፍቃድ የሚያገለግለው ለሦስት ወራት ብቻ ቢሆንም አመልካቾች በቂ ምክንያት አቅርበው ከጠየቁ በተጨማሪ ለ3 ወር ሊራዘም እንደሚችል ምርጫ ቦርድ ገልጿል፡፡
በደብረ ብርሃን መስኖ ግድብ ውስጥ ለመዋኘት የገቡ 3 ታዳጊዎች ሕይወታቸው አለፈ
በደብረ ብርሃን ከተማ መስኖ ግድብ ውስጥ ለመዋኘት የገቡ ሦስት ታዳጊ ሕፃናት ሕይወት ማለትን የከተማዋ ፖሊስ ገለፀ፡፡ በከተማዋ የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ዋና ኢንስፔክተር ምንውዬለት ጭንቅሎ፤ ታዳጊዎቹ አሳለ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ ግድብ ውስጥ ለመዋኘት ገብተው ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡
በጊዜው ታዳጊዎች ከጥምቀት በዓል መልስ በግድቡ ለመዋኘት በገቡበት ወቅት ነበር ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ የጓደኞቹን መስመጥ የተመለከተው ጓደኛቸው ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሠረት የኹለቱ ታዳጊዎች አስከሬን ጥር 12 ቀን አመሻሽ ላይ መገኘቱን የጠቆሙት ኢንስፔክተሩ፣ የአንደኛው ታዳጊ አስከሬንን ለማግኘት ፍለጋው አሁንም መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡
በግድቡ ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው ሟቾች የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን ተከትሎ ረቡዕ ጥር 13 ቀን ሥርዓተ ቀብራቸው መፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡
በሙስና ለተዘፈቀው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ዘርፍ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መ/ቤት ተቋቋመ
በግንባታው ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን መ/ቤት ተቋቋመ፡፡ አዲሱ መሥሪያ ቤት በሴክተሩ ያለውን ችግር ከመቅረፍና ጉድለቶችን በአግባቡ ከመለየት ባለፈ እንደ ፕሮጀክቱ ችግር ዓይነት መፍትሔ ለማስቀመጥ ያስችላል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም ዘርፉን ወደ ትክክለኛ ቁመና ለመመለስና የሚገነቡ ፕሮጀክቶች በተያዛቸው ውልና ስምምነት መሰረት እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሓላፊነትም እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ተቋሙ የዘርፉን ችግሮች መለየትና መቅረፍ ቀዳሚ አላማው መሆኑን ገልፀው፤ ተቋሙ ባከናወናቸው ሥራዎች የትልልቅ ፕሮጀክቶችን አሁናዊ ቁመና በመመልከት የቁጥጥረ ሥራ መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል፡፡
ተቋሙ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ የአሠራር ግድፈት ያለባቸውን ህጎች የማሻሻል ሥራ ያከናውናልም ተብሏል፡፡