እንደ ልማድ ሆኖ ጩኸት የበዛበት ነገር አይስበኝም። ሌሎች ያደነቁትን አላደንቅም ባልልም ወጣቱ ድምጻዊ ዳዊት ጽጌ እንደሰራው “የኔ ዜማ አልበም ቲፎዞ ለበዛበት ነገር ልቤ አይደነግጥም። ጭራሽም አንዳንዴ ዝግ ስሜት ይኖረኛል። እርግጥ ነው ድምጻዊው ባላገሩ አይዶል ላይ አሸናፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ በሰማነው ድምጹ አቅሙን አሳይቶናል። የአንድ ድምጻዊ ባለ ጥሩ ድምጽ መሆን ግን ብቻውን ስኬታማ አያደርግም። በስራው ላይ አሉ የተባሉ የሙዚቃ ሰዎች ተሳትፈውበታል። ይህም ግን በራሱ በቂ አይደለም። የዳዊት ጽጌ ” የኔ ዜማ ” አልበም የእሱ ብቻ ሆኖ ይቀር ወይም የእኛም ያደረሰገው እንደሆን ለማየት አልበሙን ማድመጥ ጀመርኩ። ከ” ባላገሩ ” እስከ ” ባየው ባየው “።
አብርሀም ወልዴ መቸም ባላገር ላይ ተለክፏል። ተለክፎም ሰው ይለክፋል። ስለ ባላገር በግጥምና ዜማ ሲናገር እኔን ይነዝረኛል። “ባላገር ስለራበው የልጆቹን ጓደኛ ከብቶቹን አርዶ አይበላም ” ብሎ ለባላገር ያለውን ፍቅርና ክብር ገልጦ ነው የተለከፈውና እኛንም የለከፈን ። የዚህ አልበም መጠሪያ ” የኔ ዜማ ” ይሁን እንጂ የአልበሙ መክፈቻ ባላገሩ ነው።
#ባላገሩ
” ምን ችግር ቢገጥመው ባላገር
ተስፋ አዬቆርጥም ከቶ ስላገር
………………………………..
ይመስክር ባላገር አፈርሽን ‘ሚቀምሰው
ጣ’ምሽን ቢያውቀው ነው ስላንቺ የሚያለቅሰው
……………………………………………………
ቴዎድሮስ ቢጋደል ዮሐንስ ቢቂላ
ምን ጉዳይ አላቸው ካገራቸው ሌላ … ” ይላል ። ለአብርሃም ባላገር ባለ ሀገር ነው። ሀገር ባላገሩ ልብ ውስጥ ናት። ከፍ የመለች ክብር ናት። በከተሜው አንደበት የምትገለጽ አይደለችም። አብርሃም የካሁን ቀደሞቹን ጨምሮ ስለ ባላገር ሲገጥም እንደ ክፉ ሰው ነው – ለማንም አያስቀርም። ባላገርን በቃላት ይግለጸው እንጂ ልብ ውስጥ አስቀምጦ እንዳይወጣ የማድረግ ምትሀት አለው ። ደግሞ ይሄ ዳዊት የሚባል ልጅ ልጅ አይደለም እንዴ ? እንዴት እንዴት ነው ያደረገው ? ትንግርት ነው።
አብርሃም ከባላገር መልስ አስመራ ይዞን ይሄዳል። አስመራ የነፀሐዪቱ ባራኺ ሀገር፣ የነአብርሃም አፈወርቂ፣ የነየማነ ባሪያ ሀገር። “አስመሪኖ ” የሚለው ስራ አስመራና አዲስ አበባ ለሚጋሯት ኤርትራዊት ድምጻዊት ነው ወይስ ለአስመራ ? ፀሐዪቱ ለአዲስ አበባ ላዜመችው የእሱ መልስ ፣ እዚህ መሀል አዲስ አበባ ላይ የሰራላት ሀውልት ነው ” አስመሪኖ “። ዛሬ በሕይወት የሌለችውን ፀሐዪቱን ከመቃብር ቀስቅሶ ፣ እድሜዋን ወደ ወጣትነት መልሶ ” ነይ የኔ ጣፋጭ ኧረ ነይ ” ይላታል ።
#አስመሪኖ
” ባለ ክራር የዜማ እናት
ያቺ ምስኪን ጥበብ የት ናት ?
ፀሐዪቱ ጠልቃ እንዳይሆን
ምነው ጠፋች ንጋት ሲሆን . . . ” እያለ ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ መሀል የበበራው ንጋት ፀሐዪቱ ኖራ አዲስ አበባ ላይ ሊያያት መናፈቁን ይገልጻል ።
አብርሃም አስመራን ይጠይቃል ።
” አብርሃም አፈወርቂ የማነ ባሪያ
አስመራ ወርቅሽን አፋልጊኝ ነያ ” ይላል ።
እንዲህ ያሉ ግጥሞች ሀሳብ ብቻ ይዘው ለመጻፍ ተቀምጠው የሚሰራ አይደለም። አያ ሙሌ ሲራቡ ተርቦ፣ ሲታረዙ ታርዞ ሀሳቡን ራሱን ሆኖ በነፍስ ቀለም የሚጻፍ ነው። እውነት ለመናገር ” አስመሪኖ ” ከኦሮማይ ቀጥሎ የተሰራ ታላቅ የጥበብ ስራ ነው።
” የኔ ዜማ ” አልበም 14 ምርጥ ስራዎች አንዱን ከሌላው ለመለየት እስኪቸግር የተሞላበት በአያ ሙሌ አገላለጽ ” ጥንቅቅ ! ” ያለ ስራ ነው። አንደ አልበም እንዲህ በሁሉም ሙያዎች ተሟልቶ መምጣት በአመታት አንዴ የሚገኝ ነው፤ በተለይ በዚህ የነጠላ ዜማ ጊዜ። ከዳዊት አልበም የተረዳሁት እንደ አብርሃም አይነት የተሟላ ፕሮዲዩሰር ካሰበበት የማይወድቅ አልበምን እርግጠኛ ሆኖ መስራት እንደሚችል ነው።
ዳዊት ጽጌ ክስተት የሆነ በዘርፉ የተሰማሩ የሙያ አጋሮቹን የሚያስደነግጥም የሚያነቃም ድምጽ ነው። ድሮ ትልቅ ድምጻዊ የነበረ ይመስለኛል። በአንድ ወቅት የድምጻዊት ሄለን በርሄ የመጀመሪያ አልበም ሲወጣ ዓለማየሁ ገላጋይ ለአንድ መጽሔት ” ዘንድሮ አድማጩ የሄለንን አልበም ካልገዛ እውነትም ሙዚቃን ላለመስማት አድሟል ማለት ነው ” እንዳለው ለዳዊት ጽጌም እንደዚያው ነው ። እኔን ግን የአድናቂዎቹ ጩኸት ግነት መስሎኝ አሳስቶኛል። ለመስማት አዘግይቶኛል። እንደ ስራው ምሉዕነት ገና አልተጮኸለትም። ልብ ብለን አላሰብነው ይሆናል እንጂ ለብዙ ዓመት የናፈቀን ልብ የሚሞላ ፣ እኛን የሚመስል አልበም ይህ የዳዊት ጽጌ ” የኔ ዜማ ” ነው – የኛም ዜማ።
#የኔ_ዜማ
” ፍቅር ነው መንገዴ
ይቅርታ ነው ልምዴ
ስኖር ከሰው በላይ
ምንም ነገር አላይ
የአበቦቹም ውበት ያልፋል
ብርቱም ያሉት ይሸነፋል
የሰማዩም የምድሪቱ
ፍቅር ላይ ነው መሰረቱ
ፍቅር
ፍቅር
የኔ ዜማ
የልቤ ዜማ . . . ”
#እናመሰግናለን_ዳዊት_ጽጌ
#እናመሰግናለን_አብርሃም_ወልዴ
#እናመሰግናለን_በስራው_የተሳተፋችሁ_ሁሉ