ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “የጃዋር መሀመድን የኢትዮጵያዊ ዜግነት ጉዳይ ማረጋገጫ አምጡ” ሲል ምርጫ ቦርድ ስለጠየቃቸው ተበሳጭተዋል። መበሳጨታቸውን መልሳቸው ይመስከራል።
“እስከዛሬ ዝም ብለው እኛ ጋር ሲገባ ነው እንዴ ዜግነት የሚጠይቁን? ንግግሩም መልኩም ኢትዮጵያዊ አይደል እንዴ የሚመስለው?” ነበር ያሉት።
ሲጀመር ፣ ይህ ጥያቄ ከምርጫ ቦርድ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ እንደሳቸው ካለ በፖሊቲካው ከቆየ አንጋፋ ሰው የሚጠበቅ አልነበረም።
ሲቀጥል፣ ኢትዮጵያዊነቱን ሳያረጋግጡ፣ “ኢትዮጵያዊ” የሚል መታወቂያ በመስጠታቸው ብቻ ድርጅታቸው ሊጠየቅ እንደሚችል የረሱት ይመስላል።
ከዚያ ደግሞ “እኛ ጋር ሲመጣ ነው ወይ የሚጠየቀው” ላሉት፣ ሰውየው የፖሊቲካ ድርጅት በይፋ ሲቀላቀልና እወዳደራለሁ ሲል ኦፌኮ የመጀመሪያው ነው፣ ስለዚህ ሌላ ድርጅት ውስጥ ስላልገባ “እኛጋ ስለገባ” የሚለው አያስኬድም።
በመጨረሻ፣ ለመልክማ ባራክ ኦባማ ቁጭ ኢትዮጵያዊ አይደል እንዴ የሚመስሉት? ስንቱ ህንድና ብራዚልስ? ቋንቁስ ቢሆን፣ አማርኛን አቀላጥፎም ሳያቀላጥፍም የሚናገር ስንት ፈረንጅ አለ አይደል እንዴ? በመልክና ቋንቋ ስለቻሉ ዜግነት ክተሰጠ ከዓለም ህዝብ ቢያንስ 1/3ኛው በአንድም በሌላም ኢትዮጵያዊ ይመስላልና ፓስፖርት ስናድል ልንውል ነው ማለት ነው።
ማጠቃለያ፦ መረራ ከጃዋር ጋር መሞዳሞድ መጀመሪያቸው ገና ብዙ ጣጣ ይዞባቸው ይመጣል፣ ሰላሌ ላይ አንድን ዕምነት አሰድቦ፣ ሁከትና ጥላቻን ነዝቶ፣ አመጽ ጋብዞ ፣ በሱ ምክንያት የሳቸው ድርጅት ጥላሸት ወርሶታል። ያ የሰላሌው የጥላቻ ቅስቀሳ ያመጣውን ቁጣ ለማስቀየር ሀረር ላይ ፣ [በኔ ግምት] ጃዋር የራሱን ሰዎች ልኮ መስታወት አሰብሮ “የኦፌኮ ቢሮ ተሰበረ” አለ። አስቡት፣ ፕሮፌሰር መረራና ድርጅታቸው 20 ዓመት አልፏቸዋል፣ ማንም ሰው እንኳን ቢሯቸውን ሊሰብር ፣ በክብርና በአድናቆት ነበር በየሄዱበት የሚቀበላቸው። እናም ጃዋርን ካስገቡ ወር እንኳን ሳይሆናቸው ይህ ለምን?
ጃዋር ፣ ኦፌኮ የገባው ወዶት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፣ በሳቸው ትከሻ ሊመረጥ ስለፈለገ ብቻ ነው፣ ኦነግ ዘንድ እንዳይሄድ አንጋፋዎቹ እያሉ ለሱ ማንም ቦታ አይሰጠውም። ያንን ያውቃል። ጃዋር ዓላማው አንድ ነው፣ ወይ እሱ የሚቆጣጠራትና እንደፈለገ፣ እንደኳስ የሚጫወትባት ኢትዮጵያን መፍጠር ወይም ማፈራረስ። ይህ ደግሞ እስከዛሬ ከምናውቀው የመራራ አቋም ጋር የሚሄድ አይደለም።
እናም መረራ የህይወታቸውን ትልቅ ስህተት የተሳሳቱት ከጃዋር ጋር ጋብቻ የፈጸሙ ዕለት ነው። ይልቁኑ ይቺ የዚግነት ጉዳይ ምክንያት ሆናቸው፣ “የአሜሪካ ዜግነትህን መልሰህ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማግኘትህን እስታረጋግጥ ድረስ” ብለው በዘዴ ቢያርቁት ይበጃቸዋል።
ኢትዮጵያዊ ሆኖ ታክስ ለማይከፍልበት፣ አንድም የሚረባ ነገር ለጠቅላላው ኢትዮጵያዊም ሆነ ፣ ወክለኝ ሳይለው ወክየዋለሁ ለሚለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ባልሰራበት አገር ነው እንግዲህ ፖሊቲካው ውስጥ ገብቶ የሚንቦራጨቀው።
ብዙ ጋዜጠኞች ጃዋር መሃመድን ጥያቄ ሲጠይቁ ከርመዋል፣ ነገር ግን አንድም ጋዜጠኛ 1) አንተ አሜሪካዊ ነህ፣ ኢትዮጵያዊ ሳትሆን፣ ታክስ ሳትከፍል በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን አገባህ? 2) እስቲ ለኦሮሞ ማህበረሰብ የሰራኸውን አንድ መልካም ሥራ (ወሬ አይደለም) ንገረኝ? ብሎ የጠየቀ አላጋጠመኝም።