ያልተጠበቀ አልነበረም። ለውጡን በፊት ለፊት ከሚቃወሙ፡ የዶ/ር አብይን መንግስት ለማስወገድ አጥብቀው ከሚሰሩ፡ በህወሀት መስመር ላይ ሰልፋቸውን አስተካክለው ጸረ አብይ ውሳኔዎች ላይ ጉልህ ሚና በመጫወት ከሚጠቀሱ የህወሀት መሪዎች አንዱ ናቸው። የእነደብረጺዮንን ኩርፊያ ለማስታገስና የብሄር ኮታን ለማሟላት በሚል ጠ/ሚሩ የህወሀት አመራሮችን በፊደራል መንግስቱ የሚኒስትርነት ስልጣን ቢሰጧቸውም Human grenade የሰው ፈንጂ ሆነው ነበር በአዲስ አበባ የሰነበቱት። አንድ ቀን ማፈንዳታቸው አይቀርም። በጊዜ መገላገል ነው። መዘግየት ይበልጥ ዋጋ ያስከፍላል።
ሞንጆሪኖ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመራችን ሆኖ እስከወዲያኛው ይቀጥላል የተሰኘውን መፈክር አጉልተው የሚያሰሙት ዶ/ር አብይ በሚመሩት የሚኒስትሮች ም/ቤት ውስጥ ቁጭ ብለው መሆኑ አስገራሚ ነው። ስልጣኑን አንፈልግም ብለው እነስብሃት ነጋን በቁም እስር መቀሌ ላይ ቢቀላቀሏቸው ይሻል ነበር። ለማንኛውም ዶ/ር አብይ የህወሀትን ቤት ማፈራረሳቸውን ቀጥለዋል። በእነሞንጆሪኖ መሀል ኢትዮጵያ ላይ በአንድ እግሩ ቆሞ የነበረው ህወሀት ተነቅሎ ሙሉ በሙሉ ወደመቀሌ መጠቃለሉ የማይቀር መሆኑን ያረጋገጠ ውሳኔ ነው ማለት ይቻላል።
በሴቶች፡ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትርነት እንዲሁም በሰላም ሚኒስቴር በምክትል ሚኒስትርነት የሚሰሩት ሁለት የህወሀት አመራሮች እድል እጣፈንታ ምን እንደሚሆን አልታወቀም። በቀጣይ እነዚህን የሚኒስትርነት ቦታዎች ከህወሀት እጅ የሚወጡ መሆናቸው የማይቀር እንደሆነ የሚያሳዩ ግርድፍ መረጃዎች አሉ። የህወሀት አመራር ሆነው በፌደራል መስሪያ ቤቶችና በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩት ከፍተኛ ባለስልጣናት ቀን ቀን ከለውጡ መሪዎች ጋር ማታ ደግሞ ከእነስብሃት ጋር መሆናቸው ማብቃት አለበት። ከአንደኛው መሆን አለባቸው። እነሞንጆሪኖ ከመቀሌው አኩራፊ ቡድን ጋር የሚዶልቱት ጥሩ ነገር አይደለም። ከያዙት ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን አንጻር ሳቦታጅ ቢፈጽሙ ጉዳቱ የትየለሌ መሆኑን መገመት አይከብድም። ፌደራል መንግስቱን ለመጣል እንደሚሰራ በቅርቡ በጉባዔው ይፋ ካደረገው የህወሀት ቡድን ጋር አብሮ መስራት ውጤቱ ለሀገር ጥፋት መሆኑ መታወቅ አለበት።
ህወሀትን የማፈራረሱን ሂደት ሳያጠናቅቁ ሰላም ይገኛል ማለት ቀልድ ነው። ጫጫታ ሊፈጠር ይችላል። ህወሀት በመነካቱ የትግራይ ህዝብ ተጠቃ የሚለው ጩኸት ሊበረከት እንደሚችልም ይጠበቃል። ከህወሀት በላይ ህወሀት ሆነው የአዞ እምባቸውን የሚያነቡ አውርቶ አዳሪዎች ከወዲሁ ለቅሶ ጀምረዋልና በቀጣይም ደም አስከማንባት መድረሳቸው አይቀርም። ሟርተኛና ቀውስ ጠማቂ ሚዲያዎች የህወሀትን ለቅሶ ነጥቀው እዬዬውን ለማቅለጥ ዳር ዳር ማለታቸውን ላስተዋለ በቀጣይ ከመቀሌ ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓና አሜሪካን ደረት የሚደልቁ እንደሚኖሩ መጠብቅ ያስፈልጋል። ግን ምንም አያመጡም። ህወሀት ጥርሱ ወላልቋል። ትንፋሹ ተቆርራጦ የሞት ሳል እያሳለ ነው። በማገገሚያ ክፍል በሞትና ህይወት መሀል ትንቅንቅ ውስጥ ከሚገኘው ህወሀት የሚሰነዘረው ዱላ የቄጤማ ያህል ልፍስፍ ነው። ህወሀት ተነካ ብለው በጩኸት የሚያደነቁሩ አውርቶ አዳሪዎችም በዙሪያቸው ለተኮለኮሉት ታዳሚዎቻቸው ጊዜያዊ ሙቀት ከመስጠት ያለፈ ውቅያኖስ የሚሻገር ተጽዕኖ መፍጠር አይችሉም። ጩኸቱም፡ ግርግሩም ወረት ነው። ሀገርን ማዳን ግን ዘላለማዊ ድል ነው።
እናም ጠ/ሚር አብይ በህወሀት እየማሉ፡ ስለህወሀት እየሰሩ የለውጥ ሃይሉን የሚገዘግዝ ስውር አጀንዳ እያስፈጸሙ ያሉ ባለስልጣናትን ከሃላፊነት በማንሳት የህወሀትን ቀቢጸ ሴራ በእንጭጩ መቅጨት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት። ዶ/ር አብይ ስለሀገር ሰላም ብለው ህወሀት ላይ አንጀታቸው አለመጨከኑ ዋጋ አስከፍሏል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሀት ባርነት ነጻ ቢወጣም ወገኑ የሆነው የትግራይ ህዝብ ግን አሁንም በህወሀት ግዞት ስር እንዲቆይ አድርጓል። ማፈራረሱ ይቀጥል። የትግራይን ህዝብ ነጻ ማውጣት የፌደራል መንግስቱ ቀጣይ ስራ መሆን አለበት። በህንጣሎ ወረዳ የተጀመረው ጸረ ህወሀት ተቃውሞ የህወሀት ቀሪ መንገድ በእሳት የተከበበ መሆኑን የሚያሳይ ነውና ከትግራይ ህዝብ ጎን መቆም የቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ግዴታ ነው። ህወሀትን ከእነጉድፍ ገጽታው በታሪክ ውስጥ አስቀምጦ ማሰናበት ለኢትዮጵያ ሰላም፡ ለአፍሪካው ቀንድም መረጋጋት ሊያስገኝ እንደሚችል አይጠረጠርም።