በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሚመራው ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ጥቃቶችን እያጋለጠ አይደለም ተባለ
በአዲስ መልክ እየተዋቀረ ነው የተባለለት የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ከተቋቋመበት አላማ አንፃር የተጣለበትን ሓላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ተባለ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ሲካሄድ ምክር ቤቱ በስብሰባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ 15 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከዚህ ቀደም በነበሩ ፖለቲካዊ እና ተያያዥ ምክንያቶች የሚጠበቅበትን ሓላፊነት በተገቢው መንገድ እየተወጣ አለመሆኑን ጠቁመው ፤ ችግሩን ለመቅረፍም በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ የማዋቀር እና የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የተቋሙን አቅም እና ውስንነቶች እንዲሁም የሚስተዋሉ የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶች እና ውስንነቶችን ማሻሻል የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ ነው ያሉት የቀድሞ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ፕርሮግራም ዳይሬክተርየኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ከወጣ 20 ዓመት ያለፈው መሆኑን ፣ አዋጁን አሁን ከምንገኝበት አገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የማሻሻያ አዋጁ በተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት በሚታወቀው እና የሁሉም አገራት ሰብኣዊ መብት ተቋማት በሚመሩበት ዓለም ዐቀፋዊ መርህ የሚቃኝ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አላማ አንፃር የተጣለበትን ሓላፊነት በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል።
በሌላ በኩል የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀል፥ በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መከላከል የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።
ዶ/ር ዐቢይ በክልል ጥያቄ የሚናወጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ተወካዮችን አነጋገሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከደቡብ ክልል ከተውጣጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተሰማ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ከ2 ሺህ የሚበልጡ ተወካዮች ተሳታፊ እንደነበሩ የጠቆመው ዜና ፤ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የወጣት ተወካዮች በውይይት መድረኩ መገኘታቸውን ያስረዳል።
በውይይቱ ተሳታፊዎቹ በክልል መደራጀት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ የመንገድ ችግር እንዳለ፤ የጤና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የጤና ባለሙያዎች እና የመድሃኒት እጥረት እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባልተዳረሰባቸው ዞኖችም ተቋማቱ እንዲገነቡም ጠይቀዋል።
በክልል እንሁን ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እየታመሰ ያለው የደቡብ ክልል ተወካዮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን ወዳልሄዱባቸው ዞኖች ሄደው ከህዝብ ጋር ለምን አልተወያዩም የሚል ቅሬታ አሰምተዋል።
በአገሪቱ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መሠራት አለበት ብለው የሚያምኑባቸውን ነጥቦች በማንሳትም ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ከሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተነጋግሮ መፍትኄ የማበጀት ሥራ ይሠራል የሚል ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፤ ከመሰረተ ልማት ጋር እና ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዘው ለቀረቡ ጥያቄዎችም የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር ታች ድረስ ዘልቆ ችግሮችን በመለየት አስተማማኝ መፍትኄ ለማምጣት እቅድ መነደፉንም አስረድተዋል።
በተበራከተው በክልል ከመደራጀት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ መድረክ ላይ መልስ መስጠት እንደማይቻል ያስታወቁት ጠ/ሚሩ ፤ ሆኖም የአገርን አንድነት እና የዜጎችን አብሮነት በማይጎዳ መልኩ በክልል ከመደራጀት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሂደት ወደ ትክክለኛ ምላሻቸው ለማድረስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል::
“አኬልዳማ” እና “ጀሀዳዊ አረካት” ዶክመንተሪን ለወያኔ የሠሩት ጋዜጠኞች የሙያ ነፃነት የለም እያሉ ነው
በቀድሞው ኢቲቪ (ኢቢሲ) ረዘም ያለ ጊዜ ያገለገሉ ከ4 ያላነሱ ነባር ጋዜጠኞች ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ባቀኑባቸው ምዕራባውያን አገራት ጥገኝነት ጠይቀዋል። በያዝነው ሳምንትም ሁለት ጋዜጠኞች በተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው ተሰምቷል::
ከጥቂት ቀናት በፈት ከም/ጠሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ለሥራ ወደ ኢንግላንድ ተጉዞ የነበረው እና ለ9 ዓመታት በኢቢሲ ከሪፖርተርነት እስከ ዜና ክፍል ምክትል ዋና አዘጋጅነት ያገለገለው ጋዜጠኛ ቢላል ወርቁ አንዱ ነው።
ጋዜጠኛው በዚህ ሳምንት ሰኞ የተካሄደውን የዩኬ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ለመዘገብ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ከሚመራ ልዑክ ጋር ወደ ለንደን ከተጓዘ በኋላ ነበር ጥገኝነት የጠየቀው። ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢቢሲ ነባር ጋዜጠኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሄዱባቸው ምዕራባውያን አገራት ጥገኝነት ለመጠየቅ የተገደዱት ከጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ በሚደርሱባቸው ጫናዎች እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በውጪ አገራት የሚገኙት የቀድሞ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ለቢቢሲ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት በጋዜጠኝነት ሥራቸው የኤዲቶሪያ ነጻነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል:: “ጉዳዮች እየተመረጡ ነው የሚዘገቡት” በማለት እንደምሳሌ፤ በጅግጅጋ አብያት ክርስቲያናት ሲቀጣሉ በፍጥነት ሳይዘገብ መቆየቱን፣ የሃይማኖት ተቋማት መግለጫዎች ለምሳሌ ሲኖዶሱ የኦሮሚያ ቤተክነት መቋቋምን አወግዛለሁ ማለቱ አለመዘገቡ፣ በሞጣ የተፈፀመው ጥቃት ሰፊ ሽፋን ሳይሰጠው እንደቀረ፣ የትግራይ ክልል እና የህውሓት መግለጫዎች አለመዘገባቸው፣ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ የተዘገበበት መንገድ እና ሌሎችን ጉዳዮችን በመጥቀስ የዜና ሽፋን የሚሰጣቸው ጉዳዮች የተመረጡት ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ የሙያ ነፃነት በተቋሙ አለመኖሩን በመግለፅ ይከራከራሉ።
“እንደ ከዚህ ቀደሙ እኔን ብቻ አገልግሉ የሚልና ሌላውን ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆን መገናኛ ብዙኃን በመሆኑ የድርጅቱ አገልጋይ ሆኖ ላለመቀጠል ወስኛለሁ” ያለው ቢላል ወርቁ ፤ ገዥውን ፓርቲ ማገልገል ብቻ ዓላማቸው ያደረጉና ከዚያ ውጭ የሕዝብም ሆነ የትኛውም ፓርቲ ፍላጎት የማይነሱበት ፣ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለመዘገብ የሚያስችል ሁኔታዎች የሉም በማለትም የተፅእኖውን መጠን ለማግዘፍ ሞክሯል።
አሁን ላይ ተባብሰው የመጡት የብሔርና እምነት ጉዳዮች በሙያው ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች በእርሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ባልደረቦቹም ላይ የሚያጋጥሙ እንደሆኑ ጋዜጠኞችም በሚያነሱት ጉዳዮች በማንነታቸውና ኃይማኖታቸው የሚፈረጁበት አጋጣሚዎችም በርካታ ናቸው ይላል ቢላል ወርቁ::
የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱልጀሊል ሃሚድ ግን በተቋሙ የኢዲቶሪያል ነጻነት የለም የሚሉ ክሶችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገውታል::
“የራሳችን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለን። በዛ መሠረት ነው በነጻነት የሚሰሩት። ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ማንም ጣልቃ አይገባም። ሁሉም ነገር የሚሰራው በጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ነው። አቶ ቢላል በራሱ ፍቃድ ለኑሮ ይሻለኛል ብሎ ነው የቀረው እንጂ የኤዲቶሪያል ነጻነት የለም የሚለው አያስኬድም” ሲሉም ተከራክረዋል።
ጋዜጠኞቹ ዜናዎች እየተመረጡ ነው የሚሰሩት በማለት ላቀረቡት ቅሬታም አቶ አብዱልጀሊል፤ “እኛ አገርን በማይንድ ፣ ሕዝብን በማያራርቅ መልኩ ነው ዜናዎችን የምንመርጠው። እንደውም የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ ቀድመን የዘገብነው እኛ ነን” በማለት ክሱ ከእውነት የራቀ መሆኑን ይፋ አድርገዋል::
አሁን በስደት ላይ ሆነው ለመኖሪያ ፍቃድ ማሟያ የሙያ ነፃነት የለንም እያሉ የሚጮኹት ቀጥተኛ የወያኔ ድምጽና የታማኝ ካድሬዎች መቀጠሪያ ብቸ በሆነው ኢቲቪ (ኢቢሲ) ውስጥ እያንዳንዱ ቃል በትዕዛዝ በሚሠራበት መዋቅር ውስጥ ሕዝብን ሲያሳስቱና ሀሰተኛ ፕሮፐጋንዳ ሲነዙ ከርመው የተሻለ የሙያ ነፃነት ባለበት ወቅት እንዲህ ማለታቸው ከተለያየ አቅጣጫ ትችት እያሰነዘረባቸው ይገኛል::
ቢላል ወርቁና አብዲ ከማል የህወሓት መራሹ መንግሥት አሽከር በነበሩበት ወቅት በእውነተኛ የነፃነት ታጋዮቹ እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ የፈጠራ ክስ ላይ እንዲሁም በኡስታዝ አቡበከርና የሙስሊም አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ የተሠሩትን “አኬልዳማ” እና “ጀሀዳዊ አረካት” የተሰኙ ሁለት አሳፋሪ ዶክመንተሪዎችን ያዘጋጁና ያቀረቡ ሆድ አደር ጋዜጠኞች መሆናቸውን የሚያስታውሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከለውጡ በኋላ እንኳ ለዚህ ታሪካዊ ስህተታቸው ሕዝብንም ሆነ ተጎጂዎቹን ይቅርታ ያልጠየቁ መሆናቸውን በመጥቀስ የአሁኑ ጬኸታቸውን ውድቅ እያደረጉት መሆናቸውን የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ አድርሶናል::
ምርጫውን እንዲታዘብ የተጠየቀው የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔዬን በ1 ወር ውስጥ አሳውቃለሁ አለ
የአውሮፓ ኅብረት ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ከመታዘብ ባለፈ በቅድመና ድህረ ምርጫ ወቅት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባላት ተወካዮች ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር በ2012ቱ አገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ ተነጋግረዋል። ተወካዮቹ ለአገር ዐቀፉ ምርጫ እየተካሄደ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሁለት ሳምንታት በመዟዟር እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ታዝበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ እየተካሄደ ስላለው የፖለቲካ ለውጥ በተለይም ለአገር ዐቀፉ ምርጫ እየተደረገ ስላለው ቅደመ ዝግጅት ለፓርላማ አባላቱ ገለጻ ከማድረጋቸው ባሻገር ፤ ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ እንደ አዲስ ከማደራጀት ጀምሮ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አላሰራ ብለው የነበሩ ህጎች ተሻሽለው በምክር ቤቱ እንዲጸድቁ ተደርገዋል ብለዋል።
ቀጣዮና በነሐሴ ወር አጋማሽ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሰላምና ጸጥታ ተቋማት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተቋማት ከወዲሁ ቀድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የሚናገሩት አፈ ጉባዔዋ የአውሮፓ ኅብረት በዚህ ላይ ያለውን የካበተ ልምድ ቢያካፍል የተሻለ ነገር መሥራት እንደሚቻል እምነታቸውን አጋርተዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ አባላት ልዑክ ቡድን መሪ ሎዊ ፍሌድ የአባላቱ የመስክ ጉብኝት ኅብረተሰቡ ስለ ምርጫና የምርጫ ታዛቢዎች ያለው ግንዛቤ፣ የአገሪቷ የፖለቲካና የሰላም ሁኔታ፣ የትራንስፖርት፣ የምርጫ መሳሪያዎች አቅርቦትና ሌሎችም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ከምርጫው ጋር ግንኙነት ካላቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ያመላከቱት ሓላፊው ፤ የልዑክ ቡድኑ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄዱንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከምርጫ 97 በኋላ በተለየ መነቃቃት የምታካሂደው የዘንድሮ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የፓርላ አባላቱም ሆኑ የጸጥታ አካላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያስጠነቀቁት የአውሮፓ ኅብረት አባላት ፤ ኅብረቱ በታዛቢነት እንዲሳተፍ የተጋበዘበትን ምርጫ አስመልክቶ ከአንድ ወር በኋላ ታዛቢ መላክ አለመላኩን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ይፋ አድርገዋል::