«ካሜራ ፊት ስቀመጥ ዘርም፣ ዘመድም ፓርቲም የለኝም» ያለችው የኤል. ቲቪ ጋዜጠኛ ዛሬ እስክንድር ነጋን ቃለ መጠይቅ ስታደርግ ስሜቷን መቆጣጠር እያቃታት ስትንተከተክ የተሞላችው የኦነግ ፕሮፓጋንዳ ሲፈስ ይታይ ነበር። «የቤተሰቦቼ» ባለችው ቋንቋ አለመማሯን እንደ ጭቆናና በደል አድርጋ ስታቀርበውና በእውነት ማንጠሪያው በጋዜጠኛነት ወንበር ላይ ተሰይማ የኦነግን ድንቁርና እንደ እውነት ደግፋ ለማቆም ስትውተረተር አየናት። ለመሆኑ «የቤተሰቦቼ» ባለችው ቋንቋ አለመማሯ ጭቆናና በደል ነውን? የት አለምና የት አገር ውስጥ ነው ፊደል የሌለውና የጽሑፍ ባሕል የሌለው ቋንቋ የትምህርት መስጫና የማስተማሪያ ቋንቋ የሆነው?
በጋዜጠኝነት ወንበር የተሰየመችዋ የኤል. ቲቪ ጋዜጠኛ የኦነግን ፕሮፓጋንዳ እየደጋገመች ስታስተጋባ «የቤተሰቦቼ» ባለችው ቋንቋ አለመማሯን የ«ብሔር» ጭቆና ስለነበር ሳይሆን የቤተሰቦቿ ቋንቋ ፊደል የሌለውና የጽሑፍ ቋንቋ ባለመሆኑ የተነሳ መሆኑን አታውቅም። በያ ትውልድ ድንቁርና የ«ብሔር ጭቆና» አሰፈኑ የሚባሉት ዳግማዊ ምኒልክም ሆነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዘረጉት የትምህርት ሥርዓት ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት የነበረውን የሥነ መንግሥትና የሥነ ትምህርት ሥርዓት አስቀጠሉ እንጂ ኦሮሞን ለመጨቆን ያወጡት አዲስ የሥነ መንግሥትና የሥነ ትምህርት ሥርዓት የለም። የኤል. ቲቪዋ «ጋዜጠኛ» «የቤተሰቦቼ» ባለችው ቋንቋ ያልተማረችው ኦሮሞ የንግግር እንጂ የጽሑፍ ሥልጣኔ ስለሌለው መሆኑን አታውቅም። «የቤተሰቦቼ» ባለችው ቋንቋ አለመማሯን እንደ ጭቆናና በደል አድርጋ ከቆጠረችውም የጨቆኗትና የበደሏት ለቤተሰቦቿ ቋንቋ የጽሑፍ ፊደል ያልፈጠሩት የራሷ ቤተሰቦች ናቸው።
ባጭሩ በትምህርት ሒደት ውስጥ ያለፈና ስለ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት የሚያውቅ ሁሉ እንደሚገነዘበው በዚያ ዘመን ኦሮምኛ የትምህርት ቋንቋ ያልሆነው በግራ ፖለቲከኞች እንደተስተጋባው «የብሔር ጭቆና» ለማድረግ ታስቦ ሳይሆን በኦሮምኛ ትምህርት ለመጀመር አንደኛ ኦሮምኛ የጽሑፍ ፊደል ስላልነበረውና የጽሑፍ ፊደል የሌለው ቋንቋ የትምህርት ቋንቋ የሆነበት ሁኔታ በአለም ላይ ስለሌላ፤ ሁለተኛ በቋንቋው የሰለጠነ አስተማሪ ባለመኖሩ፤ ሶስተኛ በኦሮምኛ ቋንቋ የተዘጋጁ የማስተማሪያ መጽሐፍ፣ የማጣቀሻ መጽሔቶችና የንባብ መሳሪያዎች ባለመኖራቸው የተነሳ ኦሮምኛ የትምህርት ቋንቋ ሊሆን አልቻለም።
እንኳን በዚያ ዘመን ዛሬ በምንኖርበት የሰለጠነ የዲጂታል ዘመን እንኳ ከኢትዮጵያ 85 ቋንቋዎች መካከል የአንደኛ ደረጃ ማለትም ከ1ኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የትምህርት ቋንቋ የሆኑት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቁጥር ከ25 በታች ነው። የኢትዮጵያን የአንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ማለትም ከ7ኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ትምህርት የሚሰጥባቸውን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቁጥር ካየን ደግሞ ትምህርት የሚሰጠው ደግሞ በአምስት ቋንቋዎች ብቻ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቋንቋ የሆነ አንድም የኢትዮጵያ ቋንቋ የለም።
እንግዲህ ከ85 የአገራችን ቋንቋዎች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል ትምህርት በ25 ቋንቋዎች የሚሰጠው፤ የአንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት በአምስት ቋንቋዎች ብቻ ትምህርት የሚሰጠው፤ በአንድም የአገራችን ቋንቋ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የማይሰጠው አንድም ቋንቋዎቻችን ፊደል ስላልተበጀላቸው፤ ሁለትም በቋንቋዎቹ የሰለጠነ የሰው ኃይል ስለሌለና ሶስትም በቋንቋዎቹ የተዘጋጀ የማስተማሪያ መጽሐፍ፣ የማጣቀሻ መጽሔቶችና የንባብ መሳሪያዎች ስለሌሉ ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ፊደል የሌለውና የጽሕፈት ቋንቋ የትምህርት ቋንቋ የሚሆን ይመስል ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በነበረው የኢትዮጵያ የሥነ ትምህርት ሥርዓት ስለተማረች ጭቆናና በደል የሚሆነው በእውቀት ጾመኞች ፍርድ፣ ፍፁም መሰረተ ቢስ፣ አላዋቂነት በተሞላበት፣ ልክና ለከት በሌለው የጥላቻና የድንቁርና አስተሳሰብ ብቻ ነው።