ኢሕአዴግ እንጂ ብልፅግና አልተመረጠም ያለው ህወሓት መንግሥትን አስጠነቀቀ
ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚኒስትሮች ሹም ሽር ሲያደርጉ የህወሃት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር ከሓላፊነት መነሳታቸው ህወሓትና ደጋፊዎቹን እያበሳጨ ነው።
በተጨማሪ የህወሃት ከፍተኛ አመራር የሆኑት በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) ከስልጣን እንደሚነሱ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ታውቋል።
ከእነዚህ እርምጃዎች በመነሳት ህወሃት ባወጣው መግለጫ አባላቱን ከፌደራል ከፍተኛ የሓላፊነት ደረጃዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማንሳት እርምጃ ህግን የጣሰና ችግርም የሚያስከትል ነው ሲል አስጠነቅቋል።
የህወሓትን መግለጫ ተከትሎ የዶ/ር ዐቢይ ብልፅግና ፓርቲ የተደረገው የተለመደ ሹም ሽር በመሆኑ ከብሄር እና ከፖለቲካ ጋር ማገናኘት አይገባም ሲል ወቀሳውን የሚያጣጥል ምላሽ ሰጥቷል።
ዶ/ር ሰለሞን ኪዳነ በአዲስ አበባ በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚገኙ የህወሓት ካድሬዎችና የሥራ ሓላፊዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እየተነሱ በሌሎች አባል ባልሆኑ እየተተኩ ነው በማለት ይከሳሉ:: “አዲስ አባባ ላይ እንደ ኢህአዴግ ነው የተወዳደርነው። ኢህአዴግ እስካሸነፈ ድረስ ህወሓት 25 በመቶ ቦታ፤ እኩል የማስተዳደር ስልጣን አለው። ይህንን አሰራር ማፍረስ ማለት የከተማውን መንግሥታዊ አስተዳደር መዋቅር ማፍረስ ማለት ነው” በማለትም አክለዋል።
በዚህች ላለፉት 28 ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሲሸጋገር ስሙን ብቻ ሳይሆን ርእዮተ ዓለሙን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ን በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ለውጦታል:: የተገፋው ህወሓት ይህ ሂደት ህገ-ወጥ ነው በማለት ብልፅግናን የማይቀላቀል መሆኑንን ማሳወቁ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ይበልጥ እንዳሰፋው አይዘነጋም።
የህወሓት አባላትን ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሃላፊነት የማንሳት እርምጃም የዚህ መካረር ውጤት ነው ያሉት የህወሓቱ ዶክተር መንግሥት እርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ህወሃትን ማማከር ነበረበት ብለዋል። “ይሄ የፖለቲካ ስልጣን ነው። ህዝቡ ህወሃትን እና ፕሮግራሙን ነው የመረጠው። ህወሃትን ሊወክሉ የሚችሉ ሰዎችን ህወሃት ራሱ ብቻ ነው ሊያቀርብ የሚችለው። በስመ የትግራይ ተወላጆች መተካት አይቻልም። ይሄ አካሄድ ሕገ-ወጥ ነው። የብሄር ተዋጸኦ ነው ያስመሰሉት” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ህወሓት በህዝብ ተመርጦ እንጂ ለምኖ የመጣ ድርጅት አይደለም ያሉት መቀሌ የመሸገው ቡድን አባል ህወሓት ከብልጽግና ጋር አልዋሃድም ስላለ ብቻ በትግራይ ህዝብ የተመረጡ ግለሰቦችን እየለዩ ከቦታቸው ማንሳት የህዝብ ድምጽ እንደመቀማነት ይቆጠራል ከማለታቸው ባሻገር “የተመረጠው ኢህአዴግ እንጂ ብልጽግና አይደለም” ሲሉም አዲሱን ፓርቲ አጣጥለዋል።
በሌላ በኩል የህግ ባለሙያና የህገ መንግስት ምሁር አቶ ምስጋነው ሙሉጌታ ስልጣን ላይ ያለው መንግስትን የመሰረተው ግንባር ሊፈርስ እንደሚችልና አብላጫ ድምጽ ያለው ፓርቲ በስልጣን ሊቀጥል እንደሚችል ተደንግጎ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: በሌሎች አገራትም ይሄ የተለመደ እንደሆነ ገልጸዋል።
ሆኖም ከሌሎች አገራት ልምድ በሚለይ መልኩ በኢትዮጵያ የሆነው፤ ጥምረቱ ብቻ ሳይሆን የፈረሰው ጥምረቱን የፈጠሩት አባል ድርጅቶቹ ራሳቸውን ማክሰማቸው እንደሆነ ጠቁመው ፤”የሆነ ህገ-መንግሥታዊ ሂደት መኖር አለበት። የፓርላማ አባላት የአዲሱ ብልጽግና ፓርቲ አባል ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚፈልጉ መጠየቅ አለባቸው። ቁጥራቸው የበዛና የበላይነቱን የሚይዙ ከሆነ ችግር የለውም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ህገ-መንግስታዊ ሂደቱን ያሟላ ነው ይባላል” ብለዋል።
አዲሱን የምረጫ ህግ በመጥቀስ ይህንን ያልተቀበሉ የፓርላማ አባላት በግል አልያም በተቀዋሚነት መቀጠል እንደሚችሉም አቶ ምስጋናው ገልጸዋል። በዚህ መሰረት ከ547 የፓርላማ አባላት ምን ያህሎቹ ብልፅግናን ተቀብለው መቀጠል እንደሚፍልጉና መቀጠል እንደማይፈልጉ ፓርላማው፤ ግልጽ ማድረግ ነበረበት ካሉ በኋላ ብልፅግና ሆነው የሚቀጥሉት አብላጫ ድምፅ እንደሚይዙ ምንም ጥርጥር የለውም።
የህግ አግባብን ተከትሎ ነገሮችን ማድረግ ያልፈለጉት ለምን እንደሆነ ግልፅ አይደለም የሚሉት አቶ ምስጋናው “የፖለቲካ ሹመቶቹ ብዙም አያሰደንቅም” የሚሉት የህግ ምሁሩ፤ አንድን ሚኒስትር መሻር የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ስለሆነ ያን ላለማድረግ አይገደድም ሲሉ አስታውቀዋል።
ሕዝብን የዋሸው መንግሥት የታገቱ ተማሪዎች ቤተሰቦችን ማስፈራራት ጀመረ
በታጣቂዎች የታገቱት (ኦነግ ሽኔ ጦር እንደሆነ ይታመናል) የአማራ ተማሪ ወላጆች የደረሱበት ሳይታወቅ ሳምንታት በተቆጠሩበት ሂደት ላይ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት የተማሪዎቹን ወላጆች እና ቤተሰቦችን እያስፈራሯቸው መሆኑን የታጋች ቤተሰቦች ለኢትዮጵያ ነገ ገለፁ::
በድህነት ውስጥ ሆነው በትምህርት ራሳቸውን አንፀው ሕይወትን ለማሸነፍ እና ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ለመርዳት ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩት ተማሪዎች መታገታቸው ሳያንስ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክረተሪያት ቢሮ ሓላፊ አቶንጉሱ ጥላሁን በይፋ ተማሪዎቹ በብዛት መለቀቃቸውንና ቀሪዎቹንም ለማስለቀቅ መንግሥት ድርድር እያደረገ ነው በማለት ሐሰተኛ መረጃ መስጠታቸውና ሕዝብንም በይፋ መዋሸታቸው አይዘነጋም::
መንግሥት በዚህን ያህል ድፍረት በእገታው ዙሪያ ከዋሸ አስር ቀናት ቢሆንም ተለቀዋል የተባሉት ተማሪዎችም ሆኑ የታገቱት ተማሪዎች እስካሁን ድረስ ከቤተሰባቸው ጋር ያልተገናኙ ከመሆኑ ባሻገር በሕይወት ስለመኖራቸው የሚጠቁም አንዳችም ፍንጭ አልተገኘም::
በአደባባይ ሕዝብን መዋሸት የለመደው የህወሓት መራሹን መንግሥት አሠራር ያለሀፍረት የደገመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ከሰራው ከባድ ስህተት በተጨማሪ የታገቱ ልጆቻቸው እንዳልተፈቱ በማረጋገጥ ለመንግሥት “ልጆቻችንን አድኑልን” እያሉ መንግሥትና ሕዝብን በእንባ እየተማፀኑ ያሉ ወላጆችን ማስፈራራት ጀምሯል::
የታገቱት ተማሪዎች ሁሉም የአማራ ክልል ተወላጆች በመሆናቸው ወላጆች አፈናው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮም ሆነ ከቀናት በኋላ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ስለመለቀቃቸው ከገለጹ በኋላም ደረጃ በደረጃ ወደ አማራ ክልል የመንግሥት ቢሮዎች በመሄድ በሚጠይቁበት ወቅት ተገቢውን ምላሽ ለማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ::
በጉዳዮ ላይ በቂ መረጃ ለማግኘትና ያለውን እውነት ለማወቅ ወደ አማራ ክልል የተለያዮ ዞኖች ስልክ ለደወለው የአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ የታገቱ ተማሪ ወላጆችና ቤተሰቦች በተለይ የአቶ ንጉሡ የውሸት መግለጫ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ካስነሳ በኋላ ፣ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ችግሩን ለመቅረፍና ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ከመጣር ይልቅ “ጉዳዩን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋችሁት ነው:: መንግሥታችን በአግባቡ ሥራውን እንዳይሰራ እንቅፋት እየሆናችሁ ነው:: አርፋችሁ ብትቀመጡ ነው የሚጠቅማችሁ” የሚል ማስፈራሪያ እያደረ ሱባቸው መሆኑን ይፋ አድርገዋል::
በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመጠየቅ እና የክልሉ መንግሥት ጫና ፈጥሮ ልጆቻቸውን እንዲያፈላልግላቸው የሚያደርጉት ጥረት እውነታውን በአደባባይ ገልብጦ ያቀረበውና የኢትዮጵያ ሕዝብን የዋሸው መንግሥት ከመተባበር ይልቅ ወላጆችን ማስፈራራቱ የአፈናው ሰለባ ቤተሰቦችን ጨምሮ ብዙዎችን ክፊኛ እያበሳጨ ነው::
አቶ ንጉሡ ጥላሁን በመግለጫቸው መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ እየተደራደረ ነው ማለታቸው መንግሥት ሕግ ባለበት አገር በዶምቢዶሎ ከተማ እገታውን ከፈጸመው ታጣቂ ቡድን ጋር ቀጥተኛ አልያም ድብቅ ግንኙነት ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄን አጭሯል::
ገዳዮ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ምርመራ ተጀመረ
ኖቭል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ሥራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጀመረ።
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታን አስመልክቶም ሰፊ መግለጫ ሰጥቷል። የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን በተሰኘው ከተማመከሰቱን ይፋ አድርጓል። ይህ አደገኛ ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መከላከል ዝግጅት መደረጉን ኢንስቲቲዩቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር የአየርና የየብስ ትራንሰፖርት ትስስር የምታደርግ በመሆኑ በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገራት ጋርም በአየር መንገዷ አማካኝነት በርካታ በረራዎች ስላላት ጥንቃቄው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል::
በማንኛውም የአየር መንገድ በኩል ለሚሄዱ መንገደኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ስለ በሽታው መረጃ መስጠት እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡት ደግሞ በበሽታው ተይዘው ሊሆን ስለሚችል በዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ሥራ በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መተግበር ጀምሯል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተለያዩ የዝግጁነት ሥራዎችን የጀመረ ከመሆኑ ባሻገር ለክልሎች እና ለባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን የዝግጅት ስራዎች እንዲያከናውኑ የቅድመ ዝግጅት መልዕክት አስተላልፏል።
በቻይና እንደተከሰተ በተገለፀው ቫይረስ እስከ ዛሬ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላ በተለያዩ አገራት 581 ታማሚዎች መያዛቸውን የወጣው ሪፖርት ያሳያል።እስካሁን ከእነዚህ ታማሚዎች ውስጥ 26 የሚሆነት ህይወታቸውን በበሽታው አጥተዋል::
ሁለት ጊዜ የቆይታ ዘመናቸው ከህግ ውጪ የተራዘመው ታከለ ኡማ 19 አዲስ ሓላፊዎች ሾሙ
የሥራ ዘመኑ ቢጠናቀቅም ሁለት ጊዜ ከህግ አግባብ ውጪ የተራዘመለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት ዛሬ በአዳዲስ ሹመቶች ተንበሽብሿል:: ለምርጫው በከፍተኛ ሁኔታ ሽር ጉድ እያሉ የሚገኙት ኢንጅነር ታከለ ኡማ ለከተማዋ ምክር ቤት የተለያዩ የሥራ ሓላፊነት ያቀረቡትን ሹመት ምክር ቤቱ እንዳፀደቀውም ተረጋግጧል።
በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት በተከናወነው መደበኛ ጉባዔ ላይ ታዳሚ ከነበሩት 89 የምክር ቤት አባላት ውስጥ አዲሱን የታከለ ኡማ ሹመት በ79 ድጋፍ፣ በ3 ተቃውሞ እና በ7 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቀውታል።
ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀው አዳዲስ ባለሥልጣናት፡-
1 . ኢንጅነር እንዳወቅ አብጤ – በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ
2. ኢንጅነር ሰናይት ዳምጠው- የቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ
3. ወይዘሮ ነጂባ አክመል – የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ
4 አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ – የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ
5 አቶ አብዱልቃድር መሀመድ – ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
6 ወይዘሮ ኤፍራህ አሊ- የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ
7 አቶ ሀይሉ ሉሌ – የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊ
8 አቶ ዘላለም ሙለታ – የትምህርት ቢሮ ሃላፊ
9 ኢንጅነር ደመላሽ ከበደ- የኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ
10 አቶ ስጦታው ታከለ – የትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ
11 አቶ ነጋሽ ባጫ- የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ሃላፊ
12 አቶ ይመር ከበደ – የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ሃላፊ
13 አቶ መኮንን ተፈራ- የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ
14 አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ- የንግድ ቢሮ ሃላፊ
15 አቶ አዱኛ ደበላ- የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ
16 አቶ አብርሃም ታደሰ- የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ
17 አቶ ዋቁማ አበበ – የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር
18 አቶ ታምራት ዲላ- የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር
19 አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር – የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ሆነው በመመረጣቸው በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ጥቅሟን አስጠበቀች እየተባለ ነው
በስዊዘርላንድ ዳቮስ የተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ኢትዮጵያ ጥቅሟን ያስጠበቀችበት እና አዳዲስ ግንኙነቶችን ያጠናከረችበት ነው መባሉ ተሰማ ።
በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራው የልዑካን ቡድን በዳቮሱ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ያደረገውን ተሳትፎ ማጠናቀቁም እየተነገረ ነው።
የአሁኑ ፎረም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የገነባቻቸው የሁለትዮሽ እና ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ያደሰችበት እና አዳዲስ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን መጀመር የቻለችበት ነው ቢባልም አገሪቱ አተረፈች የተባለውን ጥቅም በተመለከተ የቀረበ ዝርዝር ሪፖርት ግን የለም።
የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት እና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብይ ኤፍሬም፤ በፎረሙ ላይ ከተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ኩባንያዎች ጋር ትስስር መፍጠር መቻሉን ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓለም፣ በአፍሪካ ብሎም በቀጠናው አገራት በኢኮኖሚው አውድ ውስጥ ባላት ድርሻ እና ሚና ለኢኮኖሚ አጋርነት እና ትስስር የምትመረጥ አገር መሆኗ የታየበት መድረክ ነው በማለት ለፋና ሲናገሩ ተደምጠዋል።