ጎበዝ ትንሽ ዞር ዞር ብየ ብመጣ አዲሳባ አመል ቀይራ ጠበቀችኝ፤ የኑሮ ውድነቱ ጨርቅ አስጥሎ ያሳብዳል ፤ለነገሩ ጨርቅም ስለተወደደ የዛሬ እብድ ጨርቁን አውርሶ እንጂ ጨርቁን ጥሎ አያብድም፤
ባለፈው ከፍተኛ የጥብስ ፍቅር ያደረበት እንግዳ መጣብኝ ፤ ኮንደሚኒየማችን ስር ባለው ስጋ ቤት ስሮጥ ሄጄ ፤ ሻጩን
” እስቲ ያምሳ ብር ቁረጥልኝ ” አልኩት::
ሻጩ፤ አከሙዝየም የተሰረቀ ጎራዴ የመሰለውን ቢላዋ፤ በሌላ ፤ቢላዋ እየሞረደ በንቀት ስያየኝ ቆይቶ የሚከተለውን ቃል ወረወረ;-
” ቶንቦላ ነው?”
በዚያ ላይ ወበቁና አቧራው! በሃያ ሁለት ማዞርያ በአቧራው ምክንያት እግረኛው ሁላ መደማመጥ እንጂ መተያየት አቁሟል :፤መንግስት የአቧራውን ምርት በዚህ መጠን ለምን ፈለገው? ምናልባት ፤መነፅር በማዞር ፤ መኪና በማጠብና ጫማ በመጥረግ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማበረታታት ይሆን?
ባለፈው ትቢያና ላብ እያፈራረቀ ሲመገብ በመሰንበቱ ሳቢያ፤ ከግራጫነት ወደ ዳልቻነት የተለወጠ ሸሚዜን ለማሳጠብ ወደ ላውንደሪ ቤት ሄድኩ፤ ባለ ላውንደሪዋ ሴትዮ ፤ ሸሚዜን ጠረጴዛ ላይ አጋድማ፤ በዘንግ እያገላበጠች ስትመረምረው ከቆየች በሁዋላ፤
“ የማይደብርህ ከሆነ በብርድልብስ ዋጋ ልናጥብልህ እንችላለን”
ሰው ተጨካከነ ጎበዝ!
ብዙ ሰው በመንግስት ተስፋ እየቆረጠ አማራጭ ፓርቲዎችን ተስፋ እያደረገ መሄዱ አሳሳቢ ነው ፤ በቅርቡ ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ “ የኢዜማ “ በሚል ርእስ የለቀቀው ዘፈን በህዝብ ዘንድ መወደዱ ለዚህ አንድ ማሳያ ይመስለኛል ፤
በዚያ ላይ የመኪና ስርቆት የደረሰበት ደረጃ አስከፊ ነው፤ ሌቦች የቆመ መኪና ወስደው አርደው፤ ሆድ እቃውን ሶማሌ ተራ ላሉ አከፋፋዮች ይቸረችሩታል ፤ ጎማውን ደግሞ በመጭው ምርጫ ማግስት ለተቃውሞ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሸጡታል፤
በከተማ መኪና ስርቆት የተባባሳውን ያህል በገጠር የፈረስ ስርቆት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ፤ ህብረተሰቡ የአጎቴን አይነት ጥንቃቄ ቢያደርግ ተገቢ ነው ባይ ነኝ፤ የሆነ ጊዜ ላይ ማንኩሳ ውስጥ አጎቴ፤ ለቅምቀማ ከመሰማራቱ በፊት ፈረሱን ጠጅ ቤቱ በር ፊትለፊት አሰረው ፤ በዚህ አልረካም ፤ የፈረሱን እግር በረጅም ሰንሰለት አስሮ ፤ከራሱ ከስክስ ጫማ ጋራ በካቴና አቆራኝቶት ወደ ጠጅ ቤት ገብቶ ዘና ብሎ ተቀመጠ ፤
ጠጅ ሻጯ ምንትዋብ
“ ይሄ ጥንቃቄ ትንሽ አልበዛም?” ብትለው፤
“ተይ ባክሽ! በህሗላ አፋልጉኝ ተማለት አፋቱኝ ማለት ይቀላል”