ጀነራል አሳምነው ፅጌ (ነፍሱ በሰላም ትረፍ) ከመፈታቱ በኋላ፣ ከመሞቱ በፊት የተናገራቸውን ንግግሮች አድምጫለሁ። የምወደው አይነት ተናጋሪ ነው – የኔው ቢጤ በቀጥታ የሚናገር የግንባር ስጋ!
ከንግግሮቹ አንዱ የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ያደረገው ነው። የሃይማኖት አባቶቹ በችግር ዳር ዳር እያለፉ ቢያስቸግሩት “…. እስኪ አባቶች እውነት ተናገሩ። ካልሆነም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ብትሞቱስ….” ሲል አምርሮ የተናገረውን ንግግር ከሰሞኑ ያየሁት ነገር አስታወሰኝ።
ነገሩ እንዲህ ነው። የኢሳት ዜናን እያዳመጥኩ ነው፣ አቡነ ማቲያስ የሚመሩት ስብሰባ ላይ በጥምቀት ከጎንደሩ የመቀመጫ መደርመስ በቀር የደረሰ ተጨባጭ ነገር እንዳልሰሙ ይናገራሉ። የኢሳቱ ጋዜጠኛ ጌራ አቡኑን ይጠይቃል “በሃረር እና በሌላ ቦታዎች ረብሻ ነበረ ይህን እንዴት በመግለጫዎት አላነሱም? ሴት ተማሪዎችም ታግተዋል እናንተ ይህን በተመለከተ ምንም የማትሉት እንዴት ነው?” ይላል።
አቡነ ማቲያስ ይመልሳሉ “በዜናኮ አይዘገብም፣ እኛ ከየት እንሰማለን የጎንደሩንም በተባራሪ ወሬ ነው የሰማነው” ይላሉ። አጃኢብ አለማለት አይቻልም!
እዚህ ሃገር ማንኛውም መንፈሳዊ ደረጃ፣ የትኛውም ሽምግልና የማይረዳው ችግር ገጥሞናል! እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን የራሷ ቴሌቭዥንና ጋዜጠኞች አሏት፣ የራሷ መዋቅር እና የትዕዛዝ ተዋረድም አላት። በዚህ ተዋረድ ወሳኝ ነገሮች ሪፖርት ይደረጋሉ። ጥምቀት ለቤተክርስቲያኗ ወሳኝ በዓል ነው፣ ስለዚህ በጥምቀት የሆነ ነገር ሪፖርት መደረጉ አይቀርም፨ “አባታችን” ደግሞ ከወደ ጎንደር የሚመጣ ወሬ ብቻ ነው በተባራሪም ቢሆን የሚደርሳቸው¡
በገዳዮች እጅ ስለገቡት ምስኪን ሴቶችም አልሰሙም¡ ለምን ቢባል መልሳቸው “በቲቪ አልተወራም ነው”። አይ ብለህ ከተከራከርክ ቁጣ ይከተልሃል። አብነ ማቲያስ ቱግ ብለው “ማቲያስ አላበደም፣ የምልህን ስማ” ሲሉ ሰምቼ አውቃለሁ።
እንደ እውነቱ ግን የተማሪዎቹ ጉዳይም ሆነ የጥምቀቱ ረብሻ ግን እሳቸው አይነግረንም ባሉት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም፣ በተዓማኒው የዜና አውታር VOAም ተዘግቧል። መርጦ መስማት፣ የሰው ፊት አይቶ ማዳላት የእግዚአብሄር ሰው መገለጫ አልነበረም…. ምን ያደርጋል ቁልቁለታችን ጥልቅ ነው! በታገቱትተማሪዎች ምክንያት የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሰው ታዝቤያለሁ……
|| ከፌስ ገጿ የተወሰደ ||