የመንግስት ዋና ተግባር የዜጎችን ደህነት ማስጠበቅ ነው:: መንግስት በህዝብ፤ ለህዝብ የተቀጠረ ዘበኛ ነው ማለት ይቻላል:: ዘበኛ ቤቱንና ቤተሰቡን ካጥቂ መታደግ ካልቻለ ወይም ከለገመ ይባረራል:: አለያም ከሌባ ጋር ተመሳጠረ ተብሎ ይከሰሳል::
ላለፉት በርካታ ወራት ዘበኛው በር ላይ የለም ፤ ወይ ደግሞ ከባለቤቶች ቀድሞ ይተኛል ፤ አለያም ከሌባው ጋር ሲወዳደር አቅመቢስ ነው፤
ባገሪቱ ወንጀል ይፈፀማል:: ወንጀል ፈፃሚዎች ወንጀላቸውን እንደ አኩሪ ሙያ እንደ ሰርቶ ማሳያ ባደባባይ ይኮሩበታል :: ባንፃሩ ወንጀለኛ ለፍርድ ሲቀርብ ከተመለከትን ብዙ ጊዜ ሆነን!
ተማሪ አፍኖ መውሰድ፤ መረን የለቀቀ ወንጀል ነው :: መንግስት የተጠቂዎችን ብሶት አሳስቦት፤ እጅግ ጥንቃቄና ጥበብ የተሞላ ዘመቻ በማድረግ ሊታደጋቸው ይገባል፤
አሁን ያለው፤ ጭው ያለ ዝምታ ግን ያንድ ባላገር ተሳፋሪን ወግ የሚያስታውስ ነው፤
አንድ ባላገር ከወሎ ወዴ አዲሳባ ይመጣና ታክሲ ይሳፈራል:: ወደ መውረጃው ሲቃረብ
” እስጢፋኖስ ላይ ወራጅ አለ” ይላል፤
ምኒባሱ ግን የባላገሩን ጥያቄ ቸል ብሎ ጉዞውን ቀጠለ::
” ልጄዋ! ወራጅ አለ ቲሉህ አትሰማም ወይ?
ምኒባሱ አሁንም አልቆመም፤
ባላገሩ ምርር ቢለው እንዲህ አለ፤
” ነገሩ እንዴት ነው?! ሹፌሩ ወርዷል’ንዴ?”