“ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን መንጠራራት…” || ታምሩ ገዳ

“ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ለመሆን መንጠራራት…” || ታምሩ ገዳ

አንዳንድ ሰዎች ጥቅም፣ ፍራንካ እና ዝናን ለማግኘት ሲሉ ብቻ ያልሆኑትን ለመሆን፣ የማደያርጉትን እንደሚያደርጉ በቅቤ አፋቸው ብዙዎችን ሲያጭበረብሩ፣ የብዙዎችን የተከበረ ስም፣ ክብር እና ባህልን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

የሀያ ስምንት እመቷ አውስትራላዊት አናቤል ናታሊ ጊብሰን(ቤል ጊብሰን) በብዙዎች ዘንድ በምላሷ ጤፍ መቁላት ፣ወፍ ከሰማይ ማውረድ የምትችል የዘመኑ ወጣት ስትሆን ቀደም ባለ ጊዜ ጤናማ ምግብ ለጤናማ ሰውነት የሚል የጤና ፕሮግራም በማዘጋጀት ትታወቃለች።

ታዲያ ይህቺ በወዟ ሳይሆን በአቋራጭ የህይወት መሰላል የተሳካላት ታዋቂ ወጣት በጭራሽ ያልነበራትን በሽታ በመመኘት”ከጭንቅላት ካንሰር /Brain Cancer/ በሽታ በምግብ ብቻ ተፈወስኩኝ” በማለት ብዙዎችን አጨናብራለች።ይሄም ብቻ አያበቃም “ከሽያጭ ያገኘሁትን ሶስት መቶ ሺህ ዶላር ለበጎ አድራጎት ሰጥቻለሁ” በማለት ያላደረገችውን ለመሆን የሄደችበት መንገድ ከአውስትራሊያ የህግ አስከባሪዋች ጋር ያጋጫት ሲሄን በእዳ እና በቅጣት የአምስት መቶ ሺህ ዶላር እዳ ተቆልሎባታል።

ብዙዎችን ለማጭበርበር የተካነው የቢል ጊብስን እይምሮ እና እግሮች በአውስትራሊያ ከሚኖሩ የኦሮሚያ ተወላጆች ዘንድ ጎራ ብሎ “እኔ በአውስትራሊያ ውስጥ በሚገኙ በኦሮሞ ቤተሰብ በገድፌቻ ያደኩኝ ነኝ፣ስሜም ሳቦንቱ ይባላል( በኦሮሚኛ አገሩን እና ባህሉን የሚወድ ማለት )፣ለኦሮሞዎች ትግል ከአራት አመት በላይ ታግያለሁ፣ትግላቸው ትግሌ ነው፣እናንተ የኦሮሚያ ልጆች ለማንነታችሁ ታገሉ ፣ስትተኙ እንኳን ሁለቱንም አይኖቻችሁን እንዳትጨፍኑ…ወዘተ)በማለት የጅዋር መሐመድ እና የዶ/ር አብይ አህመድ ስሞችን በመጠቃቀስ፣” ኦሮሚያን ነጻ አውጧት…” በማለት ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ትንሽ የኦሮምኛ ቃላት ጣል አድርጋ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ቃለምልልስ ብጤ አድርጋለች። ለማህበረሰቡም ድግስ ያለ ገንዘብ እንደምታሰባስብም ተናግራለች።

እንደ ድይሊ ሜል ጋዜጣ ሰሞነኛ ዘገባ እዳዋን ለመክፈል ባለመቻሏ ቤት ንብረቷ እንዲሸጥባት በፍርድ ቤት ማዘዣ መሰረት ባለፈው እሮብ በፓሊስ የተያዘባት ቤል ጊብሰን ሁኔታን የተመለከቱ በሚልቦርን የኦሮሞ ኮሚኒቲ ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር ታረቀኝ ጨመዳ” ግለሰቧ ወደ ማህበረሰባችን ዘንድ አልፎ አልፎ ስትመጣ ስመለከታት የአንዱ ወዳጅ/ሚስት ትሆናለች ብዬ ነበር የገመትኩት እንጂ እንደዚህ አይነት ተሳትፎ ውስጥ ስለመኖሯ በጭራሽ አላውቅም። “በማለት ከኦሮሚያ ኮሚኒቲ ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት እንደሌላት አስረግጠው ገልጸዋል።

ቃለምልልሱን ያደረገላት የሻቦ ሚዲያ አፈቀላጤ በበኩላቸው “የ ሳ ቦንቱ/ጊብሰን የቆየ ታሪኳን ጠንቅቀን እናውቃለን፣አሁን ግን ጊብስን በብዙ መልኩ ተለውጣለች”በማለት ለደይሊ ሜል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቀደም ያለው የጊብሰን ቃለምልልስን የተመለከቱ አንዳንድ ወገኖች ” ጊብሰን ጀግናችን ነሽ ፣ኮራንብሽ”ያሏት ሲሆን አንድ አስተያየት ስጪ በበኩላቸው “የዚህች ሴት የተጨፈኑ ላሞኛችሁ ንግግሮችን እባካችሁ አትስሙ፣አትታለሉ” ሲሉ ይመክራሉ።ሌላ አስተያየት ስጪ ደግሞ ” ይህቺ ሴት አነጋገሯ እና ሁኔታዋ ከኦሮሞ በላይ ኦሮሞ ሆኖ ፣ስለኦሮሞ ማህበረሰብ ማንነት እና ምንነት ለመቀስቀስ፣እና ለማቀንቀን የሚደረግ መንጠራራት ነው “በማለት አካሄዷን ኮንነውታል።

ቃለ ምልልሱን ያደረገላት እርሷም ብትሆን በአፋን ኦሮሞ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሰጠችው የአስራ አንድ ደቂቃ ቃለምልልስ ከዩቲዩብ ላይ እንዲነሳላት መጠየቋን ደይሊ ሜል አክሎ ገልጿል።

የካንሰር ህመም ሳይኖራት” ከህመሜ በራሴው ጥረት፣በአማራጭ መድሀኒት እና ምግብ አማካኝነት ድኛለሁ”በማለት የብዙዎችን ልብ ያማለለችው፣በርካታ ሀብት እና ንብረት ያካበተችው ጊብሰን እኤአ 2015 ባደረገችው ቃለምልልስ”ሀሉም ነገር የፈጠራ ነበር”በማለት ያመነች ሲሆን እንዳንድ ሰዎች በበኩላቸው “ዘመድ ካላት ወደ አይምሮ ባለሙያ ጋር ትላክ፣ካልሆነም ለቅጥፈቷ ወደ ዘብጥያ ትወርወር” ሲሉ ተችተዋታል።
(በታምሩ ገዳ)

LEAVE A REPLY