የለውጡ ቡድን አባላት አገር የመምራት ብቃት እንደሌላቸው ኤፍሬም ማዴቦ ተናገሩ
የቀድሞው የአርበኞች ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊና የአሁኑ ኢዜማ አማካሪ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ሥልጣን ላይ ያሉት የለውጡ ቡድን አባላት አገር የመምራት ልምድና ብቃት እንደሌላቸው ገለፁ::
በተለያዮ ክልሎች የሚገኙ የሥራ ሓላፊዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካድሬዎቹ በጠቅላላ ህወሓት አገር ይመራበት በነቀረው የፖለቲካ ቅኝት ተጠፍጥፈው የተሠሩ ይመስል ሁሉም እንድ አይነት መሆናቸውን በተገናኘሁበት አጋጣሚ ታዝቢያለሁ ያሉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ይህ ስሜት እንዳይደበዝዝና እንዳይጠፋ ደግሞ አሁን በአገሪቱ የተንሰራፋው ጽንፍ የያዘ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል::
“እኔ አገሬን ለቅቄ በስደት ከኖርኩበት ሕይወት ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት ከ28 ዓመት በኋላ ነው:: ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እድሜ ላይ 28 ስትቀንስ ትንሽ ልጅ ነው ማለት ነው:: የእኔን ያህል የፖለቲካም የሕይወት ልምድ የለውም:: እኔ በወጣትነቴ በኢሕአፓ ውስጥ አልፊያለሁ፣ የደርግ ዘመን ልጅ እንደመሆኔ ሀይስኩል ብዙ ችግሮች ገጥመውኛል:: በስደትም የተለያዮ ነገሮችን ተጋፍጫለሁ” በማለት ጥር 16 ቀን (ዛሬ) በገበያ ላይ ከዋለችው ግዮን መጽሔት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለምልልስ ያደረጉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ዐቢይ አሕመድ እና ለማ መገርሳ ግን ከላይ በገለጽኩት መንገዶች እና ችግሮች የተፈተኑ አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል::
ከፖለቲካ ብስለትና አጠቃላይ ብቃት አኳያ የለውጡ ቡድን አመራሮች አገር የመምራት ልምድና ብቃት የላቸውም ያሉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በኢህአዴግ ውስጥ የተከሰተውን መከፋፈል ተከትሎ ሥልጣኑን የያዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ብዙ የሠራቸው ስህተቶች አሉ ብለዋል::
እነዚህ ስህተቶች እና ችግሮች እንዲከሰቱ ገፊ የሆኑ ብዙ ምክንያቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሉ የሚሉት እና ኢዜማን ከጀርባ ሆነው በማማከርና በማገዝ ሥራ የተጠመዱት ኤፍሬም ማዴቦ ፓርቲያቸው ለሁሉም ነገሮች በፍጥነት መገለጫ የማያወጣው በሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን አገር የማስተዳደር ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግሮችን ላለማባባስ እንደሆነ ተናግረዋል::
17 ቀን የሚቆየው የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ዛሬ ተጀመረ
የሚከተለው የመደመር የፖለቲካ ርዕዮት ዓለምን በግልጽ ማብራራትና ሕዝብን ማሳመን ያልቻለው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው።
በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ መካሄድ የጀመረው ስልጠና እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚቆይ የተነገረ ሲሆን ዛሬ በተከናወነው የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የከፍተኛ አመራሮቹ ስልጠና ፓርቲው ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና አገራዊ ውህድ ፓርቲ ከተሸጋገረ በኋላ በየደረጃው ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ምንነትና አስተሳሰብ ዙሪያ የተዘጋጀ ነው መባሉንም ሰምተናል።በተጀመረው አገራዊ ለውጥና ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በተገኙ ስኬቶችና የቀጣይ ስጋቶች ላይ አመራሩ የተግባር አንድነት እንዲኖረው ለማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነውም ተብሎለታል።
በሌላ በኩል ለአገሪቱ ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባትና ለቀጣይ ተልዕኮ ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና እንደመሆኑ ፤ ይህንኑ አላማ ለማሳካት በመድረኩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ምንነቱን፣ ባህሪውንና የተገኙ ስኬቶችን በአግባቡ በመገንዘብና በማስፋፋት እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት የውይይቱ አጀንዳ እንደሚሆን የሚጠቁመው መረጃ ፤ ውይይቱ በተለይም የህዝቡን የህግ የበላይነት፣ የማህበራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም በቀጣይ የጋራ አቅጣጫዎች ላይ ለመግባባት የሚያስችል የሃሳብ ልውውጥ እንደሚካሄድበት ታምኖበታል።
በስልጠናው ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልፅግና እስከ ፖለቲካዊ ብልፅግና ያሉ የርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦችና እሳቤዎች ላይ አመራሩ በጥልቀት በሚመክርበት እና ለ17 ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ አመራሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አርቲስት አበበ ባልቻና አምለሰት ሙጬ ለተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ የቦርድ አባላት ሆነው ተመረጡ
በአዲስ አበባ ለተቋቋመው የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያካተተተ የቦርድ አባላት በልዮ ሁኔታ ተመርጠዋል።
የከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደር ከያዝነው ዓመት ጀምሮ የመንግሥት ት/ቤት ተማሪዎችን የምግብ አቅርቦት መሸፈን ከጀመረ ጀምሮ ተማሪዎች በነፃ አገልግሎቱን ሲያገኙ ቢቆዮም በአሠራር ላይ ከፍተኛ ችግር መስተዋል ከጀመረ ሰንብቷል::
በተለይም ከወራት በፊት በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ጥቂት ትምህርት ቤቶች ከምግብ አጠቃቀም ጋር በተፈጠረ ችግር የተወሰኑ ተማሪዎች ለሕመም ተጋልጠው ነበር:: የከተማው መስተዳድር ይህንን ችግር ከምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ጥፋት አለመኖሩን በመግለፅ ክስተቱን ለመሸፋን ሞክሮል::
የኢትይጵያ ነገ ታማኝ ምኔጮች እንደነገሩን ከሆነ የከተማ አስተዳደሩ በውስጥ ማስጠንቀቂያ ጉዳዮ የሚመለከታቸው ሓላጸፈፊዎችንና ሠራተኞችን ማሳሰቢያ ከመስጠቱ ባሻገር በቀጣይ የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ ነበር::
በመሆኑም ችግሩ ስር እንዳይሰድ የሰጋው የታከለ ኡማ አስተዳደር በምግብ አቅርቦት ዙሪያ የሚሠሩ አዳዲስ የቦርድ አባላትና ሓላፊዎችን ዛሬ መርጧል:: በልዮ ሁኔታ የተዋቀረው ቦርድም በብዛት ታዋቂ ሰዎችን ያካተተ ሆኗል:: እነዚህ ዝነኛ ግለሰቦች በመደበኛ ሥራቸው የተጠመዱና ከመደበኛ የምገባ እንቅስቃሴው በከፍተኛ ሁኔታ የተነጠሉ በመሆናቸው ምን ያህል በምግብ ጥራትና ቁጥጥር ዘንድ ሓላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚችሉ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል::
1. ወይዘሮ አለምጸሃይ ጳውሎስ – ሰብሳቢ
2. ወይዘሮ የፍሬዓለም ሽባባው – ምክትል ሰብሳቢ
3. ወይዘሮ አምለሰት ሙጬ
4. አቶ ስኩር ካርዲን
5. አቶ አበበ ባልቻ
6. ዶክተር በድሉ ዋቅጂራ
7. ወይዘሮ ሮማን ታፈሰወርቅ
8. አቶ ጥላሁን ጉግሳ
9. አቶ ያሬድ ሹመቴ
10. አቶ አማን ፍስሃጽዮን
11. አቶ ፍትህ ቶላ
12. ዶክተር ፍሬህይወት ገብረህይወት
13. አቶ ጌጡ ተመስገን
14. ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ
15. ዶክተር መሳይ ገብረማርያም
16. ዶክተር ፈቃዱ ሙሉጌታ
17. አቶ በላይ ካሳ
18. አቶ ሰለሞን መንገሻ
19. ዶክተር ታረቀኝ ታደሠ
20. ሐዋሪያ ዮሐንስ ግርማ
21. ዶክተር ቤቴልሄም ደረጀ
22. ወይዘሮ ዘኒት ይመር
23. ወይዘሮ ሜቲ ታምራት ናቸው።
ቦርዱ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች በምግብና በትምህርት ግብዓት አቅርቦት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የማስተባበርና የመከታታተል ኃላፊነት እንደሚኖረው ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል
እስካሁን 100 ሚሊዮን ብር የወጣበት የወረታ ደረቅ ወደብ ሊመረቅ ነው
ከአንድ መቶ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የወረታ ደረቅ ወደብ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሚቀጥለው ሳምንት ይመረቃል ተባለ።
የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ ስፈጻሚ አቶ እውነቱ ታዬ ፤ የወደብ ልማቱ አገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ያደርገዋል ካሉ በኋላ በአጠቃላይ 25 ሄክታር መሬት ሽፋን የሚኖረው የወረታ ደረቅ ወደብ በመጀመሪያው ምዕራፍ ሦስት ሄክታር መሬት ግንባታ ተጠናቆ በሚቀጥለው ሳምንት ለምረቃ ይበቃል ብለዋል። ቀሪው ሔክታር በቀጣዮቹ ዓመታት እንደሚለማናአገሪቱ ያላትን የደረቅ ወደብ የማስተናገድ አቅም በስምንት እጥፍ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።
የወረታ ደረቅ ወደብ ለሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢ የወጪና ገቢ ንግድን ለማስተናገድ የሚያገለግል ሲሆን፥ አገልግሎት ፈላጊው የነበረበትን እንግልት ይቀንሳል በሚል ታምኖበታል። በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የወረታ ደረቅ ወደብ ከ እስካሁን 100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።
አዲሱ ደረቅ ወደብ ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለአካባቢው የንግድ ማህበረሰብ ለማቅረብም አገልግሎት ይሰጣል። ይህም የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይባክን የነበረውን የጊዜና ገንዘብ ወጪ እንደሚቀንስ ይጠበቃል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሞጆ ደረቅ ወደብን ዋና ማዕከል ለማድረግ 100 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየለማ ሲሆን ከአለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተጨማሪ 30 ሔክታር ለማልማት እየተሰራ ይገኛል።በዚህ መሠረት የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ በጂቡቲ ለወደብ ኪራይ ይወጣ የነበረውን ገንዘብና እንግልትን እንዲቀንስ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተብሏል።
እያንዳንዱ አስመጪ ያመጣውን ኮንቴነር በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ከደረቅ ወደቡ ማንሳት የሚጠበቅበት ቢሆንም ኮንቴነሮች በደረቅ ወደብ ለዓመታት እንደማይነሱ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን ፤ ችግሩ በመንግስት ተቋማት ላይ በስፋት ይስተዋላል።በአሁኑ ወቅት ረዥም ጊዜ የቆዩ ኮንቴነሮች እንዲወጡ ግፊት እየተደረገ ነው።