በኢዜማ ደጋፊዎች እና በአማራ አክቲቪስቶች መሃል እየተቀጣጠለ ወደሄደው አሳሳቢ ግጭት ብዕሬን ከመዞሬ በፊት ቀጥላ ያለችውን ታሪካዊ ክስተት ላስቀድም።
አንድ ክረምት ዩኒቨርሲቲ ተዘግቶ ተወልጄ ወዳደኩበት ራያ ሄድኩ። ጊዜው ወያኔ እና የኢትዮጵያ ምድር ጦር ወታደሮች ቀጣይ የሆነ ጦርነት የሚያደርጉበት ወቅት ነበር። የማይጨው ነዋሪዎች፣ መምህራን ሳይቀሩ፣ ከተማዋን ከወንበዴ ለመጠበቅ ምሽግ ላይ ነበር የሚያድሩት ።
ታድያ አንድ ጊዜ ከሌሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ እጅግ ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ እያለ፣ ቅልጥ ያለ ተኩስ ከተማዋን ያናውጣት ገባ። ወንበዴዎች ገብተው ከወገን ጋር እየተታኮሱ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ዝናቡ፣ በነጎድጓድ የታጃበው መብረቅ፣ ከሞርታር፣ ቢ ኤም እና አየር መቃወሚያ ከሚፈጥሩት ተፈጥሮን ከሚያሸብር ድምፅ ጋር ተደበላልቆ፣ ያቺን ድቅድቅ ጨለማ የተጫነባት ሌሊት የዓለም ፍፃሜ መስላለች።
ጦርነቱ ከአንድ ሰዓት በላይ ሆነው። “ይኸኔ ስንት ሰው አልቋል?” እላለሁ እንደተኛሁ በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆኜ። ድንገት ዝናቡ ቆመና ከከተማዋ መሀል ካለችው ኮረብታ ጫፍ ላይ አንድ ድምጽ ተሰማ። ኮረብታው ላይ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ምድር ጦር አባላት አሉ። ከወታደሮቹ አንዱ ጮክ ብሎ፤ ከኮረብታው ስር ወዳለው ከተማ “ተኩስ አቁም! ተኩስ አቁም! ወገን ለወገን ነው! ወንበዴ አልገባም!” ይላል እየደጋገመ። ወድያው በከተማው አንድ ጫፍ ተኩሱ ረገብ አለ። ቀጥሎም በአቅራቢያው ያለው አካባቢም ተኩስ ቆመ። እንዲያ እንዲያ እያለ ብቻ በ10 ደቂቃ በሚሆን ጊዜ የጥይት ድምጽ ጠፋ። “ሰላም” ሰፈነ።
አዎ። ወገን ለወገን ሲታኮስ ጠላት ጥይት ሳያባክን ድል ይነሳል።
በአሁኑ ሰዓት “ተኩስ አቁሙ!” የሚል ጠፋ እንጂ፣ ወገን ለወገን እየተፋጨ ነው ያለው።
በኢዜማ ደጋፊዎች እና በአማራ አክቲቪስቶች ያለው ጦርነት ኢትዮጵያን ይታደጋሉ ብለን በምናምናቸው ወገኖቻችን መሃል ላይ የተፋፋመ ጦርነት ስለሆነ ከልብ አዝነናል። ያለንበት ጊዜ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታግተው ደብዛቸው የጠፋበት፣ ወላጅ “ለማን አቤት ልበል!” እያለ የሚያለቅስበት ጊዜ ላይ ነን። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በአንዲት ሰንደቅ ዓላማ እና በአንዲት ሀገር በሚያምኑ ወገኖች መሃል የተፈጠረው ግጭት ለአንድነት ኃይሎች የጎን ውጋት ሆኗል። ለምትወዷት ሀገርና ለወገን ስትሉ፣ ግጭቱን አቁሙ!