የታገቱ ተማሪ ወላጆች እያንዳንዷን ደቂቃ በእንባና በሰቀቀን እየኖርን ነው አሉ
በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዮንቨርስቲዎች የተንሰራፋውንና የበርካታ ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፈው የብሔርተኝነቴ እንቅስቃሴን ተከትሎ፤ ከሚማሩበት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ለደህንነታቸው በመስጋት ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ የነበሩ የአማራ ክልል ተማሪዎች ማንነታቸው ባልታወቀ ኃይሎች ከታገቱ ከሀምሳ ቀን በላይ ቢሆናቸውም ምንም ዓይነት መፍትኄ አልተገኘም።
ወላጆች ልጆቻቸው መታገታቸውን ከሰሙ አንስቶ ለሚመለከታቸው አካላት ልጆቻቸውን እንዲመለሱላቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም።
የተማሪዎችን መታገት ተከትሎ ከቀናት በፊት ወደ አዲስ ዘመን ተጉዞ የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢ ከተማዋ ሃዘን እንዳጠላባት ጠቁሞ፤ የታጋች ቤተሰቦች ፊታቸው ጠቁሮ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው እንዳገኛቸውና ቤተሰቦችን ማነጋገር እጅግ አሳዛኝ እንደነበር ዘግቧል።
እያንዳንዱን ቀናት በጭንቀት እያሳለፉ የሚገኙ የታጋች ተማሪ ቤተሰቦችን አነጋግሮ የድረሱልን መልእክት ያስተላለፈው ቢቢሲ የዘገበውን ሰፊ መረጃ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
*መሪጌታ የኔነህ አዱኛ – የተማሪ ግርማሽ የኔነህ አባት ።
መሪጌታ የኔነህ ፡ – ”በጥር 2 ተለቀዋል ስንባል ደስ ብሎን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ከልጆቻችን ጋር አልተገናኘንም። መንግሥትም ያለን ነገር የለም። ገድለውብን ይሆናል ብለን እየፈራን ነው። በዚያ ላይ ልጆቹ አይተውት የማያውቁትን ነገር ሲያዩ ይደነግጣሉ ብለን እናስባለን። ሞተውም ከሆነ እውነቱን ነግረውን ቤተሰብ ጋር ተሰባስበን አልቅሰን እርማችንን ብናወጣ ይሻለናል፤ እንዲህ በየቀኑ ምን ሆነው ይሆን እያልን በሰቆቃ ከምንኖር” ይላሉ።
መሪጌታ የልጃቻቸው መታገት በቤተሰባቸው ላይ ከፍተኛ ጭንቀት ማሳደሩን “ባለቤቴ ጨንቅላቷ ተጨንቆ ጸበል ወስጄ ነው ያከረምኳት” በማለት ገልጸዉታል።
*ወ/ሮ ማሬ አበበ፤ የተማሪ በላይነሽ መኮንን ወላጅ ።
ወ/ሮ ማሬ ፡ – የእጅ ስልክ ስለሌላቸው በላይነሽን በስልክ ካገኙ ሰነባባተዋል። “ስልክ ስለሌለኝ የሆነው ሁሉ የምሰማው ከሰው ነው” ብለዋል። ”እህል አልበላ። ሌት ተቀን አይ ጉድ እያልኩ ነው። እግዜር ቢሰማን፤ መንግሥትም ቢራራልን፣ ልጆቻችን ቢሰዱልን እያልን ነው፤ አሳድጌ አሳድጌ ልጅ የለኝም ማለት ነው?” ሲሉም መልሰው ይጠይቃሉ። ተማሪዎቹን መንግሥት እንዳስለቀቃቸው ሲሰሙ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበረ የሚያስታውሱት ወ/ሮ ማሬ፤ “ወሬ ሆኖ ቀረ እንጂ” በማለት ተማሪዎቹ ተለቀዋል ቢባልም ከልጃቸው ጋር ሳይገናኙ እንደቀሩ ያስረዳሉ።
አቶ ሃብቴ እማኙ፤ የተማሪ ግርማ ሃብቴ ወላጅ አባት።
ልጃቸው ግርማ ፡ – ከታገተ በሶስተኛው ቀን በአጋቾቹ ስልክ ደውሎላቸው እንደነበረ ያስታውሳሉ። “የነበረበትን አልነገረኝም። ብቻ ደህና ነኝ ነው ያለኝ።””ተስፋዬ የነበረው እሱ ነው” የሚሉት አቶ ሃብቴ፤ “እናቱ ቤተ-ክርስቲያን እየተንፏቀቀች እኔም የምሰራው ቅጡ ጠፋኝ። ልጄ የሚያውቀው ነገር የለም፤ የቤት ልጅ ነው። እንኳን የሰው አገር የራሱንም አያውቀው። . . . እናቱም የእሱን ሁኔታ አይታ በቤት ውስጥ ያሉትን ልጆች ልትመራልኝ አልቻለችም” ይላሉ።
አቶ ሃብቴ “የማደርገው ጠፋኝ፤ ከፍ ብል ሰማይ ዝቅ ብል መሬት ሆኖብኝ፤ የእሱን መከራ ሳላይ ብሞት አይገደኝም ነበር” ይላሉ።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው ከታገቱ ተማሪዎች ወላጆች መካከል የተወሰኑትን አነጋግሬአለሁ ብለዋል። ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ፤ እንደ አገር ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት አናሳ በመሆኑ ፈጥኖ መፍትኄ ማግኘት አልቻለም ባይ ናቸው።
«በተለይም አካባቢውን የሚያስተዳድረው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት ትኩረት መስጠትና ተማሪዎችን ማስለቀቅ አለባቸው» በማለት ማሳሰባቸው ይታወቃል።
በሐረር የጥምቀት በዓልን ያወኩ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
የጥምቀት በዓል አከባበርን ተከትሎ በሐረር ከተማ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ፣ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሐረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ይፋ አደረገ።
የክልሉ የሰለምና ፀጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ናስር ዩያ ባሳለፍነው ሳምንት በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዘግይተውም ቢሆን አምነዋል። ሁኔታው የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት የፈጠሩት የፀጥታ ችግር ነው ሲሉም የተለመደ ኢሕአዴጋዊ አቋምን አንጸባርቀዋል።
በተፈጠረው ችግር የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና 7 ሰዎች መቁሰላቸውን ከሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን በመናገር ላይ ነው። በንብረት ረገድም በ11 ህንፃዎች ላይ መስታወት እና የተለያዩ ቁሳቁሶች የመሰባበር እንዲሁም ሁለት ህንፃዎች፣ ሁለት ተሽከርካሪዎችና አራት ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች በእሳት መቃጠላቸውን አስታውቋል።
የሐረሪ ክልል መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ባደረገው እንቅስቃሴ 87 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሞ ከእነዚህ መካከል 63 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ሓላፊው በመግለጫቸው አብራርተዋል።
የተፈጠረው ችግር የክልሉን ህዝብ በሰላም፣ በመቻቻልና በአንድነት የመኖር እሴቱን ለመሸርሸር ያለመ የጥፋት አጀንዳ ነው ያሉት ባለሥልጣኑ፤ ችግሩ ከሃይማኖት እና ከብሔር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም በማለት ተናግረዋል።
በሐረር በዚህ ወቅት ሰላም መስፈኑን በክልሉ ከሚገኙ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶች እንዲሁም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት ለዘለቄታው የክልሉን ሰላም የማስጠበቅ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የከፍተኛ ትምህርት አማካሪዎች ከአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጋር ተወያዮ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪዎች በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ አምባሳደር ቲቦር ናዥ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጋር ተወያይተዋል።
በምክክሩ ላይ በኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት ተነጋግረዋል። የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን መሰረት አድርጎ ሚኒስቴሩ ያከናወናቸው እና ወደፊት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ዋና ዋና የለውጥ ሥራዎች ላይም መነጋገራቸው ታውቋል።
በተጨማሪም የመምህራንና አመራር አቅምን ከማሳደግ አንጻር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ የሁለቱ ሃገራት ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር በሚሰሩባቸው መስኮች፣ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላምና ጸጥታን ከማስፈን አንጻር እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎችን ወደስራ ለማስገባት በትብብር ሊሰሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር ማድረጋቸው ነው የተገለፀው።
አምባሳደር ቲቦር ናዥ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም ዐቀፋዊ ለመሆን ለሚያደርጉት ጥረት እገዛ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፤ በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ ድጋፍና ትብብሮች የሚደረጉበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተለይም ከግል የስራ ፈጣሪዎች ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት አምባሳደሩ፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትስስር ፈጥረው ቢሰሩ ተመራቂዎችን ወደሥራ ማሰማራት እንደሚችሉ እና በዚህ ዘርፍ በአሜሪካ መንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
አምባሳደር ማይክል ራይነር በበኩላቸው አሜሪካ በኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚሠሩ ሥራዎችን ስትደግፍ መቆየቷን ጠቅሰው ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ማረጋገጫ ሰጥተዋል። በውይይቱ ከአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ሐረማያ፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን እና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል::
ነባር የስኳር ፋብሪካዎቹ ውጤታማ እየሆኑ ነው ተባለ
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ነባር የስኳር ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ያመርቱ በመደረጉ ውጤታማ አድርጓቸዋል ሲል የስኳር ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወዩ ሮባ ፋብሪካዎቹ ቀደም ሲል በተቀመጠላቸው መጠንና ጥራት ልክ እያመረቱ እንዳልነበረ ነው የተናገሩት። የአደረጃጀት ችግር፣ ቋሚ የጥገናና የሥራ ጊዜ ተለይቶ አለመተግበርና ሌሎች ችግሮችን በምክንያትነት ቀርበዋል።
የስኳር ፋብሪካዎቹ ሥራ ከጀመሩ በኋላ ለጥገና ስለሚቆሙና ለዚህም የማካካሻ አሰራር ስላልነበራቸው ከታቀደላቸው የምርት መጠን በአማካይ በግማሽ ሲያመርቱ እንደቆዮ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በ2011 በጀት ዓመት በነባር ፋብሪካዎች አሰራር ላይ በተደረገው ለውጥ ችግሮቹ በመቃለላቸው የምርት መጠናቸው በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን አስታውቀዋል::
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘርፉ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ማግኘት አለመቻሉም በውጤታማነቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ተሰምቷል። አሁን ላይም ለዘርፉ በቀጥታ ተግባር ላይ የሚውሉ የትምህርት ሙያዎችን በመለየት ስርዓተ ትምህርት እንዲቀረፅና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር በመዋዋል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ማፍራት መጀመሩንም ከመግለጫው መረዳት ተችሏል::
ለፋብሪካዎቹ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ጥገና መደረግ መጀመሩን ተከትሎም ለውጭ ኩባንያዎች ለጥገና የሚወጣውን ገንዘብ ማዳን ተችሏል ተብሏል።