ከእገታዉ ተቃዉሞ ባሻገር! ምን እንማር? || ታዬ ደንደአ

ከእገታዉ ተቃዉሞ ባሻገር! ምን እንማር? || ታዬ ደንደአ

በወለጋ በአጠቃላይ እና በቄለም ወለጋ በተለይ የፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ መኖሩ ይታወቃል። እጅግ አስከፊ እና ኢሰበአዊ ወንጀሎች በአከባቢዉ ተፈፅሟል። ህዝቡ ከባድ መከራን ሲያስተናግድ ከርሟል። እናቶች እና ህፃናት ህክምና አጥተዉ ሞተዋል። ትምህርት፣ ንግድ እና አጠቃላይ ስራ ሲስተጓጎል ቆይቷል። ብዙዎች ተገለዉ ሬሳቸዉ ተቃጥሏል። በርካታ የመንግስት አመራሮች ተገሏል። ሰዉ ፕላስቲክ እየተንጠባጠበበት በህይወት ተቃጥሎ የመጨረሻዉን የሲቃይ አይነት አይቷል። የደምቢ ዶሎ ፕሬዝዳንትም ታግተዉ መለቀቃቸዉ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ የተማሪዎች መታገት ከፍተኛ ሀዘን ፈጥሯል። ይህን እኩይ ተግባር መቃወም አግባብ ነዉ።

ትላንት በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተማሪዎቹን መታገት ምክንያት በማድረግ ሠልፎች ተደርጓል። ነገር ግን በሰልፎቹ ላይ የተንፀባረቁት አጀንዳዎች ከእገታ ባሻገር ናቸዉ። ተማሪዎቹ ታገቱ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የኦሮሚያና የፌዴራል መንግስታት ብዙ ተንቀሳቅሷል። በጉዳዩ ላይ በክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽንና በፀጥታ ኃላፊ ሁለት ጊዜ መግለጫ ተሰቷል። ሁኔታዉን ለማጣራትም በክልሉ እና በፌዴራል አመራሮች ቦታዉ ድረስ በመሄድ ብዙ ጥረት ተደርጓል። አሁንም ከፀጥታ ኃይሉ እና ከአከባቢዉ ህዝብ ጋር በመሆን ጥረቶች ቀጥሏል። ከሁሉም በላይ የአከባቢዉን ሠላም አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ ነዉ። አሠራሩ ላይ ጉድለቶች ሊኖሩ ቢችሉም ብዙ ተለፍቷል። ሠልፎች ላይ የተንፀባረቀዉ አቋም ግን ይህን እዉነታ ያማከለ አይደለም። አጋቹን ሳይሆን መንግስት ላይ ያነጣጠረ ነበር። ይህ ለምን ሆነ?

መቸም ሌላዉ ቢቀር ያ ሁሉ አመራር የተገደለዉ በመንግስት ፍላጎት ነበር አይባልም። የዉጭ ዜጎችን እና የአጎራባች ክልል አመራሮችን ጨምሮ በአከባቢዉ የብዙ ንፁሃን ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። ይህ ክፉ ጉዳይ ከማንም በላይ የኦሮሚያን ህዝብ እና መንግስት ይጎዳል። ደግሞ እገታ የተጀመረዉ በኦሮሚያ አይደለም። በቅርቡ በአማራ ክልል ስምንት ህፃናት ታግተዉ ከቆዩ በኋላ መገደላቸዉ ይታወቃል። ይህ አስነዋሪ ተግባር የትም በማንም ላይ ቢፈፀም መኮነን አለበት። የሰዉ ልጆች ሁሉ ፀር የሆነን አስነዋሪ ድርጊት የብሔር መልክ ማስያዝ ደግሞ በራሱ ክፋት ነዉ። በጋራ በመጣብን ሀዘን ውስጥ አንዱን አጥቂ ሌላዉን ተጠቂ አድርጎ ያልተገባ ስዕል መሳል ተጨማሪ ሀዘን ቢያስከትል እንጂ አያፅናናም። ከእዉነታም ያፈነግጣል።

ዶር ደለሳ ቡልቻ፥ የቀድሞዉ የደምቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝደንት፣ የታገቱት አማራ ስለሆኑ አልነበረም። ብዙ ኦሮሞዎች በአከባቢዉ ህይወታቸዉንና አካላቸዉን አጥቷል። አምስት የቤንሸንጉል ክልል አመራሮች በአንድ ጊዜ ተገሏል። አሁንም ቢሆን በእገታ ስር ያሉ የአከባቢዉ ሰዎች አሉ። ከማንም በላይ የችግሩ እሳት ያቃጠለዉ የአከባቢዉን ህዝብ ነዉ። ነገር ግን በጋራ መቃም የሚገባንን ክፉ አጋች ትቶ መንግስት ላይ ሠልፍ መዉጣት ምን ማለት ነዉ? ለታገቱት ተማሪዎች ታስቦ ነዉ?

ዓላማዉ ግልፅ ነዉ። እገታዉን በማሳበብ የፖለቲካ አጀንዳን ማራመድ ነዉ። ሰሞኑን በኦሮሚያም ግርግር አለ። ይህን ወደ አማራ የማስፋት ፍላጎት አለ። የተጀመረዉን ለዉጥ ለመቀልበስ የተወጠነ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም። ያ ከሆነ ደግሞ በአጋቹ እና በሠልፍ አስተባባሪዉ መሀከል ስምምነት ሊኖር ይችላል። እገታዉ የአሠላፊ አጀንዳ እንዳይሆን የሚከለክል ሎጂክም የለም። ደግሞም እገታዉን የፈፀመዉ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ጠላትም ሊሆን ይችላል። ፖለቲካ በአጠቃላይ እና የኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በሴራ የተተበተበ ነዉ። በርካቶች ለፖለቲካ ትርፍ ብለዉ በብሔር ስም እና በሰዉ ልጆች ስቃይ ይነግዳሉ። ከዝህ አንፃር የተማሪዎቹ እገታ መንግስት ጫና ዉስጥ ለመክተት የተፈጠረ አጀንዳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ከፍ ሲል ደግሞ ኦሮሞን እና አማራን ማጋጨት ተፈልጓል። የኦሮሞ ተማሪዎች በአማራ ክልል እና የአማራ ተማሪዎች በኦሮሚያ ክልል እንዲገደሉ የተፈለገዉ ሁለቱን ህዝቦች አባልቶ በሁለቱ ኪሳራ ትርፍ ለማግኘት እንደነበር ይታወቃል።

በአጠቃላይ ወንጀልንና ወንጀለኞችን መቃወም አግባብ ነዉ። በዝህ ላይ ፈፅሞ ልዩነት ሊኖረን አይገባም። ነገር ግን በተቃዉሞ ስም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭና ለተጨማሪ ኪሳራ የሚዳርግ አጀንዳን ማራመድ አግባብ አይሆንም። ምንም ጉድለት ቢኖርበትም የኢትዮጵያ ህዝብ ከባድ ዋጋ ከፍሎ ያመጣዉን ለዉጥ ጉድለቱን መሙላት እንጂ ለመቀልበስ መጣጣር ለማንም ትርፍ አያስገኝም።

አሁን በተለይ በወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን። በማንኛዉም ጊዜ ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። ከፊሉ ድንገት ሲደርስ ሌላዉ ሆን ተብሎ ይቀነባበራል። ስለዝህም ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ ምክንያታዊነት እና ሚዛናዊነት ያስፈልገናል። በስሜት በጠላት ወጥመድ እንዳንያዝ! ከእገታዉም ከተቃዉሞዉም እንማር!

ሠላም ዋሉ!

LEAVE A REPLY