አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ከባልደራስ

አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ከባልደራስ

ቅዳሜ ጥር 23 2012 ዓ.ም በገለልተኛ አካላት ስለተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ

በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎችና ሌሎች ንፁሃን ኢትዮጵያዊያን መታገታቸውን በመቃወም የመላው ኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ “እኔ ለእሷ ለእሱ” በሚል መሪ ቃል በመጨው ቅዳሜ ጥር 23 2012 ዓ.ም ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ተጠርቷል፡፡
የሰልፉ አስተባባሪዎች የሆኑት መዐዛ መሀመድ፣ ዮናስ ከድርና ምዕራፍ ይመር የሚመሩት ኮሚቴ ከማንም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያልወገነ የተቆርቋሪ ዜጎች ስብስብ ነው፡፡
የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማም፡-
ምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት ተልዕኮ የሌለው መሆኑ፣ ከማንኛቸውም ፖለቲካ ድርጅት ጋር በቀጥታም በተዘዋዋሪም ግንኙነት የሌለው መሆኑ፣
የሚተላለፈው መልዕክት ሙሉ ለሙሉ ከሰብዓዊነት አኳያ ብቻ መሆኑ፣
በጉዳዩ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ ተሳትፎ በማድረግ ታጋቾቹ በሰላም የሚለቀቁበትን ሁኔታ በሰላም ለመጠየቅ፤
መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ጉዳዩ በፍጥነት እንዳይፈታ እንቅፋት በመሆኑ፣ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቶ ታጋቾቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ግፊት ለማድረግ፣ እንዲሁም ቸልተኛ የሆኑ ባላስልጣናት በህግ እንዲጠየቁ ለማሳሰብ ነው፡፡
ድርጅታችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከላይ የተገለፁትን የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማዎችን ሙሉ ለሙሉ ይደግፋል፡፡ ከዚያም ባሻገር በዕለቱ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ ብሎም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአመለካከትና የማንነት ልዩነቶች ሳይገድባቸው በነቂስ ወጥተው ለታገቱ ወገኖቻችን ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

ከሰላምታ ጋር

እስክንድር ነጋ
የባልደራስ ለእውነተኛና ዲሞክራሲ ሊቀመንበር

LEAVE A REPLY