ከመቶ በላይ የሀሰት ዘገባና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ አካላትና ቡድኖች መኖራቸው በጥናት ተረጋገጠ

ከመቶ በላይ የሀሰት ዘገባና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ አካላትና ቡድኖች መኖራቸው በጥናት ተረጋገጠ

ኢትዮኦንላይን || ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው ከሚንቀሳቀሱ የሶሻል ሚዲያ አውታሮች ውስጥ፣ ሆን ብለው የሀሰት መረጃ እና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ ከመቶ በላይ ገፆች (አካውንት) መኖራቸውን  የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልፅግና ማዕከል (ካርድ) የተባለ ተቋም ገለጸ፡፡ ይህ ሕገ-ወጥ ተግባር በመጪው ምርጫ አደጋ ሊከስት ይችላል ሲል ሥጋት እንዳለው አሳውቋል፡፡

ተቋሙ፣ ላለፉት ስድስት ወራት ባደረገው የማኅበራዊ ሚዲያ የዳሰሳ ጥናት ውስጥ፣ የሀሰት መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ባማሰራጨት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታወቁ ሰዎችም በሀሰት ሥም ተሸፍነው አሉታዊ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ዛሬ ሐሙስ ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም በካሌብ ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር ባከናወነው የፕረስ ጉባዔ ላይ ጠቁሟል፡፡

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልፅግና ማዕከል (ካርድ) ዋና ዳይሬክተር ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉ ለኢትዮ-ኦንላይን በተለይ እንደገለጸው፣ የሀሰት ዘገባና የጥላቻ ንግገር ሥርጭትን ለመቆጣጠር ከ‹‹ፌስቡክ›› ተቋም ጋር እየሰሩ ነው፡፡

ፌስቡክ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የቀጠራቸው ኢትዮጵያዊያን ‹‹ሞድሬተሮች›› አለ ሲል የገለጸው ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉ፣ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚለጠፉ ጽሑፎችን ‹‹ሞድሬት›› የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን፣ ከሚፃፈው ነገር ብዛት አንፃር ግን በቂ አይደሉም፤ ስለዚህ ‹‹ፌስቡክ›› ብዙ ሰዎች በብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቀጥሮ ከሥር ከሥር መከታተልና የጥላቻ ንግግሮችንና የሀሰት ዘገባን ቶሎ ቶሎ ማጥፋት አለበት ሲል ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጿል፡፡

የ‹‹ፌስቡክ›› ተቋም ችግር ብዙ ጊዜ የተለያዩ የጥላቻ ንግግርች ተለጥፈው ሲገኙና ሪፖርት ሲደረጉላቸው፣ ወዲያውኑ ምላሽ አይሰጡም፤ ምክንያቱም፣ የሰው ኃይል እጥረት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያንን የንግግር ዓውድ የሚረዱ ሰዎች እጥረት አለባቸው ብሏል፡፡

‹‹አሁን እኛ እንደ ተቋም፣ ከ‹‹ፌስቡክ›› ተቋም ጋር ግንኙነት ጀምረናል፤ የተወሰነ ጥብቅ ያልሆነ የሥራ ግንኙነትም አለን፤ ከእነርሱ ጋር በተነጋገርነው መሠረት ለኢንተርኔት ጸሐፊዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ በጋራ ሥልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው፡፡

በዚህ መሠረት፣ ‹‹ፌስቡክ›› ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ ያመጣል፤ እኛ ደግሞ ባለድርሻ አካላት ሰልጣኞችን ፈልገን እናዘጋጃለን፤ ይህን የምናከናውነው በሀገራችን የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግሮችን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓውድ ‹‹ፕላት ፎርም›› እንዲመሠረት ነው፡፡

ይህን ችግር መቆጣጠር የሚቻለው እዛው ‹‹ፌስቡክ›› ውስጥ ሆኖ ነው የሚለው ጋዜጠኛ በፍቃዱ፣ ከውጭ ሆኖ ለመቆጣጠር እንኳን በግለሰብና በተቋማት ደረጃ ይቅርና የኢትዮጵያ መንግሥትም ፌስቡክን የመቆጣጠር አቅም የለውም ሲል አስረድቷል፡፡

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልፅግና ማዕከል (ካርድ) የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆነው አጥናፍ ብርሃኔ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተቋማቸው በሰራው የማኅበራዊ ሚዲያ ቅኝት ጥናት፣ ብዙ ተከታይ ያላቸው ከመቶ በላይ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች የሀሰት ዘገባና የጥላቻ ንግግር ሆን ብለው እንደሚያሰራጩ በማስረጃ መያዛቸውን ለኢትዮ-ኦንላይን አሳውቀዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ወደ ሕጋዊ ዓውድ ካልገባ፣ በመጪው ምርጫ ላይ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችልም ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አሁን እኛ የምናደርገውን ጥናት ተንተርሰን እነዚህ እነዚህ ገፆች የሀሰት መረጃና የጥላቻ ንግግሮች በተደጋጋሚ ያሰራጫሉ ብለን ከነማስረጃው ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን ያሉት አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ወደ ትክክለኛው ዓውድ እንዲመጡም ‹‹ኔሚንግ ኤንድ ሼሚንግ›› ማድረግ አንዱ ሥልታችን ነው፤ የጥላቻ ንግግርና የሀሰት ዘገባ በየትኛውም የዓለማቀፍ ሕግ ወንጀል መሆኑን በመጀመሪያ በማሳወቅ ወደ ተጠያቂነት ማምጣት ደግሞ ዋና ዓላማችን ነው፡፡

አንድን ብሔር፣ አንድን ሃይማኖት፣ አንድን ፆታ ዒላማ አድርገው ፍጅትና መገለልን የሚሰብኩ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብለን እናምናለን፤ እነርሱም ይህን ተገንዝበው ወደትክክለኛው መስመር እንዲገቡ እንፈልጋለን ሲሉ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ብልፅግና ማዕከል (ካርድ) የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፍ ብርሃኔ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

LEAVE A REPLY