ዶ/ር ዐቢይን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከታገቱ ተማሪ ወላጆች ጋር ተወያዮ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች በቅርቡ ከታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወላጆች ጋር መወያየታቸው ተሰማ።
በዚህ ውይይት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች በተጨማሪ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የተማሪዎቹ የትውልድ ቦታ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
የታገቱት ተማሪ ወላጆች በዚህ ወቅት የልጆቻቸው አድራሻ እስከጠፋበት ዕለት ድረስ የነበራቸው የስልክ ልውውጥ ምን እንደሚመስልም ጉዳዩን በሚመለከት የተቋቋመው ግብረ ኃይልን እየመሩት ነው ለተባሉት ሓላፊዎች አስረድተዋል።
ወላጆቹ በቅድሚያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በመገኘት ስለሁኔታው መወያየታቸውን አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጠቁመው ፤ ግብረ ኃይሉን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በነበራቸው ቆይታም መንግሥት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት እያከናወነው ያለውን ተግባር ለወላጆች በዝርዝር እንዳብራሩላቸውም ተናግረዋል።
በውይይቱ ከወላጆች ለቀጣይ ሥራ የሚሆን መረጃ መገኘቱ ተሰምቷል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታገቱ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚያሳይ የተረጋገጠ መረጃም ሆነ ማስረጃ አለመኖሩን ለወላጆቻቸው ማስረዳታቸውንም አቶ ንጉሡ ገልጸዋል።
መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ሲባል በጥንቃቄና አስተውሎት እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ችግሩን ለመፍታት ወላጆች በምን መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ምክር ለግሰዋል።
በአጠቃላይ በመድረኩ የጸጥታ መዋቅሩና የፖለቲካ አመራሩ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ያለምንም እረፍት እየሠራ መሆኑ ተገልጾ መተማማን ላይ ከመደረሱ ባሻገር ፤ የታገቱ ተማሪ ወላጆች በበኩላቸው መንግስት በአካል በማግኘት ስለአወያያቸው ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ተገንዝበናል ማለታቸው ተሰምቷል።
በውይይቱ መንግሥት ጉዳዩን በሚመለከት እስካሁን ያከናወነውን ተግባር መረዳታቸውን የተናገሩት የታጋች ተማሪ ወላጆች ፤ መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ልክ ከሠራ ልጆቻቸውን የማግኘት ተስፋቸው ትልቅ እንደሆነም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለቀጣዮ አገራዊ ምርጫ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን መቆጣጠር ይገባል ተባለ
ቀጣዮ አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ስርጭት መቆጣጠር እንደሚገባ የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማዕከል ወይም ካርድ አስታወቀ።
በአገሪቱ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ስርጭት ለመከላከል በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተነግሯል።
መንግሥት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በማስፈን፣ የተቋማቱን ተዓማኒነት በማሳደግ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤ የሚጨምሩ ሥራዎችን በማከናወን የሚመለከታቸው አካላት ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ መሥራት ይገባልም ተብሏል።
ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ባደረገው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ቅኝት፣ በኢትዮጵያ የተደራጁ የመረጃ ማዛባት ሥራዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ስርጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ አስረድቷል። ይህ ሁኔታም አገራዊ ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት ሊጨምር እንደሚችልም ነው የመብቶች ዴሞክራሲና ብልጽግና ማዕከል የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ ብርሃኔ ያብራሩት።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዜጎች በቂ እና ትክክለኛ መረጃ ኖሯቸው የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ ፤ ሆኖምመሰል የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች የዜጎችን በቂ መረጃ የማግኘት መብት ሊያሰተጓጉሉ ይችላሉም ብሏል። በምርጫ ወቅት መሰል ችግሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ከወዲሁ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብም ይፋዊ የተማፅእኖ መልእክት ተላልፏል።
በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን ነፃ መሆናቸው ተረጋገጠ
በቻይና በከፍተኛ ሁኔታ የተዛመተውና በርካቶችን እየቀጠፈ ባለው ኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩት አራት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን መረጋገጡን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ይፋ አደረገ።
ማክሰኞ ዕለት በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩና ከቻይና የተመለሱ አራት ኢትዮጵያውያን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መገኘታቸውን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ገልጾ ነበር። በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ለተጠርጣሪ ህመምተኞቹ የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምረመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን መጠቆሙ ይታወሳል።
ወደ ደቡብ አፍሪካ ለተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ የተላኩት የአራቱ ተጠርጣሪዎች ውጤት ከኖቭል ኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል ሚኒስትር መ/ቤቱ አስታውቋል ።
ከእነዚህ አራት ኢትዮጵያውያን መካከል ሦስቱ ቫይረሱ በተከሰተበት ዉሃን ግዛት ተማሪ ነበሩ። በበሽታው የተጠረጠሩት ግለሰቦቹ በለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተለይተው ክትትል እንደሚደረግላቸው በወቅቱ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በቻይና አንድ ግዛት ውስጥ የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ መላው ቻይናን ማዳረሱንና በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 170 እንደደረሰ መረዳት ተችሏል።
ሥልጠና አቋርጠው የወጡት የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች የዱከም ኢንዱስትሪ ዞንን ጎበኙ
የአዲሱ ብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በዱከም ከተማ የሚገኘውን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ዛሬ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
ባለሥልጣናቱ በጉብኝታቸውም የኢንዱስትሪ ዞኑን የስራ እንቅሰቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል ነው የተባለው።
የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር ስልጠና ከጥር 16 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ስልጠና ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ ስልጠናውም እስከ የካቲት 2 2012 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል ኢትዮጵያ ነገ በባለፈው ሳምንት የዜና እወጃው መዘገቡ አይዘነጋም።
ይህ ስልጠና ፓርቲው ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና አገራዊ ውህድ ፓርቲ ከተሸጋገረ በኋላ በየደረጃው ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በብልፅግና ፓርቲ ምንነትና አስተሳሰብ ዙሪያ የተዘጋጀ ነው ። በተጨማሪም በተጀመረው ሃገራዊ ለውጥና ከለውጡ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ እርምጃዎች፣ በተገኙ ስኬቶችና የቀጣይ ስጋቶች ላይ አመራሩ የተግባር አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑም ተዘግቧል።
በሌላ በኩል ለአገሪቱ ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባትና ለቀጣይ ተልዕኮ ለማዘጋጀት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ቢባልም ዋነኛ አላማው ግን ከፍተኛ አመራሮቹ ለቀጣዮ አገራዊ ምርጫ አዲሱ ውህድ ፓርቲ ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉ በርካታ ካድሬዎችን ማፍራት የሚችሉበትን ብቃት ለማጎልበት ያለመ እንደሆነ ታማኝ ምንጮቻችን ነግረውናል።