በትግራይ ነዋሪዎች ከንግድ ባንክ ከ2 ሺኅ ብር በላይ እንዳያወጡ ታገደ
በህወሓት ቀጥተኛ ጫና ውስጥ የወደቀችው ትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ገንዘብ ማውጣት አለመቻላቸው እየተነገረ ነው::
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ደንበኞች ገንዘብ ማውጣት አለመቻላቸውን በመናገር ላይ ናቸው።
በአብዛኞቹ የኢዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ከአንድ ሺህና ከሁለት ሺህ ብር በላይ ማውጣት እንደማይችሉ ተነግሮናል ሲሉም የችግሩን ጥልቀት ጠቁመዋል።
በዓድዋ ከተማ ሰሎዳ ዓዲኣቡን በተባለው ቅርንጫፍ ብር ለማውጣት የሄደችው ተጠቃሚ “ከሁለት ሺህ ብር በላይ ማውጣት አትችይም” መባሏን ስትጠቁም፤ በዚህ ከተማ የሚገኙ ሌሎች ቅርንጫፎች ደግሞ ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሲሰጥ እንደዋለ ከዚያ በላይ ግን ብር የለም መባላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በውቅሮ ክልተውላዕሎ የሚገኘው ቅርንጫፍ ከአንድ ሺህ ብር በላይ አልሰጥም ማለቱን የባንኩ ደንበኞች ተናግረዋል። አምስት ሺህ ብር ለማውጣት ወደ ቅርንጫፉ ሂዳ፤ አንድ ሺህ ብር ብቻ የተሰጣት አንድ ኗሪም በተመሳሳይ የገጠማትን ተናግራለች። ከዚህ መጠን በላይ ማውጣት አትችሉም ተብለው የተከለከሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ተጨንቀው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ደምወዛቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚከፈላቸው የክልሉ የመንግሥት ሠራተኛ “ብር የለም ጠብቁ” መባላቸውን ገልጸዋል:: በመቀሌ የሚገኙ ቅርንጫፎችም በወረፋ ተጨናንቀውና የጠየቁት ብር ሳይሰጣቸው ስለቀረ ሲበሳጩና በቁጣ ሲናገሩ ታይቷል።
እንደምክንያት የተጠቀሰው የተለያዩ ሰዎች ገንዘባቸው ከባንኩ እያወጡ እንደሆነ ነው። ችግሩ በሌሎች አከባቢዎችና በሌሎች የግል ባንኮችም፤ ሊከሰት እንደሚችል ተገምቷል።
በትግራይ ውስጥ፤ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የተሰጣቸው አራት ዋና ዋና አከፋፈይ ማዕከላት በመቀለ፣ በማይጨው፣ በዓድዋና ሽረ እንዳሥላሰ የሚገኙ ሲሆን፤ በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ የብር እጥረት ስለአጋጠመ ነው ወደ ቅርንጫፎች ብር ያልተላከው መባሉን አንድ የንግድ ባንክ ሠራተኛ ተናግሯል ::
ቢቢሲ ያናገራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አልሰን አሰፋ ግን የገንዘብ ዕጥረት እንደሌለ ጠቁመው፤ “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዕጥረት አልገጠመውም። ምናልባት የኔትወርክ ችግር ቢኖርበት ነው” በማለት የተባለው ውሸት ነው ሲሉ አጣጥለዋል።
“ከ2 ሺህ ብር በላይ አታወጡም የሚል ህግም የለም” የሚሉት አቶ አልሰን፤ ያለው ችግር ከቴሌ ጋር የሚያያዝ እንደሆነና ገንዘብ የማውጣት ገደቡንም በተመለከተ “ይሄ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። የባንኩ አሰራርም አይደለም” ብለዋል።
“ማንኛውም ሰው በባንኩ ያስቀመጠውን ብር በየትኛውም ቅርንጫፍ የማውጣት መብት አለው። ይህንን መብቱ የመከልከል መብት የለንም።” ሲሉ የትግራይ ነዋሪዎችን ወቀሳ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ጃዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ ነው ሲል ኦፌኮ አስታወቀ
በመራራ ጉዲናና በቀለ ገርባ የሚመራው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በአባልነት የመዘገበው ጃዋር መሐመድ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ነው ሲል አስታወቀ።
በአገሪቱ ሕግ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ስለማይችሉ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው የተነገረው ጃዋር መሐመድ የፓርቲው አባል መሆኑን ተከትሎ በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከአንድም ሁለት ጊዜ ግለሰቡ ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ለፓርቲው በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
የምርጫ ቦርድን ተደጋጋሚ ጥያቄ ያልካዱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፓርቲው ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ “ጀዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ እንዳይሆን ገደብ የሚጥልበት ሕግ የለም፤ ስለዚህም ኢትዮጵያዊ ነው” የሚል አስገራሚ ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
ለረጅም ዓመታት የአሜሪካ ዜጋ እንደሆነ የሚታወቀው ጀዋር መሐመድ በኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል በመሆን በቅርቡ ቀጥተኛ የፖለቲካ እንቀስቃሴ ውስጥ መግባቱ ከወዲሁ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
በአገሪቱ ሕግ መሠረ አንድ የውጪ አገር ዜጋ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንደሌለው መታወቁ ደግሞ ዜጎች ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄን እንዲያቀርቡ አድርጓል።
” በምርጫ ቦርድ በኩል መጀመሪያም ሆነ ለሁለተኛ ጊዜ የተላከው የድብዳቤ ይዘት አንድ አይነት ነው። የአቶ ጃዋር መሐመድን የዜግነት ሁኔታን ነው የጠየቁን። የዚህን አገር ዜግነት አግኝቷል ወይስ አላገኝም የሚለው ነው። ቦርዱ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው በምርጫ መሳተፍ እንማይችል ጠቀሶ ነው ጥያቄውን ያቀረበው” የሚሉት አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ ከምርጫ ቦርድ ይህ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ጃዋር መሐመድ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ በጽሑፍ መጠየቃቸውን እና ጃዋርም ለምርጫ ቦርድ ምላሽ የሚሆን መልስ “የዜግነት አዋጅ ቁጥር 378/1996” ጠቅሶ ለፓርቲው መስጠቱን ይፋ አድርገዋል።
“ጃዋር ምላሽ እንዲሰጥ በጽሑፍ አሳወቅነው። እሱም ምላሽ ሰጥቶናል። ይህንንም ለቦርዱ ለመስጠት ዝግጅት ላይ ነው ያለነው። እስከ ጥር 29 ነው ምላሽ ስጡ ያሉን፤ እኛም አዋጅ 378/1996 አንቀጽ 22 ጠቅሰን ከዚያ በፊት ምላሽ እንሰጣቸዋለን” በማለት የተናገሩት የኦፌኮ አመራር፤ ” ጃዋር አንደኛ ወደ አገር ተመልሶ እየኖረ ነው። ሁለተኛ ዜግነቱን ለአሜሪካ መልሷል። ሦስተኛ ደግሞ ለሚመለከተው አካል ዜግነቱን እንዲመለስለት አመልክቷል። ከዚህ ውጪ ሕግ የሚጠይቀው ነገር የለም። ስለዚህ ጃዋር መሐመድ የኢትዮጵያ ዜጋ ነው” ሲሉም የፓርቲያቸውን አቋም አመላክተዋል ።
ከሳምንታት በፊት ጃዋር መሐመድ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፤ በምርጫው ላይ ለመሳተፍ የአሜሪካ ፓስፖርቱን የመመለስ ሂደቱ ከምን እንዳደረሰ ተጠይቆ ፤ “ፓስፖርቴን መልሼያለሁ። በእኔ በኩል የሚጠበቀውን ጨርሺያለሁ። ምንም የሚያግደን ነገር የለም” ሲል ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም።
መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተከትሎ የምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎች መሸሽ ጀመሩ
ከፍተኛ የሆነ ውጥረት የነገሰባት እና የተለያዮ የታጠቁ ኃይሎች ይንቀሳቀሱባታል በምትባለው በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የተለያዮ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ጥለው በመሸሽ ላይ ናቸው::
በምዕራብ ኦሮምያ በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የተማረሩና ሰምኑን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ስፍራው ገብቶ እየወሰደ ባለው እርምጃ የተደናገጡም የተማረሩም በርካታ ነዋሪዎች ወደ ጋምቤላና ሌሎችም ከተሞች እየሸሹ እንደሆነ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት ችለናል።
በተለይም በቅርቡ የታገቱትን የአማራ ተወላጅ የሆኑ የዮንቨርስቲ ተማሪዎችን ተከትሎ በምዕራብ ወለጋ ጫካዎች ውስጥ እና በአንዳንድ መንደሮች ውስጥ መሽገዋል ባላቸው ታጣቂዎች ላይ መንግሥት የሚወስደው ከባድ እርምጃ ነዋሪዎችን ማስደንገጡና ስጋት ላይ መጣሉ ተሰምቷል::
በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና ራሳቸውን የነፃነት ተዋጊዎች ነን ብለው በሚጠሩት ሸማቂዎች መካከል የሚደረገው ተኩስ ልውውጥ እስከዛሬ ከታዮት የጦር እንቅስቃሴዎች ሁሉ የላቀ መሆኑ በህይወታቸው ላይ አደጋ ተጋርጦብናል የሚሉ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደሌላ ስፍራ በከፍተኛ ሁኔታ በመሸሽ ላይ ናቸው::
መዓዛ አሸናፊና ብርቱካን ሚዴቅሳ በቀጣዮ አገራዊ ምርጫ ችግሮች ላይ ተወያዮ
መጥቷል የተባለውን ለውጥ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወሳኝ ሓላፊነት ከተሰጣቸው የሴት ሹማምንት መሀል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በነሐሴ ወር ይካሄዳል ተብል በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ተወየ
የፍትህ ሥርዓቱንና የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መብትን በትክክል ያስጠብቃሉ ተብሎ በመንግሥትም ሆነ በህዝብ ተስፋ የተጣለባቸው ሁለቱ ሹማምንት፤ በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ይዘትና አፈጻጸም፣ ወደ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዓይነትና ባህሪያት፣ እንዲሁም የምርጫና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች ስለሚደራጁባቸው የህግ አግባቦች፣ የዳኞች ስልጠና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ነው፡፡
ፍርድ ቤቶች ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡላቸው አቤቱታ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የህዝብ አመኔታ እንዲኖራቸው፣ በተለይም ከምርጫ ድምጽ ቆጠራና ውጤት ጋር ተያይዞ ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአጭር ጊዜ ውሳኔ ስለሚያገኙበት አሠራር፤ እንዲሁም የምርጫውን ሂደት ፍትሃዊነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ሊወሰድ ስለሚገባበት ሁኔታም በመዓዛ አሸናፊና ብርቱካን ሚዴቅሳ የተመሩ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ ሓላፊዎች በጥልቀት መክረዋል፡፡
በተጨማሪም በምርጫ አፈጻጸም ጉዳዮች ላይ ሰፊና የተሻለ ልምድ ካላቸው የአፍሪካ አገራት ዳኞችና የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ ከፍርድ ቤት ሚና አንጻር መልካም ተሞክሮ የሚቀስሙበት ሁኔታ እንዲመቻች አቅጣጫ አስቀምጠዋል እየተባለ ነው::
መንግሥት የታገቱትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ ቸልተኛ ሆኗል ሲል ኢዜማ አስታወቀ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎችን የማስለቀቅ ሓላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በየትኛውም ወገን የሚፈጸም ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው ብሏል፡፡ መንግስት ከየትኛውም አደረጃጀትም ሆነ ቡድን በላይ ጸጥታን ለማስከበር አቅም አለው ያሉት የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ይህን ስልጣኑን በመጠቀም ረገድ ግን ቸልተኝነት አሳይተዋል በማለት ተናግረዋል፡፡
በደምቢ ዶሎ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ መንግሥት የተማሪዎችን ህይወት በመጠበቅ ረገድ ሓላፊነቱን አለመወጣቱን ያሳየ ነው ያለው ፓርቲው፣ መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ተግባር በአግባቡ እንዲወጣም ጠይቋል፡፡
ለታገቱ ተማሪዎች የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም ክልል ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች ተናቦ መስራት የሚፈልግ መሆኑን የገለፁት አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ መንግስት ከላይ የሚያሳየው የፖለቲካ አሳታፊነት ወደታች አለመውረዱ ህግን እና ስርዓትን ከማያከብሩ ሰዎች ጋር ተደማምሮ ለስብሰባ በምንቀሳቀስበት ወቅት ተግዳሮት እየገጠመን ነው ብለዋል::
ኢትዮጵያ ቀጣዩን ምርጫ ለማድረግ ዝግጁ ናት ብለን አናምንም ያለው ኢዜማ፣ ምርጫው ይከናወን ከተባለ ግን መንግስት፣ ፓርቲዎችም ሆኑ ዜጎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታ እንዳለባቸው አመላክቶ ኢዜማ የአገር ዐቀፍ ፓርቲ መሆኑን የሚያሳይ የእውቅና ሰርተፍኬት ከምርጫ ቦርድ እንደወሰደ ይፋ አድርጓል፡፡
40 ዓመት በስደት የቆዮትን ጨምሮ ፤ 2 ሺኅ ኢትዮጵያውያን ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ
ለበርካታ ዓመታት በስደት ኬንያ ውስጥ የቆዩ ከሁለት ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ፍቃድ ወደ አገራቸው ሊመለሱ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያዊያኑ በራሳቸው ፍላጎት ለበርካታ ዓመታት ከቆዩባቸው የዳዳብና የካኩማ ስደተኛ ካምፖች ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችላቸው ድጋፍና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደዱት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ለረጅም ጊዜ በስደተኛ ካማፖቹ ውስጥ የቆዩ ሲሆኑ ከመካከላቸውም ከ40 ዓመት በላይ ከአገራቸው ወጥተው በስደት የኖሩ ይገኙባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያዊያኑን ጉዳይ ለመከታተልና አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ዳዳብና ካኩማ የስደተኞች ካማፕ አቅንተው እንደነበረ የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ “ስደተኞቹን የመመለሱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያለምንም ጫና በራሳቸው ፍላጎት የሚከናወን ነው በማለት ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ካኩማና ዳዳብ በተባሉት የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ባለፉት በርካታ ዓመታት በፖለቲካዊና ሰብኣዊ ተግዳሮቶች ምክንያት አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ይገኙባቸዋል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ከኬንያ መንግሥት ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ስደተኞች ለመርዳት የሚያስፈልጉ ተግባራትን በማከናወን የመጀመሪያ ዙር ተመላሾችን በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ ለመመለስ መሰናዶውን አጠናቋል።
በመጀመሪያው ዙር 85፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ2ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጅት ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል ከሰባት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው 400 ህጻናት ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ወደ አገራቸው ለሚመለሱት ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀድሞ አካባቢያቸውና ኑሯቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ ነው ያሉት አምባሳደር መለስ ዓለም።
በኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊ የሆኑ የጉዞ ሰነዶችን እንዳዘጋጀና ለዜጎቹ ጥያቄ ምላሽ እየሰጠም ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ጋር ኬንያን ጨምሮ በሌሎች የአካባቢው አገራት ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን በፈቃዳቸው ለመመለስ የሚያስችል የመግባባያ ሰነድ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ መፈራረሙ ይታወሳል።