የዚያን ቀን ምሽት || በእውቀቱ ስዩም ( ክፍል አንድ)

የዚያን ቀን ምሽት || በእውቀቱ ስዩም ( ክፍል አንድ)

አረጋኸኝ ወራሽ ወደ መድረኩ ወጥቶ ነፋስ ነው ዘመዴ የሚለውን አንጀት አልፎ ፤ ጉበት የሚበላ ዘፈን መዝፈን ጀመረ:: አረጌ ደሞ!! አሁን ይህን በመሰለ ወርቅ ምሽት እንዲህ አይነት ነገር ይዘፈናል?

አርፌ በሰላም እዝናናለሁ ብየ አስቤ ነበር:: “ እንዴ የጠፋ ሰው” የሚል ቃል ሰምቼ ዞር ስል አቦሌን አየሁት :: ጀርባየን በፍቅር ቸብ ሲያደርገኝ ከባለጌ ወንበሬ ልከነበል ለትንሽ ተረፍኩ፤ መዳፉ ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የውሻ ቤት በር ሊዘጋ ይችላል ::፤ አቦሌ neavy seal የሚባለው ያሜሪካ ምርጥ ኮማንዶ አባል ነበር፤ ባላወቅሁት ምክንያት ተቀንሶ፤ ዲፖርት ተደርጎ ሸገር በቦዘኔነት ይኖራል፤

ካንዴም ሁለት ሶስቴ ሲመጣ የሪፓብሊካን ጋርድ አባል አድርገው እንዲቀጥሩት አመልክቶ ነበር፤ over qualified ነህ ብለው ፊት ነሱት::

እና በብዙ አመት ስልጠና ያገኘውን ድብድብ ሳይጠቀምበት ሊያረጅ መቃረቡ ሲያስብ ሁሌም ይቆጨዋል፤ ትንሽ ከቀማመሰ ካጠገቡ ያለውን መሸተኛ ይተናኮላል ::ግን ድብድብ ሲጀመር ራሱን ችሎ አይደባደብም፤ እኔን እንደምንም ብሎ ያለፍላጎቴ ያሳትፈኛል፡:

” አታስብ!! ዛሬ ልደቴን በማስመልከት ካልኮልም ሆነ ከመተናኮል ነፃ ነኝ ” አለና አጠገቤ ተቀመጠ፤

” ስንት አመት ሆነህ” አለው ከቀኝ ጎናችን የተቀመጠ መሸተኛ ::

አቦሌ ወደ ሰውየው ዞሮ ‘ አርባ አመቴ ነው “

“አትመስልም ግን “

“ማለት?”

” ማለቴ የሀያ አመት ጎረምሳ ነው የምትመስል”

” ቀሪውን ሃያ አመት ለራስህ ፈልገከው ነው? ” አለና አቦሌ ሊደበድበው ተነሳ፤

መሀል ገብቼ ገላገልኩ፤

ትንሽ ቆይቶ አንድ ሌላ ጎረምሳ በስልክ “ሆጄቻ ቀባ ቱሬ” እያለ ወደ ክለቡ ገባ፤

አቦሌ ” አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያልተቀባ ነገር ተርፎ ነው ቀባ ቀባ እያልክ ትዛዝ እምታስተላልፍ?” አለና ገፈተረው::

እረ ፕሊስ! ማሎ! ማሎ! ብየ ገላገልኩ፤ ምስራቅ አፍሪካን ማናጋት የሚችል ግጭት ባጭሩ ቀጨሁ::

ይህ በእንዲህ እያለ፤ የክለቡ” ሰኪሩቲ ጋርድ ” ጥግ ላይ ቆሞ፤ ፀጉራም ክንዶቹን ደረቱ ላይ አመሳቅሎ ፤ በቁጣ ያፈጥብናል ::

የቀድሞ የኢትዮጵያ መረብ ኳስ ቡድን ተጫዋች ነበር:: በቅርቡ ደሞ ካንድ ዩንበርሲቲ በቴኳንዶ የክብር ዶክትሬት ተቀብሏል :: ሁሌም ከሰው ጋር ሲጣላ” እንዳልደፍቅህ “ ማለት ይቀናዋል፤

በግራ ጎናችን የተቀመጠው ሰውየ በጣም እምታምር፤ በጣም እምታሳሳ ሴትዮ ከጎኑ አስቀምጦ፤ ጠረጴዛ ላይ ደገፍ ብሎ ቆሞ፤ ጠቅላላ እውቀት ነገር እየለቀቀባት ነው፤

“የዚህንም ዘፈን ግጥም የፃፈው ዝነኛው ገጣሚ የማነ ገብረ አብ ነው” ሲላት ሰማሁ::

አቦሌ ልጂትዋ ወደ ሽንት ቤት እስክትሄድ ጠብቆ ” ጀለስ! ይልማ ገብረአብ ለማለት ፈልገህ ነው ? ወይስ ዘፈናችንን እንደ ባህር በራችን ለሻቢያ አሳልፈህ ልትሰጥ ፈልገህ ነው? ” አለና ኮቱን አውልቆ ሰጠኝ፤

“ኮትህን የምታወልቀው ምን አስበህ ነው?” አለ ሰውየው አንጋጦ አቦሌን በግራ መጋባት እየተመለከተው::

“ላስተኩሰው!” አለና የሰውየውን ኮሌታ ጨምድዶ ያዘው::

ሰውየው፤
” ስማ ማነህ !! ዛሬ ከሰው ጋር ለመደባደብ ዝግጁ አይደለሁም:: ድምፄ በጉንፋን ተዘግቷል ብሎ አፈገፈገ::

” ድምፅ መዘጋት ከድብድብ ጋር ምን አገናኘው?”

” በህግ አምላክ! ለማለትም ሆነ “ድረሱልኝ” ለማለት በቂ ድምፅ ያስፈልጋል” አለ ሰውየው፤

አቦሌ ሳቀና ሰውየውን ለቅቆ ወደ ቦታው ተመለሰ፡

ትንሽ ቆይቶ ሰኪሩቲ ጋርዱ መሸተኞችን እየጣሰ እኛ ጠረጴዛ ላይ መጣ፤፤

“ዝም ብለህ አጠገብህ ያሉት ሰዎች ስትነኩስ አይሃለሁ:: ለመሆኑ አዘሃል?”

አቦሌ ራሱን በአሉታ ነቀነቀ፤

“ እዘዝ ወይ ቦታውን ልቀቅ”

“ሁለቱን ባላረግስ “

“ ያው እደፍቅሃለሁዋ”

ከዝያ ቅጥሎ የተከሰተው ነገር በጣም ከመፍጠኑ የተነሳ ሳተላይቷ እንኳ የመዘገበችው አይመስለኝም። ሰኪሩቲው መሬት ላይ ወድቆ ፊቱን በጆቹ ይዞ ይንከባለላል፤

ከብዙ ትርምስና ግርግር በሁዋላ የክለቡ ባለቤት ደረሰ፤ ወደ ወደቀው ዘበኛ በንቀትና በግርምት እየተመለከተ:-
” በወር አስር ሺህ ብር እየከፈልኩህ እንዴት አንድ ሁለቴ እንኳን ሳትመክት ትወድቃለህ “?!

ዘበኛው በወደቀበት የፊቱን ደም ባይበሉባው እየጠረገ፤
“ የህክምና ርዳታ አይቀድምም ጌታየ?”

በለቤትየው ወደ አቦሌ ዞሮ፤

” ስራ አለህ?!”

” የለኝም ”

” ጥሩ ከዛሬ ጀምሮ የዚህ ክለብ ሰኪሩቲ ጋርድ አድርጌ ቀጥሬሃለሁ፤ ደመወዝህን ነገ እንነጋገራለን፤ ለጊዜው የዚህን ሙትቻ ኪስ ፈትሸህ ለዚህ ምሽት የሚሆንህን ፍራንክ ውሰድ “

LEAVE A REPLY