ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ በቅርቡ እንደሚስማሙ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ

ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ በቅርቡ እንደሚስማሙ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሁሉንም አገራት በሚጠቅም መልኩ ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን ተስፋ  ተናገሩ።

አወዛጋቢው ትራምፕ ይህን ያሉት ትናንት አርብ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት መሆኑን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። በስልክ ውይይቱ  ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ ስለሰነበተው ውይይት ሁለቱ መሪዎች አንስተው የተወያዩ ሲሆንየሚያደርግ፤ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ለመድረስ መቃረቡንና ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ  እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል ተብሏል።

ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ማክሰኞ ጥር 19 ጀምሮ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ድርድር ከታቀደለት ጊዜ ዘግይቶ ትናንት አርብ  መጠናቀቁ ታውቋል። በተከታታይ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ሲደረግ የነበረው ውይይት ላይ የአገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች የህግና የውሃ ጉዳይ ባለሞያዎችን እንዲሁም የአሜሪካ ባለስልጣናትና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተውበታል።

በዚህ ድርደር በሁለት ቀናት ውስጥ ከስምምነት ተደርሶ የግድቡ ውሃ መሙላትና የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ መቋጫ ያገኛል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም ለቀናት በቆየው ውይይት ማብቂያ ላይ የአገራቱ ተወካዮች የግድብን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በድርቅ ወቅት፣ ለዓመታት የተራዘመ ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅትና ለዓመታት የተራዘመ ደረቅ ወቅት ላይ ስለሚኖረው የውሃ አሞላልን በተመለከተ መሰረታዊ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል።

የአገራቱ ሚኒስትሮችም የቴክኒክና የሕግ ቡድኖቻቸው በመሰረታዊነት መግባባት ላይ የተደረሱባቸው ነጥቦችን በማካተት እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ ማዘዛቸውንም በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አረጋግጠዋል። ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ድርድሩ በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን፣ እንዲሁም የአገራችንን ነባርና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብትን በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው” ብሏል።

በሦስቱ አገራት መካከል በህዳሴው ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር በጥር ወር አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተደራዳሪዎቹ መካከል ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ለመዝለቅ ተገዷል። አገራቱ በተለይ ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማውጣት እየገነባቸው ያለው ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ነው። ግብጽ የውሃ ሙሌቱ እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ እንዲሆን ስትጠይቅ ኢትዮጵያ ግን ሙሌቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ያላትን ቁርጠኛ አቋም በግልፅ አስቀምጣለች።በድርድሩ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የየአገራቱ የሕግና የቴክኒክ አማካሪዎችን ተሳታፊ  ነበሩ።

LEAVE A REPLY