እገታው እንደ አገር ከገጠሙን ፈተናዎች ሁሉ ከባዱ ነው ሲሉ ደመቀ መኮንን ተናገሩ
ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የሚገኙ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው እገታ በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ካገጠሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ መሆኑንምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
“በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለማድረስ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ እየተረባረበ” እንገኛለን በማለትም መንግሥት በጉዳዮ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰባት ቤት የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ በእንጅባራ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ላይ ነው እንዲህ ሲሉ የተደመጡት። “መንግሥትን በማመን ከወላጆቻቸው ተነጥለው በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች እገታ በወቅቱ እንደ አገር ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል አንዱ ወቅታዊ ፈተና ነው” ሲሉም የችግሩን ጥልቀት አመላክተዋል።
ተማሪዎቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ መሆኑን የጠቀሱት ም/ጠ/ሚኒስትሩ ተጨባጭ ውጤት ላይ አለመደረሱና የተማሪዎቹ እገታ የወሰደው ረጅም ጊዜ የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦችንና ሕዝቡን ባልተቋጨ ጭንቀትና ባልተፈታ ሐዘን ውስጥ እንዲቆዩ አስገድዷቸዋል ብለዋል ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ችግሩ ውስብስብ መሆኑን ያመላከቱት ደመቀ መኮንንበቅርቡ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር ፊት ለፊት በተደረገ ውይይት በተለያዩ ወገኖች ያልተጣሩና ተለዋዋጭ መረጃዎች መሰራጨታቸው የታጋች ቤተሰቦችን ስጋትና ጭንቀት እጅግ መራር እንዳደረገው ለመረዳት እንደተቻለም አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተማሪዎቹና በወላጆቻቸው ላይ ባጋጠመው አሳዛኝ ክስተት እንደወላጅ “ከልባችን አዝነናል” ሲሉም ስሜታቸውን በሐዘን ድባብ ገልጸዋል። እገታው መንግሥት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅና ችግር ሲያጋጥምም ፈጥኖ የመፍታት አቅሙን ማጠናከር እንዲሁም ድክመቶችን ማረም እንዳለበት በከፍተኛ ሁኔታ ያመላከተ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
• ተለቀዋል የተባሉት ታጋቾች የት ናቸው?
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ዕገታው ያጋጠመበት አካባቢ “የሰላምና የጸጥታ ችግር የሚስተዋልበት በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ የችግሩ ሰለባ ሆነው ቆይተዋል” ሲሉ ድርጊቱ ቀደም ሲልም የነበረ መሆኑን አመልከተዋል።
በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲዎች የተረጋጋ ድባብ እንዳይሰፍን ፍላጎት ባላቸው አካላት ከዚህ በከፋ ደረጃ ጉዳት እንዳይደርስና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ “በየደረጃው የምንገኝ አካላት በተግባር የመፍትሄው አካል ሆኖ መገኘት የሚጠይቀን ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
ከሰሞኑ ስለታገቱ ተማሪዎች ለመጠየቅ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተካሄዱትን ሰልፎችን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰልፎቹ በሰላማዊ ሁኔታ መካሄዳቸው የሚያስመሰግን ነው” ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላትን በተመለከተም “ስህተትን ላለመድገም በማረም፤ እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታ ያለፈቀደውን በግልጽ በማሳወቅ ሁሉም የመፍትሄ አካል መሆን ኃላፊነትም ግዴታችንም ነው” ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ዶክተር ዐቢይ አህመድ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ጎበኙ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከግብፅ ጋር ስላለበት ውዝግብ እንጂ ግንባታው ከምን እንደደረሰ ያልተነገረለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በመስክ ጉብኝቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ጭምርተገኝተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ያለበትን ሁኔታ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፤ የግድቡ የሲቪል እና ኤሌክትሮ መካኒካል የግንባታ ደረጃ ያለበትን ሁኔታም ገምግመዋል።
በጉብኝቱ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሥራ ክንውን እና ግንባታው የደረሰበትን ሁኔታ ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀርቧል።
የክንውን ሁኔታውን በመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕልምን እውን ለማድረግ ውጤታማ ሥራ የማከናወንን አስፈላጊነት በዝርዝር ለባለሙያዎቹ አብራርተዋል። ከአያያዝ ጉድለት የተነሣ የተከሠተውን የሥራ መጓተት ያስታወሱት ጠቅላዮ ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የህዳሴው ግድብ የግንባታ ሥራ የገጠመውን ችግር ለመፍታት መንግሥት የወሰዳቸውን ርምጃዎች አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ የሥራ ዘርፍ ላይ ለተሠማሩት ኩባንያዎች “የዛሬው ጉብኝቴ ከዚህ ቀደም ካደረኩት የተሻለ አፈጻጸም ያየሁበት በመሆኑ አስደስቶኛል” ያሉት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግሥት ተስፋ የጣለበትን ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግም በተናጥል ሳይሆን በህብረት እና በጋራል ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ አመት በሚያደርገው ጉብኝት ቢያንስ ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል ሲያመነጩ ማየት እንደሚፈልጉም መልእክታቸውን ለኩባንያዎቹ አስተላልፈው ፤ በዚህ የግንባታ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታትም መንግስታቸው ሌት ተቀን እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት በጥራትይ እየተሠራ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው ፤ በቀጣይ 2013 ዓ.ም ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉም ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ በቅርቡ እንደሚስማሙ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሁሉንም አገራት በሚጠቅም መልኩ ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን ተስፋ ተናገሩ።
አወዛጋቢው ትራምፕ ይህን ያሉት ትናንት አርብ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት መሆኑን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። በስልክ ውይይቱ ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ ስለሰነበተው ውይይት ሁለቱ መሪዎች አንስተው የተወያዩ ሲሆንየሚያደርግ፤ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ለመድረስ መቃረቡንና ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል ተብሏል።
ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ማክሰኞ ጥር 19 ጀምሮ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ድርድር ከታቀደለት ጊዜ ዘግይቶ ትናንት አርብ መጠናቀቁ ታውቋል። በተከታታይ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ሲደረግ የነበረው ውይይት ላይ የአገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች የህግና የውሃ ጉዳይ ባለሞያዎችን እንዲሁም የአሜሪካ ባለስልጣናትና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተውበታል።
በዚህ ድርደር በሁለት ቀናት ውስጥ ከስምምነት ተደርሶ የግድቡ ውሃ መሙላትና የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ መቋጫ ያገኛል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም ለቀናት በቆየው ውይይት ማብቂያ ላይ የአገራቱ ተወካዮች የግድብን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በድርቅ ወቅት፣ ለዓመታት የተራዘመ ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅትና ለዓመታት የተራዘመ ደረቅ ወቅት ላይ ስለሚኖረው የውሃ አሞላልን በተመለከተ መሰረታዊ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል።
የአገራቱ ሚኒስትሮችም የቴክኒክና የሕግ ቡድኖቻቸው በመሰረታዊነት መግባባት ላይ የተደረሱባቸው ነጥቦችን በማካተት እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ ማዘዛቸውንም በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አረጋግጠዋል። ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ድርድሩ በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን፣ እንዲሁም የአገራችንን ነባርና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብትን በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው” ብሏል።
በሦስቱ አገራት መካከል በህዳሴው ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር በጥር ወር አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተደራዳሪዎቹ መካከል ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ለመዝለቅ ተገዷል። አገራቱ በተለይ ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማውጣት እየገነባቸው ያለው ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ነው። ግብጽ የውሃ ሙሌቱ እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ እንዲሆን ስትጠይቅ ኢትዮጵያ ግን ሙሌቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ያላትን ቁርጠኛ አቋም በግልፅ አስቀምጣለች።በድርድሩ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የየአገራቱ የሕግና የቴክኒክ አማካሪዎችን ተሳታፊ ነበሩ።
መብራት ኃይል በ58 ሚሊዮን ዶላር ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ አስመረቀ
በተለይም በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ የሚስተዋልበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ58 ሚሊየን ዶላር ወጪ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መተግበሪያ ፕሮጀክት ማስመረቁ ተነገረ።
ኢ.አር.ፒ ወይም ኢንተርፕራይዝ ሪሶስር ፕላኒንግ የተሰኘው ይህ መተግበሪያ የተቋሙን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳደግ ባሻገር ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት መስጠት ያስችላል እየተባለለት ነው።ከመተግበሪያው በተጨማሪ ድርጅቱ የተጓዳኝ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ፕሮጀክትም በተያያዥነት እንዳስመረቀ ተሰምቷል።
የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ እና ሌሎች የሥራ ሓላፊዎች በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፥ ፕሮጀክቱ ፍትሀዊ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልፅ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የኃይል ብክነትን ለመቀነስና የተቋሙንም ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።
ተቋሙ ራሱን ለማዘመን በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየሠራ ሲሆን ፤ በዘርፉ ልምድ ካለው ከህንዱ ቴክ ማሂንድራ ኩባንያ ጋር በ2008 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት ሲተገበር መቆየቱና ውጤታማነቱ መረጋገጡ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
አዲሱና ዘመናዊው መተግበሪያ ለዕለታዊ ተግባር የሚያስፈልግ ሀብትና ግብዓትን ማቀናጀት፣ የመረጃ ፍሰትን ማሳለጥ፣ መረጃዎችን በአንድ ቋት ፈጥሮ ወጥነት ባለው መልኩ ማቀናጀት የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር ፤ ለማምረቻ፣ ለግዥና አቅርቦት ስርጭት፣ ለሂሳብ አያያዝ፣ ለግብይት፣ ለደንበኞች መስተንግዶ፣ ለሰው ኃይል ቁጥጥርና ሌሎችም ዘርፎችም አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
ለተገልጋዮች የተቀናጀ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የተጠቃለለና የተደራጀ ሪፖርት ለማግኘት እንደሚያግዝም ተጠቁሟል። የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የሥራ አመራር ቦርዱ መንግሥት ለኃይሉ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራም ለተጠቃሚዎች የኃይል ውስንነት መኖሩ የቅሬታና መልካም አስተዳደር ምንጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድርጅቱ ራሱን አዘምኖ ውጤታማ እንዲሆን መፍትሄዎችን ማስቀመጡን ጠቅሰው፤ አሠራሩን ያልተማከለ ማድረግ፣ የጥገናና መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለሦስተኛ ወገን መስጠትና የውስጥ አሠራሩን በቴክኖሎጂ መቀየር ዋነኛ ትኩረቱ መሆናቸውን ሓላፊው በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል።