ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የበርካታ አንጋፋ ሙዚቀኞችን ሙዚቃ ያቀናበረውና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጉልህ አበርክቶ ያለው ሻለቃ መላኩ ተገኝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ሻለቃ መላኩ ተገኝ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሀሙድ አህመድ እና ብዙነሽ በቀለን ጨምሮ የበርካታ አንጋፋ ድምፃውያንን ሙዚቃ ያቀናበረ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ነበር። የጥላሁን ገሰሰ የ13 ወር ፀጋ፣ ምን ታደርጊዋለሽ፣ አታላይ ነሽ እና ይገርማል እንዲሁም የብዙነሽ በቀለ ጭንቅ ጥብብ የሚሉት ሙዚቃዎች ሻለቃ መላኩ የቅንብር አሻራውን ካኖረባቸው በርካታ ዘፈኖች መሀል ለአብነት ይጠቀሳሉ።
አንጋፋውና ብዙም ያልተዘመረለት ሻለቃ መላኩ ተገኝ በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ለረዥም ጊዜ አገልግሏል። የሙዚቃ ባለሙያው በተወለደ በ75 ዓመቱትናንት ጥር 24 ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ስመ ገናናው የዜማ ደራሲ አየለ ማሞ ሻለቃ መላኩ ተገኝ አሻራው እስከዛሬ የዘለቀ፣ ዜማን በጥሩ ሁኔታ የሚረዳ እና ብቁ የሙዚቃ ሰው ነበር ሲል ይገልጸዋል።
የሻለቃ መላኩ ተገኝ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በምስራቅ ፀሃይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቹ ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አጋሮቹ በተገኙበት ተፈጽሟል።