የሴራ ደባ መንግሥቴን ቢፈታተነውም ኢትዮጵያን ከማስቀጠል አያግደኝም ሲሉ ዶ/ር ዐቢይ ገለፁ

የሴራ ደባ መንግሥቴን ቢፈታተነውም ኢትዮጵያን ከማስቀጠል አያግደኝም ሲሉ ዶ/ር ዐቢይ ገለፁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው የተለያዮ ጥያቄዎች በቂ ምላሽና ማብራሪያ ሰጡ።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተማሪዎቹን ያገተው ማነው?፣ የታገቱት ተማሪዎች ተለቀዋል ተብሏል፤ የት ነው የሚገኙት? ማነው ያገታቸው? የሚለው ጥያቄ ይገኝበታል። ቀደም  ሲል በኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ታዳጊዎችን አግቶ ገንዘብ የመጠየቅ እና ገንዘቡ የማይከፈል ከሆነ የመግደል እርምጃ ተስተውሏል። ይህን አይነት ህገ-ወጥነት ለመግታት ምን እየተደረገ ነው?

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ጉጂ እና ቦረና አካባቢ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግሥት እንዴት ተዘጋጅቷል? ምርጫ በነሐሴ፤ በክረምት ወር እንዲካሄድ መወሰኑ ምን ያህል ትክክለኛ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ተነስተዋል::

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል በርካታ ብሄረሰቦች የክልል እንሁን ጥያቄ እያነሱ እንደሆነ በማስታወስ፤ የብሄረሰቦች ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት በሕገ-መንግሥቱ መሠረት እንጂ ሌላ ጥናት ማድረግ አስፋለጊነት የለውም የሚል ሐሳብም ቀርቧል።

ወደ ትግራይ ክልል ሊያመሩ የነበረ የቻይና ልዑካን ቡድን ወደ ትግራይ እንዳይሄድ ተከልክሏል፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችም ከሥራ ስለመገለላቸው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ከሰሞኑ የተደረገው ውይይት ይዘት ምን እንደሆነ እና የተደረሰበትን ደረጃ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲያብራሩ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

በበርካቶች ዘንድ ይሁንታና ተአማኒነት ያገኘ ምላሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሰጡም አንዳንዶች ግን ምላሻቸውን በማጣጣል ሥርዓቱ አሁንም ችግሮችን ሸፋፋኝና አስመሳይ ነው በማለት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሳባቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል::

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዐቢይ አህመድ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ከመስጠታቸው በፊት፤ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ መንግሥታቸው ምን አይነት ችግር ገጥሞት እንደነበረ እና ችግሮቹን ለመፍታት እየመጣበት ያለውን መንገድ  በጥልቀት አስረድተዋል።

ከእርሳቸው በፊት የነበረው መንግሥት በውስብስብ ‘ኔትወርክ” ተይዞ እንደነበረ እና እርሳቸውም ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ይህን ‘ኔትወርክ ለመበጣጠስ’ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን፤ ይሁን እንጂ ይህ ለመንግሥት ከፍተኛ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። እስከታችኛው የመንግሥት እርከን ድረስ የተዘረጋው ይህ ኔትወርክ፤ ሲፈለግ ማንም እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ አቅም አለው ነበር ያሉት።

“ይህ ውስብስብ እና ጥልፍልፍ ኔትወርክን መገንዘብ ችግር ነበር። ኔትወርኩን መበጣጠስ መከራ ነው። ይህን ኔትወርክ ማግኘት እና መበጠስ ስንጀምር ደግሞ ኔትወርኩ እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ድረስ ትስስር እንዳለው ተረድተናል” ያሉት ዶክተር ዐቢይ ፤ “ሕዝቡ እንዲረዳ የምፈልገው አሁን ያለንበት ጊዜ የመጨረሻ ከፍተኛ ፈተና የተሞላ ወቅት መሆኑን ነው።” ብለዋል።

“የሴራ ፤ የደባ ፖለቲካውን ማስቆም ፈተና ሆኗል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን የምናስቀጥል መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ይህ የሚታለፍ ፈተና ነው።” ሲሉም በለውጡ መንግሥት ህዝብ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ከሰጡት ምላሽ ውስጥ አንኳር ነጥቦችን እንደሚከተለው አቅርበናል:-

  *** በደምቢ ዶሎ ስለተፈጸመው እገታ ***

“ቦኮ ሃራም ሰው ሲያግት ሓላፊነት እወስዳለሁ ብሎ ያውጃል፤ እዚህ ግን እስካሁን ሓላፊነት እወስዳለሁ ያለ የለም::በውል የማይታወቁ ግለሰቦች አሉ። ተጎድተዋል እንዳይባል በእገታው የተጎዳ የለም። ተማሪ ያልሆኑ፤ መኖሪያቸው ሌላ ቦታ የሆኑ ተቀላቅለው አሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር፣ የሰላም ሚንስትር እንዲሁም ከሁሉም የጸጥታ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ምርመራ ላይ ነው፤ ምርመራ ሲጨርሱ የሚደርሱበትን ግልጽ ያደርጋል። ባልተሟላ መረጃ መግለጫ መስጠት ስላልነበረብን ነው መረጃ ሳንሰጥ የቆየነው”  ብለዋል::

*** በምዕራብ ወለጋ እና በጉጂ ስላለው የጸጥታ ችግር ***

“ሁሌም መፍትሄው ሰላማዊ ነው። ነገር ግን ለዲሞክራሲ እጇን በከፈተች አንድ አገር ሁለት የታጠቀ ኃይል ሊኖር አይችልም :: አሁን ላይ መንግሥትን በሁለቱም ጫፍ ጫና ውስጥ የሚስገባ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው” ብለዋል።” ህግን የማስከበር ሥራ ሥንሠራ ኦፕሬሽን ወሰዳችሁ’ እንባላለን”፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ ሕግ የማስከበር ሥራን እየሰራ አይደለም እየተባለ ይወቀሳል “

*** በትግራይ እና በፌደራል መንግሥት መካከል ስላለው ግነኙነት ***

“ከ10 በላይ ሚንስትር ዲኤታዎች አሉ፤ አንድም አልተነሳም፤ ሌላ ሚንስትር እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤም አልተነሱም።  የትግራይን ሕዝብ ያገለለ መንግሥት በኢትዮጵያ ሊኖር አይችልም። እኛም እንዲሆን አንፈቅድም::

“ብልጽግና የፈለገውን ማድረግ ይችላል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የራሱን ካቢኔ መርጦ ማቋቋም ይችላል። ስትፈልጉ ጠቅላይ ሚንስትሩን አንሱ ::ህውሓት አልተገፋም፤ ወደፊት አብረን ልንሰራ እንችላለን” ብለዋል።

     *** ስለ ቀጣዮ አገራዊ ምርጫ ***

“ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ እንደመሆኑ ቦርዱን ጠርታችሁ አናግሩ:: መንግሥት ከመመስረቱ አንድ ወር ቀድሞ ምርጫ መካሄድ አለበት። ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ነው። ግንቦት ወይስ ነሐሴ የሚለውን ምርጫ ቦርድን ጠይቁ። ሥልጣኑ የእናንተ ስለሆነ” ያሉ ሲሆን፤ መንግሥት ከመመስረቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ ምርጫ መካሄድ አለበት ” ሲሉ ተደምጠዋል።

 *** የክልል እና የዞን እንሁን ጥያቄዎች ***

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይይ ክልል የመሆን እና የልማት ጥያቄ አብሮ የሚሄዱ ጥያቄዎች አይደሉም ብለዋል። “ክልል፣ ዞን እና ወረዳ በበዛ ቁጥር ደሞዝተኛ ነው የሚበዛው እንጂ የሕዝብ የልማት ጥያቄ አይደለም የሚመለሰው” ብለዋል።የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 47 በመጥቀስ ሕገ-መንግሥቱ በራሱ ይህን በማስፈጸም ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ክልል እንሁን ጥያቄዎችን በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽም መጠበቅ ስህተት መሆኑን አረጋግጠዋል። “ምርጫ ቦርድ አሁን ላይ ይህን ሁሉ ማስፈጸም ይችላል ብሎ መጠበቁ ትክክል አይሆንም” ብለዋል::

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ኢቲዮ ቴሌኮም፣ መብራት ኃይል እና ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ያስመዘገቡትን ውጤት ተናግረዋል::

 *** ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ***

“ለአሜሪካ እና ዓለም ባንክ ምስጋና ማቅረብ የሚያስፈልገው፤ በሚያውቁን እና አቅም ባላቸው ፊት ስንነጋገር መስማማት ጀምረናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።

ሦስቱም አገራት የመጨረሻ የተባለለትን ስምምነት ለመፈረም ከተዘጋጁ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት “ዝርዝር ዕይታ እና ውይይት ስለሚያስፈልገው [እንዳይፈረም] የሚል አቅጣጫ በመስጠቴ ፊርማው ቆይቷል” ሲሉም አስረድተዋል።

“እስካሁን የነበርነው ጠቅላይ ሚንስትሮች በግድቡ ዙሪያ የአቋም ልዩነት አላሳየንም” ያሉ ሲሆን፤ “ግብጽን ሳይጎዳ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ እንሄዳለን። በዚህ ላይ የአሜሪካም ሆነ የዓለም ባንክ አቋም ይሄ ነው። ይህ የሚሆን ከሆነ ብዙ እርዳታ ቃል ተገብቷል::

የግድቡ መጠን ሳይሆን አሁን ላይ አሞላል እና እንዴት ይለቀቅ የሚባለው ጉዳይ ላይ ተደርሷል። ሁለቱ ሚንስትሮች [የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚንስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር] ያደረጉትን ማድነቅ እፈልጋለሁ”  ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “ከየትኛውም መንግሥታት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ስንወያይ ቀድሞ የሚመጣው የአባይ ጉዳይ ነው ። ድርድሩ በአጭር ጊዜ ይቋጫል ” ሲሉ እምነታቸውን በመልሳቸው ላይ አንጸባርቀዋል::

LEAVE A REPLY