ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ህጋዊ ሰውነት ማጣትን ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ ውሳኔ ሰጥቷል።
ቦርዱ ጉዳዩን ባወጣው መግለጫ ኢህአዴግ በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ማሳወቁን አረጋግጧል። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ግንባር (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ፤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ ቦርዱ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ ማቅረቡ በመግለጫው ተጠቅሷል።
የግንባሩን መፍረስ የመወሰን ሥልጣን የቦርዱ በመሆኑ ግንባሩም ሆነ ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ፤ ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሑፍ ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል? በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ አስተላልፏል።
ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመስረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሰራረት ከሚያሳየው መዝገብ መረዳቱን ገልጿል። በዚህ መሰረት ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ነው ያስታወቀው። የግንባሩን መፍረስ ተከትሎም ቦርዱ የኢሕአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግ መረዳቱን አብራርቷል።
ይህን ተከትሎ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ድርጅቶች አዴፓ ፣ኦዴፓ እና ደኢህዴን ብልጽግና የሚባል ፓርቲ መመስረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ፤ በህጉ መሰረት በብልጽግና እና በህወሓት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑቦርዱ የኢሕአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፦
• ብልጽግና እና ህወሓት የኢሕአዴግ ንብረትና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
• በኢሕአዴግ ስም ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
• ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት 3/4ተኛው ለብልጽግና ፓርቲ ( የሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ¼ተኛ ደግሞ ለህወሓት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሰረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ አሳስቦ፤ በዝርዝር የተጠቀሱትን ተግባራት ፈጽመው በህጉ መሰረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ቀጠን ያለ ትእዛዝ ሰጥቷል።