ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ክልል በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሰጎ እና የሲሌ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ በደረሰው የጎርፍ አደጋ በተለያዩ ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ትላንት (ሰኞ) ሌሊት የጣለውን ዝናብ ተከትሎ የሰጎ እና ሲሌ ወንዝ በመሙላቱ ቆላ ሸሌ፣ ቤሌ ንኡስ፣ ሸሌ ሜላ እና ኤልጎ ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በተጠቀሱት ቀበሌዎች የሚገኙ አብዛኛው ቤቶች በውሃ ተውጠዋል፣ የቤት ንብረት ወድሟል፣ በማሣ ላይ ያለ ቋሚ ሰብል እና ንብረት ላይም ለጊዜው ትክክለኛ መጠኑ ያልተረጋገጠ ጉዳት ደርሷል።
በቀበሌዎቹ ሰብኣዊ እርዳታ በፍጥነት ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጋሞ ዞን አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ይፋ አድርጓል፡፡ በተጨማሪ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ እየጣለ ባለው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በተከሠተ የመሬት ናዳ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑንም ቢሮው ጠቁሟል፡፡
በአደጋው የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር፣ 170 ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል:: ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋርም በቅንጅት እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ አሁን ላይ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ በመቀጠሉ ምክንያት፣ ተመሳሳይ አደጋ ሊደርስ ይችላል ተብሎ በተገመቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን የማንሳት ሥራም ተጀምሯል፡፡