የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት በዓለም ዐቀፍ ካምፓኒ አማካይነት እየተካሄደ ነው

የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት በዓለም ዐቀፍ ካምፓኒ አማካይነት እየተካሄደ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የትራንስፖርት ሚኒስቴር ኢፒቲሳ ከተባለ ዓለም ዐቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በሚያከናውነው የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት ዙሪያ ውይይት ማካሄዱ ተሰማ።

ደህንነታቸውን ባልጠበቁ መንገዶች ምክንያት የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመከላለከል በአገሪቱ የተመረጡ መንገዶች ላይ፣ የመንገድ ደህንነት ግምገማ በማካሄድ የማሻሻያ ሥራዎችን ለመሥራት እቅድ ተይዟል። ይህን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢፒቲሳ ከተባለ ዓለም ዐቀፍ የስፔን አማካሪ ድርጅት ጋር የመንገድ ደህንነት ግምገማ ጥናት እያከናወነ ነው።

ድርጅቱ አደጋ በብዛት በሚከሰትባቸው በተመረጡ 10 የመንገድ ኮሪደሮች ከአዳማ አዋሽ፣ ከሚሌ ጋላፊ፣ ከመቐለ አዲግራት፣ ከአዲስ አበባ ኮምቦልቻ፣ ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ፣ ከአዲስ አበባ ነቀምት፣ ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከሻሸመኔ ሶዶ፣ ከሻሸመኔ ዲላ እንዲሁም የአዲስ አዳማ የክፍያ መንገዶች ጨምሮ የ2 ሺህ ኪሎ ሜትር የግምገማ ጥናቶቹን በማካሄድ ላይ ነው።

በተመረጡት ኮሪደሮች ላይ በሁለቱም የመንገድ አካፋዮች የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) መረጃ በመውሰድ የመንገድ ፍተሻ ተደርጓል። በመሆኑም መንገዱ በሚያቋርጥባቸው 79 ወረዳዎች ላይ በአጠቃላይ 8 ሺህ 166 በትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት በየዕለት የተመዘገቡ የትራፊክ አደጋ መረጃዎችን በመልቀም፣ በኮሪደሮቹ ላይ ያለውን የዓመት አማካይ የትራፊክ መጠንን በመውሰድ የትንተና ሪፖርት ለትራንስፖርት ሚኒስቴር የብሔራዊ መንገድ ደህንነት ጽሕፈት ቤት ማቅረቡም ተገልጿል።

በትንተናው መሰረት ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትሩ መንገድ ውስጥ የመንገድ ደህንነት ኦዲት የሚሠራባቸውን ሦስት የኮሪደር መስፈርቶች፣ በቀጣይ ስልጠና ለመስጠት በተዘጋጀው የመነሻ ምክረ ሃሳብ ውይይት ተደርጓል።

LEAVE A REPLY