የ21 ዓመቱ ካሜሮናዊ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

የ21 ዓመቱ ካሜሮናዊ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሃያ አንድ ዓመቱ ካሜሮናዊው ተማሪ በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆኑ ተረጋገጠ። በቻይና ያንግትዜ ዩኒቨርስቲ  ትምህርቱን ይከታተል የነበረው ተማሪ ዉሃን ከተማ ለጉብኝት በሄደበት ወቅት በበሽታው መያዙን ከዩኒቨርስቲው የወጣው መግለጫ ያሳያል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደሚኖርበት ከተማ ጂንግዙ ከተመለሰም በኋላ በበሽታው መያዙ ተረጋግጧል። የቢቢሲ ዘጋቢ ኪልያን ኒጋላ ከካሜሮኗ መዲና ያውንዴ እንደዘገበው ይህ ዜና መሰማቱ በካሜሮናውያን ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።

300 የሚሆኑ ካሜሮናውያን በዉሃን የሚገኙ ይገኛሉ::ወደየትኛውም ቦታ መንቀሳቀስም ስለማይቻል የውሃ፣ ምግብና ሌሎችም ቁሳቁሶች እጥረትም በማጋጠሙ ችግር ላይ መውደቃቸው እየተነገረ ነው።

ዩኒቨርስቲው ለተማሪው ቤተሰቦች እንዲሁም ለኤምባሲው  የወጣቱን በቫይረሱ መያዝ ያሳወቀ ሲሆን ህክምናም እየተከታተለ መሆኑን ከማረጋገጡ ባሻገር በአሁኑ ሰዓት የሰውነት ሙቀቱ እየተስካከለ እንደሆነ፣ የምግብ ፍላጎቱም መመለሱን እንዲሁም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም በመግለጫው ላይ ይፋ አድርጓል ።

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች በቻይና የሚገኙ ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ መዛመቱን ተከትሎ በርካታ መንግሥታት ከቻይና በተለይም ከዉሃን እንዲያወጧቸው ቢማፀኑም ምላሽ አላገኙም።

ባለፈው ሳምንት በዉሃን የሚገኙ ካሜሮናውያን ለፕሬዚዳንታቸው ፓውል ቢያ ቤጂንግ የሚገኘው ኤምባሲ ምንም እርዳታ እያደረገላቸው እንዳልሆነ እንዲሁም መሰረታዊ የሸቀጥ ፍጆታዎችም እጥረት አለ በማለት ደብዳቤ ፅፈው ነበር።

LEAVE A REPLY