የታከለ ኡማ መግላጫ መእመናንን አበሳጭቷል
ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጥር 26 እኩለ ሌሊት በቦሌ ክፍለ ከተማ 22 ተብሎ በሚጠራው ሰፈር: ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል አካባቢ ለረጅም ጊዜ ቆሻሻ መጣያ በነበረ ቦታ ላይ የተሰራ ቤተ ክርስቲያንን ሊያፈርሱ በመጡ ፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት ሁለት ወጣቶች ህይወታቸውን ሲያጡ 18 ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
ከሌሊቱ 1 ሰዓት (1AM) ላይ ምእመናን በጸሎት ላይ በነበሩበት ወቅት የመጡት አፍራሽ ግብር ኃይሎች ጋር በተከስተ ግጭት ነው ሚሊዮን እና ሚኪ የተባሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመተው የተገደሉት።
በተጠቀሰው ስፍራ አካባቢ አዲስ የፈለቀ ፀበል መኖሩን ተከትሎ ቤተክርስቲያን በአነስተኛ ደረጃ ተቋቁሞ ወደፊት በትልቁ ይሠራል በሚል ስፍራው ታጥሮ ተቀምጦ ነበር፡፡ ሆኖም የከተማ አስተዳደር ቦታው ህገ ወጥ ይዞታ ነው በማለት ማክሰኞ ሌሊት የፀጥታ አካላት መጥተው ማፍረስ ሞክረዋል፥፥ በእርምጃቸው የተበሳጩት የአካባቢው ነዋሪዎች ድርጊቱን እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል፡፡
የከተማ መስተዳድሩ በከንቲባ ታከለ ዑማ አማካይነት በቅርቡ ለፓትርያርኩ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን የይዞታ ባለቤትነት ማረገገጫ በሰጠበት ወቅት ፤ ከንቲባው በቀጣይ በእንጥልጥል ላይያሉ የቤተክርስቲያን ይዞታ ባለቤትነታቸውን ለማረጋገጥ ትኩረትሰጥተው እየሠሩ እንደሚገኙ ገልፀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትናንትእኩለሌሊት ለመንፈሳዊ ክብረ በዓል ዝግጅት እየተደረገ፣ሕብረተሰቡም ፀሎት እያደረገ ባለበት አሳች ሰዓት (ከሌሊቱ 1 ሰዓት አካባቢ) አንስቶ እስከ ንጋት የዘለቀ እርምጃ ፖሊስ መውሰዱ ተሰምቷል፡፡
የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ሓላፊ የሆኑት መልአከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ፤ ስለ ጉዳዩ ሲያስረዱ ምዕመኑ ለክብረ በዓል እየተዘጋጀ ባለበት ዕለት ፣ ፖሊስ ለምን እርምጃውን በውድቅት ሌሊት መውሰድ እንደፈለገ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጠቁመው፤ በሰዓቱ በነበረው ግጭት ሁለት ወጣቶች በጥይት ሲገደሉ፤ ሌሎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባቸውን አስረድተዋል፡፡
የቦታውን ባለቤትነት በተመለከተ ከአስር ዓመት በፊት ጥያቄ ቀርቦበት በጊዜው በመንግሥት ባለስልጣናት መቀያየር ምክንያት ምላሽ ሳያገኝ የቆየበት ሂደት እንዳለ የጠቀሱት ሓላፊ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ይፋዊ ደብዳቤ ለወረዳው ፅፎ እየተከታተለ ነበርም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
መልዐከ ሕይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ በክስተቱ የሞቱ ወጣቶችን ቤተሰቦችን በማግኘት መፅናናታቸውንና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በሆስፒታሎች ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ተሰምቷል፡፡
ሁኔታውን ማውገዛቸውን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በፌስ ቡክ ገጻቸው ገልጸዋል። ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት ጥያቄዎች ምክንያት አንድም የሰው ሕይወት ይጠፋል ብለን አስበን አናውቅም ብለዋል።
ከንቲባው በዚሁ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ቃል በየትኛውም ወገን ያሉ የጥፋቱ አካላትን በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን ማለታቸውን ተከትሎ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ከሃላፊነት ለመሸሽ ሲሉ ምእመናንን ከአጥፊ የመንግስት አካላት ጋር ደርበው መጠቆማቸው በዚህ ጥልቅ ሃዘን ላይ ባለንበት ወቅት መስማት አሳዝኖናል ያሉ አስተያየት ሰጭዎች በሰላም አምላካችንን በማመስገን ላይ ሳለን በጥይት ተደብድበን ተገድለን ባለንበት ወቅት ከንቲባው በመንግሥት እና በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት በማለት ምእመኑን ካታጣቂዎች ጋር መደመራችው አንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰባት ሰዎች ማሰሩን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል።