ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አዲስ የተወለደ ሕጻን ልጅ ከተወለደ ከ30 ሰዓት በኋላ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘበት የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል:: ይህም ሕጻኑን በበሽታው የተያዘ በዕድሜ ትንሹ ሰው አድርጎታል።
ሕጻኑ የተወለደው የበሽታው መነሻ ናት ተብላ በምትታመነው ዉሃን ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እንደሆነም በመነገር ላይ ነው። የሕፃኑ እናት ከመውለዷ በፊት በተደረገላት ምርመራ የበሽታው ቫይረስ እንዳለባት የታወቀ ቢሆንም፤ በሽታው እንዴት ወደ ሕጻኑ እንተላለፈ ግን እስካሁን ድረስ ግልጽ አልሆነም።
ከ28 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ባጠቃው በዚህ ቫይረስ 563 ሰዎች ሞተዋል:: በበሽታው የተያዙ ህጻናት ቁጥር ግን ውስን እንደሆነ የመንግሥት የዜና ተቋም የሆነው ዢንዋ ዘግቧል:: አዲስ የተወለደው ህጻን ላይ ቫይረሱ ስለመገኘቱ የጠቆሙት ምንጮች ሕጻኑ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና 3.2 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን ገልጸዋል።
ህጻኑ በማህጸን ውስጥ እያለ ቫይረሱ ከእናቱ ተላልፎበት ሊሆን እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች በመናገር ላይ ናቸው። ” አጋጣሚው የኮሮና ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል እንዳለው ተረድተን ተገቢውን ትኩረት እንድንሰጥ ያደርገናል” ሲሉ በዉሃን የህጻናት ሆስፒታል ሃኪም የሆኑት ዜንግ ሊንግኮንግ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ነገር ግን ህጻኑ ምናልባትም ከተወለደ በኋላ ከእናቱ ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪ ሳቢያ በቫይረሱ ተይዞ ሊሆን እንደሚችልም የሚጠራጠሩ የህክምና ባለሙያዎችም በርካታ ናቸው።
“ህጻኑ ቫይረሱ መደበኛ በሆነው የበሽታ መተላለፊያ መንገድ ሊያገኘው ይችላል። ይህም እናቱ በምትስል ጊዜ በትንፋሽ የመተላለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው” ያሉት ደግሞ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ኤፒዴሞሎጂስት የሆኑት ስቴፈን ሞርስ ናቸው።
የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የተያዙት ሰዎች አብዛኞቹ በእድሜ የገፉ ሲሆኑ እስካሁን ባለው መረጃም እድሜያቸው በ49 እና 56 ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ቫይረሱ በህጻናት ላይ መተያቱ የተለመደ ክስተትአይደለም አስብሎታል::