በአዲስ አበባ ከተማ 22 አካባቢ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ እና በቴፒ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት የዜጎች ሕይወት በማለፉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች እና አባላት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን!
የሕግ አግባብን በተከተለ እና ግልፅነት ባለው መንገድ ሕግ እና ሥርዓትን ማስከበር ሲቻል ጨለማን ተገን በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ 22 አካባቢ ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የተያዘን ቦታ ለማስለቀቅ በሚል በተወሰደው የኃይል እርምጃ የሁለት ወጣቶች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ የወጣቶቹን ሕይወት ያጣነው ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በቂ ጥረት ሳይደረግ በተወሰደ የኃይል እርምጃ መሆኑ እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው፡፡
በቴፒ ከተማም በተቀሰቀሰ ግጭት የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ በርካቶችም ቆስለዋል! በአካባቢው ያለው ችግር ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የከረመ ሲሆን በየጊዜው እያገረሸ ዜጎች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት በአካባቢው ያለውን ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመፍታት ሰላም የማስፈን እና የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊኑቱን እንዲወጣ ስንል እናሳስባለን::
ኢዜማ የፀጥታ አካላት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በሚሠሩበት ጊዜ ሁሉ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እዲያክብሩ እና ዜጎችን ከጥፋት እንዲጠብቁ የተሰጣቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እናሳስባለን! መንግሥት ሕዝብን የመጠበቅ ግዴታቸውን የማይወጡ እንዲሁም ለዜጎች መጎዳት እና መበደል ምክንያት የሆኑ አካላትን አጣርቶ በአስቸኳይ ለሕግ እንዲያቀርብ እና ለሕዝብ እንዲያሳውቅ አጥብቀን እንጠይቃለን!
ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች ልባዊ መፅናናትን እንመኛለን!
ጥር 28፣ 2012 ዓ.ም
የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት