ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ስመ ገናናው አሜሪካዊ ራፐር ሊል ዋይን የዘር መሰረቱን ለማወቅ ባደረገው ምርመራ ናይጄሪያዊ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ፤ ናይጄሪያውያን በከፍተኛ ሁኔታ ደስታቸውን እየገለፁ ነው:: የአገሪቱ ባለስልጣናቱም ዜናውን በደስታ ተቀብለውታል ተብሏል።
ውጤቱ ከተገለፀ በኋላ የናይጄሪያ ዲያስፖራ ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቢኬ ዳቢሬ ፣ ሊል ዋይንን “ናይጄሪያዊ ወንድማችን” ሲሉ አሞካሽተውታል። ታዋቂው ራፐር ሊል ዋይን ወደ ናይጄሪያ ሲመጣ አቀባበል እንዲሚያደርጉለትም ተናግረዋል።
የዘር መሰረቱን ለማወቅ ምርመራ ያደረገው ሊል ዋይን ፣ ሪቮልት ለተሰኘ ቴሌቪዥን በሰጠው ማብራሪያ ጣቢያ ባደረገው የዘር ምርመራ 53 በመቶ ናይጄሪያዊ መሆኑን ገልጾ በቀጣይም አገሪቱን የመጎብኘት እቅድ እንዳለው አስታውቋል:: ናይጄሪያውያንም ዜናውን ተከትሎ ደስታቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየገለፁ ነው።
“ሊል ዋይን 53 በመቶ ናይጄሪያዊ ነው፣ ወንድሜ እንደሆነ ሁልጊዜም ይሰማኝ ነበር። ስኑፕ ዶግና ፊፊቲ ሴንትም ናይጄሪያዊ ሳይሆኑ አይቀሩም” በማለት ኢሆማ የተባለ ግለሰብ በትዊተር ገፁ ላይ አስገራሚ ጽሑፍ አስፍሯል።
“የውጭ አገር ታዋቂ ሰዎች ናይጄሪያዊ ነን የሚሉበት ሁኔታ ይገርማል፤ እኛ የማናየው ነገር ይታያቸዋል መሰለኝ” ያለው ደግሞ ሪድባብሎ የተሰኘ ናይጄሪያዊ ነው።
“ሊል ዋይን 53 በመቶ ናይጄሪያዊ መሆኑ ከመጀመሪያው ታውቆኛል :: እንዲያውም የኢቦ ብሔር ነው” የሚል ጽሑፍበትዊተር ገጿ ላይ ያሰፈረች ናይጄሪያዊትም ለአብነት ትጠቀሳለች።