“ ቅናሽ ያደርጋል ታናሽ” || በእውቀቱ ስዩም

“ ቅናሽ ያደርጋል ታናሽ” || በእውቀቱ ስዩም

የመጣሁ ሰሞን ይዠው የመጣሁት ዶላር የሚያልቅ አልመሰለኝም ነበር:: በጣም በጣም አንገርግቦ ቆልቶኝ ነበር፤ ሂሊኮፍተር ከመከራየት ያገደኝ የቅርጫት ኳሱ ንጉስ ሞት ነው፤

በየ አምሳ ሜትሩ “ራይድ ድረስልኝ ” ማለት ልማዴ ሆነ:: ቀስ በቀስ የኪሴ ተርዚና እየሟሸሸ ሲሄድ ይሰማኝ ጀመር፤ ከሰማያዊ ምኒባሶች ጋር አቋርጨው የነበረውን ውል ፈረምኩ፤ ጥቅጥቅ ብሎ በሞላ ምኒባስ ውስጥ ” ጎበዝ ! ምናለ ጠጋ ጠጋ ብትሉልኝ” የሚል አንጀት የሚበላ ድምፅ ከሰማችሁ የኔ ነው :: ብዙ አልቀጠልሁም:: ህዝብ የሚሳፈርበት ሳይሆን ፤የሚሰፈርበት ሃይገር ባስ ፤ “ እንኳን ወደ ቤትህ ተመለስህ” ብሎ ተቀበለኝ፤

የሰፈራችን ነዋሪ ኪሴ እየተመናመነ እንደመጣ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም :: ባለፈው ተጉለት ስጋ ቤት ፊትለፊት ቆሜ ገብስ ቆሎ ስበላ፤ የሆነ ጎረምሳ መጥቶ፤

” ሃይመሌ በውቄ! ትራንስፖርት አገልግሎት ያስፈልጋል?”

ብሎ ጠየቀኝ::

እና መልሴን ሳይጠብቅ ጥግ ላይ ያቆማት አቧራ የጠገበች ሞተር ይዞ ወደኔ ቀረበ :: ሞተሪቱ ፤ ሞተር ሳይክል ከመሆኗ በፊት መድፍ እንደነበረች የጠረጠርኩት ያወጣችውን ምድር አንቀጥቅጥ ድምፅና አንድ ሙሉ ከተማ የሚሰውር ጭስ ሳስተውል ነው::

ከፋኝ!! አልቅስ አልቅስ አለኝ::

” እግዜር ይስጥልኝ! በቅርቡ ስነፅሁፉን ትቼ ማራቶን ለመጀመር እያሰብኩ ስለሆነ ከፊት ከፊት ትመራኛለህ” ብየ አሰናበትኩት፤

“ ቅናሽ ያደርጋል ታናሽ” ይላል ማንኩሴ ሲተርት፤ ከቸገረህ የሚገለገልብህ እንጂ የሚያገለግልህ አታገኝም :: አሁን ከትናንት ወድያ፤ አምሽቼ በላውንደሪው ቤት በር በኩል ሳልፍ ያየሁትን ማመን አቃተኝ:: የላውንደሪ ቤቱ ዘበኛ እንዲታጠብልኝ ወረፋ ያስያዝኩትን ብርድልብስ ለብሶ ይጎማለላል::

“This is unprofessional! ምናምን እያልኩ ያዙኝ ልቀቁኝ ስል ዘበኛው ተረጋግቶ፤

“ በጋራጅ ቱታና በበርኖስ መሀል ታፍኖ ከሚቀመጥብህ እኔ ትከሻ ላይ ሆኖ ቢናፈስልህ ይሻላል ብየ ነው” ብሎ ደረቀ:: በዚህ አላቆመም “ ያናፈስኩበትን ትበጭቅልኛለህ ብየ ሳስብ ጭራሽ ትወቅሰኛለህ?:: ወትሮም እጄ አመድ አፋሽ ነው” እያለ መብከንከን ጀመረ:: በጣም ተሰምቶኝ ፤ ብርድልብሴን ትከሻው ላይ አስቀምጦ ላናፈሰበት ከፍየው ጉዞየን ቀጠልኩ::

በማግስቱ ሌላ ደከም ያለ ላውንደሪ ቤት ሄጄ ::

“ አምስት ካናቴራ! ሁለት ሹራብ አንድ ጂንስ! በስንት ቀን ታደርሽልኛለሽ?”

“ሁለት ሳምንት”

” በሁለት ሳምንት ጊዜማ ኮሮና ይገለኛል”

ትስቅልኛለች ብየ ነበር፤ እ ሷ ወይ ፍንክች እቴ!

“ ታድያ ምን ችግር አለ !! አጥበን ለወራሾችህ እናደርሳለን!”🙁☹️

LEAVE A REPLY