ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከቻይናዋ ውሃን ከተማ የሚመጡ ሁሉም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ መወሰኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።
ኢንስቲቲዩት የኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታ እና በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በመግለጫው፤ የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ እስከ አሁን ድረስ 29 ጥቆማዎች በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ ለሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰዋል ብለዋል።
29ኙ ላይ በተደረገው ማጣራት፣ 14ቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት ያሳዩ ስለነበረ፣ ተለይተው ወደ መቆያ ስፍራ እንዲገቡ ተደርገዋል፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ 11 ናሙናዎች ተልከው ስምንቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን 3 ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የምርምራው ውጤት እየተጠበቀ ሲሆን በቀጣዬቹ ቀናት ተጨማሪ 3 ናሙናዎች ለምርመራ እንደሚላኩ ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተላኩት ውስጥም አምስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አንዱ ቻይናዊ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽሽኝን ቀድሞ ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።
ከቻይና ውሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ መወሰኑን እና ወደ ሀገር ውስጥ እንደገቡ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው አስፈላጊው የህክምና ክትትል ለመንገደኞቹ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ከሌላው መንገደኛ ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን ፤ በተጨማሪም ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮት እንደተዘጋጀም ገልጸዋል። ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የጤና ሁኔታ መከታተል እንዲቻል ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ አገልግሎት መጀመሩም ተሰምቷል።
የኮሮና ቫይረስ ምርመራን በአገር ውስጥ ለማስጀመር የሚረዱ የመመርመሪያ ቁሳቁሶችም ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ፤ መሳሪያዎቹ ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ ምርመራው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ይጀመራል ብለዋል። የኮሮና ቫይረስ በ25 አገራት ላይ የተከሰተ ቢሆንም በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ብቻ እስካሁን የቫይረሱ ተጠቂ አለመገኘቱ ተገልጿል።